Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያልሞከርነው ምን አለ?

ሰላም! ሰላም! ‹‹ሐበሻ ‘ጥበቡን’ ጥበብ ቀሚስ ላይና ምሳሌ ላይ ጨረሰው›› ስል ባሻዬ ሰምተውኝ ኖሮ፣ ‹‹ወሬስ የት ሄዶ?›› ብለው ቀብ አደረጉኝ። እሳቸው ደግሞ ሲመጣባቸው አንዴ ቀጨም ያደረጉትን ነገር በዋዛ አይለቁም። እናም ቀጠል አድርገው (ተቀጣጣይ እሳት እንጂ የማልወደው፣ ነገር ሲቀጣጠል በጉጉት ደሜ ትግ ትግ እንደሚል የታወቀ ነው)፣ ‹‹ይመስለናል እንጂ ይኼ ሳይለፉ ማካበት፣ በአቋራጭ መበልፀግ፣ በተመዘበረ ገንዘብ መነዛነዝ የመጣው እኮ፣ ማልደን ተነስተን ላብ ስናፈስ ከዋልን ለወሬ ለምንቀንሰው ሰዓት በውስጠ ታዋቂነት ዕረፍት ስለሚነሳን ይመስለኛል። አይመስልህም? ‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ ይባላል በአገራችን፤›› ብለው ነገሩን ወደኔ መሩት።

እንኳን በ‘ይመስለኛል! አይመስልህም?’ ዴሞክራት ሆነው ነገሩን ወደኔ መሩት እያልኩ በውጤ ‹‹ልክ ነው!›› ብዬ ዝም አልኩ። አዎ! ታዲያ እንደኔ በቤተ ሙከራ የማይለካ፣ የማይረጋገጥ፣ የማይመሳከርን ነገር እየደመደሙ ነገር ከማስረዘም ማሳጠር ይልመድባችሁ። ሌላ ምን እላለሁ? ዘንድሮ ነገርና ኳስ የሚያስረዝሙት ናቸው ከዋንጫ ፉክክር ሲርቁ ያየናቸው። ወይስ እኔ ብቻ ነኝ የሚታየኝ? አይ እናንተ!

‘መሃረቤን አያችሁ አላየንም?’ ከመጫውታችን በፊት የባሻዬን ጨዋታ ልጨርስላችሁ። ምናሉኝ? በአንድ ቀዬ ትዳራቸው የሚያስቀና አካላቸው ቢያረጅም ከሚስታቸው ጋር ያላቸው ፍቅር እያደር የወጣት የሆነ አዛውንት ነበሩ አሉ። መቼም አበባ ካለ ንብ ያንዣብባል። ስኬታችሁና ደስታችሁ እያደር ምቀኛ ሲያፈራ ስታዩ ጽጌሬዳ ጉያ እሾህ ጠፍቶ እንደማያውቅ አስታውሱ። ምነው ስንት መርሳት የሚገባንን ነገር አንረሳም እያል በጎሳ እያበርን የማይገነባ ነገር ከማስታወስ፣ በሜዳ ሳር ጤዛ መመሰጥ ለኑሮ የሚበጅ ሚስጥር ያካፍላል ይባላል።

እናም አንድ ቀናተኛ የአዛውንቱን ጎጆ ማፍረሻ መላ ሲፈልግ (መቼም ኑሮ ያልተወደደበት መሆን አለበት የቻፓ መላ ትቶ ፍቅር ማፍረሻ መላ ሲፈልግ ጊዜ የሚያጠፋው) ሰነባብቶ ማምለጫውንም አዘጋጅቶ (የቀናተኛም ብሩህ አለው ማለት ነው? ይታያችሁ እንግዲህ) ጠጋ ብሎ ‹‹አንቱ! ኧረ ይህቺ ሚስትዎ ትሄዳለች። ምን ሆና ነው?›› ይላቸዋል። ‹‹አይተሃታል?›› ይላሉ በቸልታ። ‹‹በዓይኔ በብረቱ?›› ይመልሳል። ሰውዬው ሚስታቸውን ወዲያው ጠርተው፣ ‹‹ሰማሽ ሂያጅ ነች ይሉሻል። ይኼው ወሬኛው ፊት ጠየቅኩሽ፤›› ሲሏቸው ሚስታቸውን ወሬኛው ጣልቃ ገብቶ ‹‹አንቱ! እንዴት ያሉ ሰው ነዎት ግን? ትሄዳለች ስልእኮ በሐሳብ ትነሆልላች ማለቴ እንጂ ትወሰልታለች መች ወጣኝ?›› ብሎ ሲቆጣ፣ ‹‹በል ተወው ወንድሜ። ያለዛሬም ሐሳብ ሲወሸም አልሰማሁ፤›› ብለው አባረሩት። ላልደረሰበት የቃላት ጨዋታ አይመስልም አሁን ይኼ ታሪክ? እንዲያው እኮ!

