Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግዙፍ የአሜሪካና የቻይና ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ዞን ሁለተኛ ምዕራፍ ለመገንባት ታቅዷል

ግዙፍ የሆኑ የአሜሪካና የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ በመምጣት ላይ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተካ ገብረኢየሱስ የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ጂያንግሱ ሰንሻይን ግሩፕ የተሰኘ ግዙፍ የቻይና ኩባንያ በኢትዮጵያ 945 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ ጂያንግሱ ታዋቂ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያ መሆኑንና በኢትዮጵያ በአዳማ ከተማ ግዙፍ የሱፍ ጨርቅ ማምረቻ ለማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት የኩባንያው ፕሬዚዳንት አዲስ አበባ በመምጣት መፈረማቸውን አቶ ተካ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው የሱፍ ጨርቆችን እያመረተ ለዓለም አቀፍ ገበያ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡ ጂያንግሱ እ.ኤ.አ. በ1986 ጂያንግይን ግዛት ውስጥ የተመሠረተ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ቡድን ነው፡፡ በጨርቃ ጨርቅና በአልባሳት ምርት፣ በኢነርጂ፣ በሪል ስቴት፣ በመድኃኒትና በኬሚካል፣ እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት የተሰማራ እንደሆነ የኩባንያው ድረ ገጽ ያስረዳል፡፡

በተመሳሳይ ሒውማን ዌል የተባለ የቻይና የመድኃኒት አምራች ኩባንያ በደብረ ብርሃን አካባቢ የመድኃኒት ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩን አቶ ተካ አስረድተዋል፡፡ ሒውማን ዌል ቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገባ ቢጠየቅም ፋብሪካውን በፍጥነት መገንባት በመፈለጉ በደብረ ብርሃን ከተማ አካባቢ ለመገንባት መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ የቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ዞን ለመድኃኒት አምራቾች ተለይቶ በቂሊንጦ አካባቢ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

በተያያዘ ዜና ሃኒዌል የተሰኘ ግዙፍ የአሜሪካ የኮሙዩኒኬሽን ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ገመዶች ማምረቻ ለማቋቋም ፍላጎት እንዳለው መግለጹ ተጠቁሟል፡፡ የሃኒዌል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥተው ኩባንያቸው በኤሌክትሪክ ገመዶች ማምረቻ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን አቶ ተካ ተናግረዋል፡፡

ሃኒዌል ኢንተርናሽናል የመገናኛ መሣሪያዎች፣ የኢንጂነሪንግ አገልግሎቶች የሚሰጥና የአውሮፕላን የተለያዩ ክፍሎች አምራች ኩባንያ ነው፡፡ የኩባንያው ዓመታዊ ገቢ ከ38 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2009 ዓ.ም. 1.2 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር የ35 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

አቶ ተካ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ኮሚሽኑ አሠራሩን በማዘመን የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠቱን፣ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠረ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራ ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኤምባሲዎች በኩል ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር በዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕዮች ላይ በመገኘት የታላላቅ ኩባንያ ኃላፊዎችን እንደሚያነጋግሩና ጥረቱም ውጤት እያስገኘ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን እየተከታተሉ የሚገጥማቸውን ችግር የሚፈቱ አንዳንድ ባለሙያዎችን ኮሚሽኑ መመደቡን አቶ ተካ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ አዲስ የጀመርነው ውጤታማ አሠራር ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ኩባንያ አንድ ባለሙያ መድበናል፡፡ በየሁለት ሳምንቱ እኔ ወይም ኮሚሽነሩ ባሉበት ሪፖርት ያቀርባል፡፡ የትኛው ኩባንያ ምን ዓይነት ችግር እንደገጠመውና እንዴት እንደተፈታ፣ ፕሮጀክቱ ምን እንደደረሰ ሪፖርት የሚደረግበት አሠራር ዘርግተናል፡፡ በቅርብ ነው የጀመርነው፡፡ ግን ጥሩ ውጤት እያገኘንበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት መጀመሩና መንግሥት አገሪቱን ወደ ማምረቻ ማዕከልነት ለመለወጥ ያሳየው ቁርጠኝነት የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ የንግድ ሥራ ተስማሚነት መመዘኛ ሪፖርት ጥሩ ውጤት አስመዝግባ አታውቅም፡፡ በቅርቡ የወጣው የዓለም ባንክ ሪፖርት ኢትዮጵያን ከ190 አገሮች 159ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ አቶ ተካ ኢትዮጵያ ጥሩ ውጤት እንዳላስመዘገበች አምነው፣ ደረጃዋን ከ100 በታች ለማውረድ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአብዛኛው ችግሩ ያለው በሎጂስቲክስ ዘርፍ መሆኑን ገልጸው ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አሠራሮችን በማሻሻል ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከቪዛ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከኢማግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ጋር በቅርበት በመሥራት፣ ለውጭ ባለሀብቶች ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚቆይ ‹‹መልቲፕል ቪዛ›› መስጠት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ባለሀብቶች መሬትና መሠረተ ልማቶች ለማሟላት እንዳይጉላሉና በአጭር ጊዜ ወደ ምርት እንዲገቡ በማሰብ መንግሥት በአዳማ፣ መቐለ፣ ኮምቦልቻ፣ ጂማና ድሬዳዋ ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባት ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ተካ፣ የአራት አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዲስትሪ ፓርኮች ግንባታ በአራት ክልሎች መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከታሰበው በላይ የባለሀብቶች ፍላጎት ጨምሮ በመገኘቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ለመገንባት መታሰቡን ተናግረዋል፡፡ ‹‹መጀመሪያ ከታቀደው በላይ 11 ሼዶች ገንብተናል፡፡ አሁንም በተለይ ከውጭ ባለሀብቶች በቀረበው ጥያቄ ሁለተኛ ምዕራፍ ለመገንባት ታቅዷል፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ንብረት የወደመባቸው ባለሀብቶች የማምረቻ መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ አስገብተው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን፣ ባለሀብቶቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲስተናገዱ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከኤምባሲዎቻቸው ጋር በቅርበት እንደሚሠራና ለአምባሳደሮቻቸው ጉብኝቶች ማመቻቸቱ ተገልጿል፡፡ በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች አማካይነት የማረጋጋትና በአገሪቱ ስለተከሰተው ትክክለኛ ሁኔታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መግለጫዎች መስጠታቸውን አቶ ተካ ተናግረዋል፡፡

‹‹አንድ ሰሞን በተፈጠረው ሁኔታ ባለሀብቶች አልሸሹም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራና በጎረቤት አገሮች ሁሉ ሰላም የሚያስከብር መንግሥት ነው፡፡ የተፈጠረውን ሁኔታ መቆጣጠር እንደሚችል እናውቃለን እያሉ ሥራቸውን ቀጥለዋል፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች