Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለተፈጠረው የውኃ እጥረት ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጠሁ አለ

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለተፈጠረው የውኃ እጥረት ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጠሁ አለ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በደቡብና በሰሜን አዲስ አበባ የከርሰ ምድር ውኃ ጉድጓዶች በመንጠፋቸው ምክንያት የተፈጠረውን ችግር በጊዜያዊነት መፍታቱን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዓርብ መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ በአቃቂ ጥልቅ ጉድጓዶች መጠባበቂያ የነበሩ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች ወደ ታች ዝቅ እንዲሉ በማድረግ ችግሩን በጊዜያዊነት መፍታቱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መጠባበቂያ ውኃ መሳቢያዎችን በማስመጥ ችግሩ በጊዜያዊነት ተፈቷል፡፡

አቶ አወቀ እንዳሉት፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አዳዲስ ፓምፖች እንዲመረቱ ከቻይናና ከፈረንሣይ ኩባንያዎች ጋር ድርድር ተደርጓል፡፡

በጀቱ ምን ያህል ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አወቀ ሲመልሱ፣ ችግሩን በፍጥነት ለመፍታት የግዥ ሒደቶች እንዳልተጠበቁ ገልጸዋል፡፡ የአቃቂን ግንባታ ካካሄዱት የቻይናና የፈረንሣይ ኩባንያዎች ጋር ዕቃውን እንዲያቀርቡ ድርድር በማድረግ፣ በተለይ ክፍያው በገበያ ዋጋ እንዲፈጽም ስምምነት መደረጉን አቶ አወቀ ገልጸዋል፡፡

ችግር የገጠማቸው የአቃቂ ከርሰ ምድር ጉድጓዶች በሦስት ማዕከላት የሚገኙ ናቸው፡፡ በአንደኛው ማዕከል 17፣ በሁለተኛው 20፣ በሦስተኛው ደግሞ 24 ጥልቅ ጉድጉዶች ይካተታሉ፡፡ እነዚህ ጉድጓዶች ከ500 ሜትር በላይ ጥልቀት ያላቸው ሲሆን፣ የውኃ መሳቢያ ፓምፑ አንድ መቶ ሜትር ላይ ተንጠልጥሎ ተተክሏል፡፡

በወቅቱ ጉድጓዶች በቂ ውኃ ስለነበራቸው የውኃ መሳቢያ ፓምፑ በቂ ውኃ መሳብ ይችል እንደነበር ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ውኃው በመሸሹ የአዲስ አበባ ከተማ አብዛኞቹ መንደሮች ለውኃ እጥረት ተዳርገዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት በፈረቃ በሳምንት አንዴ ውኃ የሚያገኙ አካባቢዎች ለሦስት ቀናት ያገኛሉ፤›› ያሉት አቶ አወቀ ጊዜያዊውን መፍትሔ ጠቁመዋል፡፡

በሰሜን አዲስ አበባ ያሉ የውኃ ጉድጓዶችም ነጥፈው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የከተማው ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ተጨማሪ አሥር ያህል ጉድጓዶችን በመቆፈር ወደ ሥርጭት በማስገባቱ ችግሩ መቀረፉን አመልክቷል፡፡

‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መሻሻል አሳይቷል፤›› ያሉት አቶ አወቀ፣ ለተፈጠረው የውኃ አቅርቦት ቀውስ አስተዋጽኦ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በመቀነሱ የከተማው ውኃ አቅርቦት መሻሻል ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በቀን 608 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ የማመንጨት አቅም አለው፡፡ የከተማውን የውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የገርቢ የውኃ ማመንጫ ፕሮጀክትን ለማስጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...