ከምክንያታዊነት ይልቅ እንደ እንግዳ ደራሽ በየጊዜው ብቅ የሚሉ የዋጋ ጭማሪዎች ለአገራችን ገበያ አዲስ አይደሉም፡፡ በአገር ሰላም፣ የተትረፈረፈ ምርት ባለበት ወቅት ምርት ሸሽገው ገበያውን እያጋጋሉ ውጥረት የሚፈጥሩ ነጋዴዎች አድራጎት ቀድሞም የነበረና የቆየ ክፉ አመል እየሆነ መጥቷል፡፡
ዓመት በዓልን አሳበው ተፈላጊ ምርቶች ላይ ዋጋ ቆልለው ሸማቹን ያለ ውዱ ተገዶ፣ ከአቅሙ በላይ ዋጋ እንዲጫንበት ማድረግ የተጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ የነዳጅ ዋጋ በሊትር አሥር ሳንቲም ይጨምራል በተባለ አፍታ፣ የአንድ እንቁላል ዋጋ በ50 ሳንቲም ይንራል፡፡ ይህንን ያልተመጣጠነ አድራጎት ለመቅረፍ ኧረ በሕግ ቢባልም ጆሮ ዳባ ተብሏል፡፡ በዓለም ገበያ አሥር ዶላር በማይሞላ ገንዘብ የሚሸጠው ጂንስ ሱሪ ኢትዮጵያ ሲደርስ በውድ ዋጋ ካልሸጣችሁኝ ሞቼ እገኛለሁ ያለ ይመስል ሦስት፣ አራት እጥፍ ዋጋው ንሮ ሲሸጥ ሸማቹ የሚሞግትበትና የሚጮህበት ያለው አይመስልም፤ ምርጫም የለውም፡፡ በገበያ ዋጋ ወጪና ትራፋቸውን በተገቢው መጠን አስልተው ሳይሆን፣ ስንጥቅ ትርፍ ለማጋበስ ጉጉት ያደረባቸውን በርካቶች የአጭር ርቀት አትራፊዎች ያፈራ ገበያ ተንሰራፍቷል፡፡ ዱባይ ሄድ ብሎ ትንሽ ዕቃ ያመጣ ነጋዴ፣ መቶ በመቶ ካላተረፈ በቀር መሸጥ የማይታሰብ እስኪመስል ድረስ እንደ ሕጋዊ ሥራ ተቆጥሮ የሚሠራበት፣ ሁላችንም በገሃድ የምናውቀው ሐቅ ከሆነም ሰነባብቷል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ሊጨምር ነው በተባለ ማግሥት እንደሸማች ፊታችን ድቅን የሚለው ሥጋት፣ ሰበብ ፈላጊው ገበያ ምን ያህል እንደሚጋጋል ነው፡፡ የደመወዝ ይጨመራል ወሬን የሰማ ቤት አከራይ፣ ገና ጭማሪው ሳይደረግ ተከራዩ ላይ ይህን ያህል ጨምር እያለ ማሳቀቁ የተለመደ ሆኗል፡፡ የሰሞኑን የደመወዝ ጭማሪም ለዚህ እማኝ ማድረግ ግድ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የኖርንበት ነውና፡፡ ሁሉም አከራይ ግን ገፍቶ አዳሪ ነው ማለትም አይደለም፡፡ ከቤሰተብ በላይ አሳቢ፣ የሰው ጉዳት የሚጎዳቸው፣ ችግሩ የሚታያቸው አከራዮች ስንት እንዳሉም መጥቅስ ይገባል፡፡
ከቤት ኪራይ ጭማሪ ባሻገር በደመወዝ ጭማሪ ጦስ ምክንያት ልጆቹን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤትም በሁለት መስመር ወርሃዊ ክፍያችን በዚህን ያህል ጨምሯል ተብሎ መልዕክት ሊደርሰው የሚችለውን ደመወዝተኛም ቤቱ ይቁጠረው፡፡ የምግብ ቤት የምግብ ዝርዝሮች ሳይቀሩ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጎባቸው፣ ተሸሞንሙነው ይቀርባሉ፡፡ እዚህ ግባ የማይባለውን ‹‹የደመወዝ ጭማሪ›› ለመቀራመት የማይዘምት መፈለግ ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡
ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ሰበብ በማድረግ ምርትና ሸቀጦች ላይ ዋጋ የጨመሩ ነጋዴዎች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ፣ ሕገወጦች ስለሆኑ ልክ አስገባቸዋለሁ ያለው ንግድ ሚኒስቴር፣ ይህን መናገሩ ታዲያ ምን አዲስ ነገር አለው ያስብላል፡፡ የሰሞኑ ደመወዝ ጭማሪ ሰበብ ተደረገ እንጂ በሆነ ባልሆነው ዋጋ ማናር የተጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያም ቢሆን የሥራ ኃላፊዎች በተቀያየሩ ቁጥር የሚስተጋባ የገደል ማሚቶ ድምፅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ገበያውን የሚመራው ሕግና ሥርዓት ከመሆን ይልቅ ዛቻና ማስፈራሪያ ላይ የተጣበቀ አካሄድ በመከተል ለውጥ እንደማይመጣ ለመገንዘብ ያዳገተው ይመስላልና ነው፡፡
የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ የነበረው፣ ምርት የሚሸሽገው ወይም ሆን ተብሎ ከገበያ እንዲጠፋ የሚደረገው የምርት ዕጥረት እንደተፈጠረ በማስመሰል እጥፍ ድርብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ለመሸጥ የሚደረግ መሆኑ የሚታወቅና ያፈጀ ታክቲክ ነው፡፡
በሸቃቢ ሚዛኖች፣ በተዛባ ልኬት ሸማቾች መማረር የጀመሩት በዚህ ሰሞን አለመሆኑ ሐቅ ነው፡፡ የነዳጅ ማደያዎችም የሚቸረችሩትን ነዳጅ የሚሸቅቡትም የደመወዝ ጭማሪ ስለተደረገ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ አከራዮችም ተከራያቸውን ማሳቀቅ የጀመሩት ዛሬ እንዳልሆነ ንግድ ሚኒስቴር ባይጠፋውም፣ አሁን ዕርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ግን እስከዛሬስ ምን ሲሠራ ነበር? ብለን እንድንጠይቀው ያስገድደናል፡፡
ለቆየው ችግር ዛሬ ድንገት ተነስቶ ወዮላችሁ የሚለው ንግድ ሚኒስቴር፣ ከዚህ ይልቅ በአግባቡ የንግድ እንቅስቃሴውን መቆጣጠር ባለመቻሉ የተፈጠረ እንደሆነ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ደመወዝ ጭማሪ ስለተደረገ ዋጋ የጨመሩት ላይ ቀድሞ ዕርምት ባለመወሰዱ ምክንያት የምናየው ችግር፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ አጥቶ በማስፈራሪያና ዛቻ ታጥሮ ይገኛል፡፡
ስለዚህ ንግድ ሚኒስቴር እንዲነግረን የምንፈልገው በአግባቡ ዕርምጃ መውሰዱንና ዕርምጃውም ለውጥ ማምጣቱን ብቻም ሳይሆን፣ ዘለቄታዊ ለውጥ የሚያመጣ ሥርዓት መተግበር መቻሉን ነው፡፡ እንደ ሸማች አዲስ ዜና የምንለው ይህ ሆኖ ስናይ ነው፡፡