  ያለ ነገር ስለወሬና ወሬኞች ጎነታትዬ እንዳልጀመርኳችሁ ይገባችኋል። አጉል በአሉባልታ አጥብቀን ያላሰርነው ዘቅዝቀን እየተሸከምን የምንደፋው እህል፣ የምንዘጋው ዕድል እያደር ብሷል። እኔም ክፉኛ እያዘንኩ ነው። ሰሞኑን ስሜ በሚያውቀኝ ሁሉ በሐሰት ሲብጠለጠል፣ ሲነሳና ሲጣል ሰነበተ። ካለእናንተ ለማን ይነገራል ብዬ እኮ ነው? ምን ተባልኩላችሁ መሰላችሁ? አንድ ‘ሲኖትራክ’ እዚህ ጫንጮ ተበላሽቶ በቆመበት በተገመተው ይሸጥልኝ የሚል ደንበኛ አላስቆም አላስቀምጥ አለኝና ወጣ ወጣ አበዛሁ። እንደ ወትሮው ግንባሬ የሚመታባቸው ሥፍራዎች ‘አንበርብር የት ደረሰ? በሚሉ ጥያቄዎች ደመቁ። ኋላ አንዱ የወሬ ፈላስፋ፣ ‹‹አልሰማችሁም እስካሁን? አንበርብር እኮ የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ በሌለበት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በማላይበት አገር መኖር በቃኝ’ ብሎ ወደጎረቤት አገር ተሰደደ፤›› ብሎ ነዛው። ዘር እንደ ወሬ ብንዘራ ይህቺ ድንግል መሬት ለሰባት ትውልድ የሚበቃ እህል አታሳፍሰንም ነበር ግን? ይገርማል እኮ።

 ወዲያው ትናንሽና ጥቃቅን ወሬኞች (አንዴ ለኳሽ ያግኙ እንጂ አይቻሉም) ‹‹እውነት ነው ካንደበቱ ሰምተናል። ‘ከዕለት ወደ ዕለት ቅሬታዬ እየበረታ ሄዷል። ልማት ያለ ዴሞክራሲ በአፍንጫዬ ይውጣ ሲል በጆሬዬ ሰምቻለሁ (እኔም ሰምቻለሁ) እኔም የሰማሁ መስሎኛል…›› እየተባባሉ ጫንጮ ተቀምጬ የፖለቲካ ጥገኝነት ፈቃድ በወሬ አስጠይቀው በወሬ አሰጡኝ። ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ደንበኛ፣ የሰማ ሁሉ ጉድ አለ። አምኖ ያበደረ ክስ መሠረተ። የተበደረ ውስኪ አወረደ። እውነትም ጦር ከፈታው ወሬ . . . !

‹‹አኖርሽ ነበረ በሬዬንም ሸጬ፣ አበላሽ ነበረ ወይፈኔን አርጄ፣ በምኔ ልቻልሽ ባንገቴ ተይዤ፤›› አልኩ የተባለውን ስሰማ። ማንጠግቦሽ፣ ‹‹እንኳን አንተ ዝም ያለው ፈጣሪም ዝም አለ ተብሎ ይወነጀላል። በአሉባልታ ይወገራል። ያለ ነው…›› ብላ ልታፅናናኝ ሞከረች። ላያስችል አይሰጥ ሆነና ደግሞ ስመለስ ቀንቶኝ ኮሚሽኔን ተቀብያለሁ። እንዳልኳችሁ አስችሎኝ ጭራሽ የሥራ ሞራሌ ተነሳስቶ አንዳንድ ቦታ ልደውል ትኩረቴን ሰበሰብኩ። ማስታወሻዬን ገላለጥኩ። በእንጥልጥል የያዝኩትን ድለላ ካቆምኩበት ልቀጠል ስልኬን አንስቼ ልክ ልደውል ስል ይደወላል። ‹‹ሃሎ?›› ስል እምነት የጎደለው ድምፅ ‹‹አንበርብር!›› ብሎ ይጮሃል። ‹‹አዎ ነኝ!›› ከማለቴ፣ ‹‹ምንድነው የምሰማው?›› ብሎ አንድ የሚያውቀኝ ያናዝዘኛል። አስተባብዬና አስረድቼ ወሬኛውን በትብብር የእርግማን ናዳ አሸክሜ ስዘጋ ሌላ ስልክ መጣ። ‹‹ሃሎ?›› ስል አገላብጬ እመልሳለሁ ብዬ የተበደርኩት ሰው እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ይጮህብኛል።

‹‹አሁን ከዚህ ወዲያ ለእኛ ገንዘብ እንጂ ፖለቲካ ምናችን ነው? ሰው መቼስ ጫፍ ሳይዝ አይቀጥልም…›› ሲል መዓት ወረደብኝ። እሱንም እንዲሁ አባብዬ ወሬውን ሳስተባብል ሰዓቴ ነጎደ። በልቤ ግልጽነትና ተጠያቂነት ፍፁም ይንገሥ ቢባል መንግሥታት በጀታቸውን በሚቀጥሯቸው ቃል አቀባዮችና ማስተባበያ መድረኮች ሊጨርሱት ይችላሉ ማለት ነው እላለሁ። በትዝብት በመገረም እተክዛለሁ። ከሁሉ ከሁሉ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቀ መባሌ ትዝ ሲለኝ የቂመኛዬን ቀለም እወቅ፣ ማንነት ድረስበት እያለኝ እረበሻለሁ። እንዲያረጋጋኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ስደውል ደግሞ እሱ ያው የምታውቁት ነው ቀለል አድርጎ፣ ‹‹እንኳን የኢኮኖሚ ጥገኝነት ጠየቀ አላሉህ። እንዲያ ቢሉህ ኖሮ ሠርተህ እየኖርክ የምትበላው ሳታጣ ምን ልትሆን ነበር? ይልቅ የስም ኪራይ ጀምር። ሰው በእጅ አዙር በሰው መታወቂያ የልቡን መዘክዘክ የሚፈልግበት ጊዜ ሆኗል፤›› ይለኛል። እስኪ አሁን ካልጠፋ ‘ቢዝነስ’ ስሜን አጥፉ ብዬ ለብሶት መተንፈሻ ላከራይ? ይህ ነበር የቀረኝ!

በሉ እስኪ እንሰነባባበት። ምንም እንኳ የሚሰማውና የሚታየው የመኖር ትጥቃችንን ሊያስፈታ ቢታገለንም ይህቺን ታህል መተንፈሳችን አልጎዳችንም። እሱም ተራው ደርሶ አትቁም እስኪባል ቋሚ ምን ይሆናል አትሉኝም? አዎ! ተስፋ ሳለ ምን ይሆናል። ባሻዬ ምን ሲሉኝ ነበር መሰላችሁ? ‹‹እሱ ኑር እስካለ ድረስ ብታጣ፣ ብትራቆት፣ ብትታረዝ ምን ማድረግ ትችላለለህ? ‘እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም’ ትላለህ። ዳሩ እሱ የከፈተውን ጉሮሮ አረመኔ ሲቆርጠው ዝም እያለ አስቸገረ። ግን መታገስ ነው። ሃይማኖትህ ምንም ሆነ ምን መሠረቱ ትዕግሥትና ፍቅር መሆን አለበት። ይኼውልህ ምሳሌ፡፡ አንድ የቆሎ ተማሪ ‘በእንተ ስለማርያም’ ይላል ጭራሮ አጥር ጥግ ቆሞ። ውስጥ ያሉ እናት ሰምተው ‘ተሜ አትቁም’ ይሉታል። ‘እመ እኔ መቼ ቆሜ? በእኔ ተመስሎ እኮ ፈጣሪ ነው የቆመው’ ቢላቸው ‘ከምኔው አንተ ዘንድ ደረሰ? አሁን ሌማቴ ባዶ መሆኑን ከፍቼ አሳይቼ ሳልከድነው?’ አሉት። ተሜ ተራውን ‘ነው? እንግዲያስ ልቀመጥ’ ብሎ ተማሪነቱን ተወው ይባላል።

‹‹የሚለመን ሳይኖር እንዴት ልለምን ብሎ እኮ ነው። አይ ተሜ! ‘ከሰነፍ ተማሪ ከገንዘብ ቀርቃሪ፣ ከሸምጣጣ ሱሪ ይሰውርህ’ የሚባለው ይኼኔ ነው። ስንፍና የጥበብና የተግሳፅ ጠላት ናት። አየህ፣ ዓለም በማጣት በማግኘት፣ በመውጣት በመውረድ፣ በሞት በሕይወት ጋጣ ስትከፋፈል ታግሶ ለሰነበተ፣ ቆሞ ለታዘበ፣ ታክቶ ላልተቀመጠ የማስተዋልንና የዕውቀትን ብርሃን ታበራለት ዘንድ ነው። ጅብ ቸኩሎ ምን ነከሰ? ቀንድ አትለኝም? ምንድነው እኔን ብቻ የምታስለፈልኝ? አዎ! ሁሉን ታግሰን እኛው በእኛው እዚሁ ተደቋቁሰን ይህቺን ምድር ብናርሳት ታጠግበናለች። ‘ወንድሜ ፊት ነሳኝ’ ብሎ ሰው ያባቱን ርስት ጥሎ ከሄደ ያው ባርነት ያው የባዳ በደል ነው የሚጠብቀው። አፉን የከፈተ ባህር ነው የሚውጠው። አይደለም? መቻል ያሳልፋል። መቻቻል ያሰነብታል።  እህ ሌላማ ያልሞከርነው ምን አለ?›› ሲሉኝ ባሻዬ መልሴ ምንም ነበር! መልካም ሰንበት!            

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት