Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትእንዴት ነህ ድርድር?

  እንዴት ነህ ድርድር?

  ቀን:

  2007 ዓ.ም. የምርጫ ዓመት ነበር፡፡ አሁን/ዛሬ ሦስተኛው ዓመት የሥራ ዘመኑ ውስጥ የሚገኘውን፣ ሁለት ዓመት ተኩል የቀረውን አምስተኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወለደውም ይኼው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 56 ስለፖለቲካ ሥልጣን ሲደነግግ፣ በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል/ያደራጃሉ፣ ይመራል/ይመራሉ ይላል፡፡

  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች የመንግሥት ሥልጣን ይረከባሉ የሚለው የሕገ  መንግሥቱ አንቀጽ 73 ነው፡፡ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል እንደሚመረጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ እንደሚችል፣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት/ፓርቲ ብቻውን በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ሳያገኝ ቀርቶ በጣምራ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክር ቤቱ የነበራቸውን አብላጫነት ያጡ እንደሆነ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተበትኖ በሕዝቡ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች ሌላ ጣምራ መንግሥት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመሥረት እንዲቻል የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የፖለቲካ ድርጅቶቹን እንደሚጋብዝ፣ በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶቹ አዲስ መንግሥት ለመፍጠር ወይም የነበረውን ጣምራ መንግሥት ለመቀጠል ካልቻሉ ግን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተበትኖ አዲስ ምርጫ መደረግ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል፡፡

  የእስካሁኖቹ የኢትዮጵያ አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች ግን የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስቸግር፣ የጣምራ መንግሥት ምሥረታ ወዳጅ ወይም አጋር ፍለጋ ደፋ ቀና ውስጥ የሚያስገባ ችግር ውስጥ ከተው አያውቁም፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ጣጣም ሆነ ፀጋ ለሽርሽር እንኳን ወስዶ ያስተዋወቀን ምርጫ አይተን አናውቅም፡፡ ከዚህም የተነሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫው ውጤት እንዲያ ያልለየለት አሸናፊነት ውስጥ አስገብቷቸው፣ ግራ ገብቷቸው እንደ ፖለቲካ አየሩ፣ እንደ ፖለቲካ አቋማቸው መገጣጠም ገርነትና ክፋት የጥምረት መንግሥት ምሥረታና አጣማጅ አጋር ፍለጋ ፈግፈግ ራመድ፣ ጎብደድ ለጠጥ ሲሉ ለማየት ወይም እንዲህ ያለ ችሎታ እንዳላቸው ወይም ከነጭራሹ እንዲህ ያለ ነገር ስለመኖሩ እንደሚያውቁ ለማወቅ አልታደልንም፡፡ የምርጫ ውጤቶችም ሆኑ ምርጫዎች እንኳንስ መንግሥት ምሥረታ ውስጥ፣ ፓርላማ ውስጥም ምርጫው ውስጥም ጥምር ለማስገባት ይበልጥ ንፉግ እየሆኑ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እየቆጠሩ የሚያሳዩን ከምርጫ እንቅስቃሴ ውጪ በምርጫ ወቅት የግርግር ሰሞን ብቻ ነው፡፡

  በተለይም አምስተኛውን ፓርላማ አምጦ የወለደው (የለም! ጠፍጥፎ የሠራው) አምስተኛው ምርጫ አሸናፊነቱን ያጎናፀፈው መቶ በመቶ ለገዢው ፓርቲ ነው፡፡ በመጀመርያው ምርጫ ለአራት፣ በሁለተኛው ምርጫ ለአሥር፣ በሦስተኛው ምርጫ ለ236፣ በአራተኛው ምርጫ ለአንድ የሌላ (ተቃዋሚ) ፓርቲ አባል መቀመጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በ2007 ዓ.ም. አንድም የ‹‹ባዳ›› ፖለቲካ ፓርቲ ወኪል አያደርስብኝም ብሎ ሁሉንም ጠራርጎ ወስዷል፡፡ የምርጫውንና የምርጫውን ውጤት ገመና አደባባይ ወጥቶ ለመስጠት ግን ብዙ ጊዜ አልወሰደም፡፡ በምርጫው ውጤት መሠረት የተቋቋመው አምስተኛው ፓርላማ የመጀመርያውን የሥራ ዘመን መስከረም መጨረሻ ላይ እንደጀመረ ኅዳር 2008 ዓ.ም. ላይ ዛሬም ድረስ መላ ያላገኘውና በሪፐብሊኩ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ያሳወጀው የ2008/2009 ዓ.ም ትግል ፈነዳ፡፡ እንቅስቃሴውን፣ አመዱን፣ ውድመቱን፣ በዚህ ስም ለመጥራት ‹ፈነዳም› ለማለት የወሰደው ጊዜ፣ ያልተለመደው ውጤት አምጦ የወለደው አፀፋ ዕርምጃ በቂ መነሻ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢሕአዴግ በጥልቀት የመታደስ ምላሽ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲን አጠልቃለሁ፣ የመንግሥት ሥልጣንን የግል መበልፀጊያ ማድረግን እዋጋለሁ፣ የፓርላማ አወካከልን አሻሽላለሁ ባይነቱና ሥራ አጥነትንና የበደል ክምችትን የማቅለል ደፋ ቀናው ሁሉ የመጣው ከዚህ የትግል ግፊት ነው፡፡ አንዱ ጉዳይ ይኼኛው ነው፡፡ ኢሕአዴግ እውነት በጥልቀት እየታደሰ ነው? እውነት የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ፓርቲ ጉዳዩ ገብቶታል? ይኼንን ኢሕአዴግ ራሱም፣ ከኢሕአዴግ ጋር ድርድርና ውይይት የሚያደርጉትና ማድረግ ያለባቸው ሁሉ ሊመልሱት የሚገባ ጥያቄና ጭብጥ ነው፡፡

  የኢሕአዴግ ‹‹በጥልቀት መታደስ›› የመጣው ከትግል ግፊት መሆኑ እውነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በውድመት የቀለመው በልማት ላይ ማኩረፍን ሁሉ ያስመዘገበው አመፅ ተስፋን እንዳመጣ ሁሉ፣ የማነቆ መጥበቅንና የትግል መሸነፍን አስከትሏልና በዚህ ረገድ መንገድ መለወጥ፣ የትግል አቅምን የሚያጠናክር ገዢውን ቡድን ወደ አወንታዊ፣ መደፋፈር የሚስብ፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የዴሞክራሲ ዝንባሌ እንዲፋፋ የሚያግዝ፣ በምርጫ የመሸነፍና ከሥልጣን ወርዶ በሰላም የመኖርን፣ ለመንግሥት ሥልጣን የመወዳደርን አስፈሪነት የሚገፍፍ የትግል ዘዴ ላይ መሰማራት ያስፈልጋል፡፡

  ገዢውን ቡድን ወደ አወንታዊ መደፋፈር መሳብና በውስጡም የዴሞክራሲ ዝንባሌ እንዲፋፋ የማገዝ አስፈላጊነት፣ ኢሕአዴግ ለ25 ዓመታት አሻራውን ባሳረፈበት ኢትዮጵያ ውስጥ የዋና ዋና ጉዳዮች ጅምር ስላለ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ባለንበት ሁኔታ የትግሉ ዋና ዒላማ ገዢው ቡድን ባለመሆኑ ነው፡፡ አንድን መንግሥት እንደምንምና በየትኛውም መንገድ ከሥልጣን አስወግዶ ከዚያ ወዲያ በምርጫ ተወዳድሮ ያሸነፈ ይምራ ብሎ ፎርሙላ እንዳልሠራ የገዛ ራሳችን ታረክ ገና ትኩስ ምሳሌ ነው፡፡ የትግሉ ዋና ዒላማ ገዢው ቡድን ሳይሆን ለብቻዬ ልግዛ ብሎ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ ያደረሰው ብልሽት ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥታዊ አውታሩ ማለትም የደኅንነትና የመከላከያ፣ የፍትሕ፣ የምርጫ፣ የመረጃና የፕሮፓጋንዳ ተቋሙ ሁሉ ከየትኛውም ቡድን ይዞታነትና ወገንተኛነት እንዲላቀቅና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ችሮታነት እንዲያከትም፣ ሁሉም ዓይነት መብቶች በተግባር ኑሮ ውስጥ የሚታዩና ከገዢው ፓርቲ የቁርጠኝነት መሃላ ውጪ የሚኖሩ በማድረግ ላይ ማተኮርና ኢሕአዴግን ሰንጎ የትግሉ አካል እስከ ማድረግ የሰፋ ሥልት ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ኢሕአዴግን በብልህ ትግል ማሯሯጥ ግድ እንደሆነ ማስተዋል ይገባል፡፡

  በዚህ የግዴታም ቢሆን የድርድርና የውይይት ወቅት ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ ችግሮች ላይ የዴሞክራሲ ኃይል መሆን ከፈለጉ፣ መጀመሪያ በዱሮ ሥርዓት ናፋቂነት በማያሳማ የፖለቲካ ጥራት ብልጫ ማምጣት አለባቸው፡፡ ትናንሽ ቡድን እየፈጠሩና ካብ ለካብ እየተያዩና የመያያዝ አስፈላጊነትን ሳያጤኑ የድርድር ኃይል ሊሆኑ የመደራደር አቅማቸውን ዕውን ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ የሆነ ዓይነት አንድነት/ኅብረት ሊያያይዛቸው ይገባል፡፡

  ተቃዋሚዎችን ከምርጫ 1997 ዓ.ም. በላይ ትምህርትና ተሞክሮ የሚሰጣቸው ገጠመኝ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የ1997 ዓ.ም. ምርጫና ድኅረ ምርጫ ትግሉ የያዛቸውና ያሯሯጣቸው የፖለቲካ መስመሮቻቸውን በግልም ሳያጠሩ፣ በጋራም ሳያቀራርቡና ኢዴሞክራሲያዊነትን ሳያራግፉ፣ ከተጠራጣሪነትና ከመሰሪ ሥሌትና ከጠባብ ሥልጣን አፍቃሪነት ሳይላቀቁ፣ እንዲሁም የአገሪቱ መላ ሕዝቦች የተያያዙበትን ጠንካራ ትብብር ሳያበጁ ነው፡፡ ተባብሮና አስተባብሮ በአንድ ልብ የመምራት አቅም ጎድሎ፣ በቅጡ የተጠና አስቀድሞ የተዘጋጀ በውይይት የዳበረ ትልም ጠፍቶ፣ እንደምንም ብሎ ኢሕአዴግን ከመጣል በላይ የዕይታ ድርቅ ጠንቶ ዕድሉ ባከነ፡፡ የባከነው ዕድል ሥልጣን የመያዝ/ያለመያዝ አይደለም፡፡ እንኳንስ ያኔ ከአሥር ዓመት በፊት ትግሉና ግብ ግቡ በዚሁ ከቀጠለ ወደፊትም በምርጫ ማሸነፍ ቢቻል እንኳን ሥልጣን መያዝ በጭራሽ አይቻልም፡፡ የመንግሥትን አውታራት የኢትዮጵያን ዓምደ መንግሥት ከአንድ ወይም ሌላ ቡድን ይዞታነት ማፅዳት ገለልተኛ ማድረግ ሳይቻል በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን መያዝ ዘበት ነው፡፡

  በ1997 ዓ.ም. ተቃዋሚዎች ‹‹የአህያ ባል›› መተረቻ ሆነው የአንዱ ቁርጥ እስኪለይ ሌላው ጥግ በመያዝና ራስን በማዳን ጅል ብልጠት ተራ ገብተው ተደቆሱ፣ አስደቆሱም፡፡

  አሁንም ኢሕአዴግ ትግል አስገድዶት የድርድር መድረክ ተከፍቷል፡፡ ይኼ መድረክ የዘሩትን ማብቀል የሚችል ነው፡፡ መድረኩ የሚገኝበት የአየር ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁን መነሳት ከሚጠይቅ በስተቀር የዘሩትን ለመስጠት ምቹና ተስማሚ ነው፡፡ የሚጎድለውና የሚያሳስበው ተቃዋሚዎች ምን ይዘዋል የሚለው ነው፡፡ የነፃነትና የዴሞክራሲ ውድ መፈክር ያነገቡ ወገኖች እጃቸው ከምን?

  ተቃዋሚዎች ከጥንቱ፣ ከቆየውና ከትኩሱ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ድክመት ተምረው የአዲስ አካሄድ ጥንስስ የመሆን አደራ ሊሸከሙ ተዘጋጅተዋል? ኢሕአዴግን እንደ ምንም ብሎ ከመጣል ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ከመድረስ ማዕዘን የወቅቱን አገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ የትግል ሥልትና ስትራቴጂ፣ እንደሁም ድርድርና የውይይት ሐሳብ ይዘው ለመንቀሳቀስ ከተዘጋጀ ጅምር ተነስተዋል?

  ኢሕአዴግስ? ኢሕአዴግ ሕዝብ መረጠኝ ባለ ማግሥት የተቀጣጠለ ትግል አስገድዶት በጥልቀት መታደስ ውስጥ ገብቻለሁ ብሏል፡፡ ዕውን ኢሕአዴግ በጥልቀት የመታደስ ዴሞክራሲውን የማጥለቅ ፍላጎት አለው ወይ?

  ኢሕአዴግ አሁንም የዴሞክራሲን መሠረት በአግባቡ የማንጠፍ ፍላጎት ያለው መሆኑ በትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የወደቀ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የትንታኔ መጽሔት በሆነው አዲስ ራዕይ (ከመስከረም እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም.፣ 11ኛ ዓመት፣ ቅጽ 5፣ ቁጥር 6) ላይ በምናገኘው “እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄያችን አስፈላጊነት፣ ይዘትና ፋይዳ” የሚል ዓብይ ጽሑፍ ላይ ተመርኩዘን ስለኢሕአዴግ ፍላጎት ለመረዳት እንሞክር፡፡

   በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ፓርቲው በሳይንሳዊ ትንታኔ የሚሠራ ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት የተነገረንና “ኅብረተሰብ በማያቋርጥ ሁኔታ ወደፊት ማደግና መሻሻል ያለበት መሆኑ” የኅብረተሰብ አንዱ ሕግ ተደርጎ መቀመጡ (ገጽ 256)፣ ሲጋጭብን ምን ጉድ እየተወራ ነው? ልንል እንችል ይሆናል፡፡ ግን በዚያው ገጽ ላይ ስለኅብረተሰብ ሌላ ሕግ ሲወሳ ወደፊት ስለመራመድና ወደኋላ ስለ መመለስ መጠቀሱን ይዘንና ለዓለማችን ብርቅ ያልሆኑትን የኋሊት መሄድንና ባሉበት መርገጥን አስበን፣ ስህተቱን ከጥንቃቄ ጉድለት የተፈጠረ አድርገን ብንገምት አግባብ ይሆናል፡፡

  “የመበስበስ አደጋን ማስወገድ” በሚል ሽፋን ከ1993 እስከ 1994 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ውስጥ የተካሄደው “የተሃድሶ” ክንዋኔ ውስጠ ሚስጥር የተፈነቀለ አንጃን አሻራ የማፅዳት ጉዳይ እንደ ነበር ስለሚታወቅ፣ የዚያን ጊዜውና የአሁኑ ምን አገናኝቶት የሚል ክርክር ውስጥም አንገባም፡፡ በዚሁ ጽሑፍ ውስጥ የሠፈረውን የኢሕአዴግ ሹሞች ሥልጣንን መጠቃቀሚያ ወደ ማድረግ መንሸራተታቸውና አለመንሸራተታቸው፣ ከአርሶ አደሩ ትግል መጠንከርና መቀዛቀዝ ጋር የተያያዘበትን (ማለትም ግስጋሴ የሚያመናምነው ጥንታዊ መደብ “የተራማጅ” ፓርቲና መንግሥት አመራር ጥራት ጠባቂ የሆነበትን) ወፈፌ ንድፈ ሐሳብ ስናነብ፣ ወረድ ብሎም የዝቅጠት አጀማመርን በማሳየት ስም የሠፈረው “ድርጅታችን የአርሶ አደሩ ጥያቄዎች የነበሩትን የዴሞክራሲና የብሔር እኩልነት፣ ራስ በራስ የማስተዳደርና የምርት ነፃ ተጠቃሚነት መብቶችን በማረጋገጡ የአርሶ አደሩ ትግል ስለተቀዛቀዘ …. የታየ ዝንባሌ ነበር” የሚል ሐሳብ (ገጽ 10 እስከ 11) ስንመረምር ዋናው ጉዳይ እውነትን ከሚያሳይ ሳይንሳዊ ትንታኔ ይልቅ የድጋፍ መሠረቴ የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍል የአንተ መንግሥት ነኝ ብሎ የመሸንገል ጉዳይ እንደሆነ ይገባናል፡፡ በአያሌው የትምህርት ቀመስነትና የከበርቴያዊ ዕድገት ቀመስነት ጥያቄዎች የሆኑት የዴሞክራሲ፣ የብሔር እኩልነትና የራስ በራስ አስተዳደር ጉዳዮች ከምርት ነፃ ተጠቃሚነት ጋር እኩል የአርሶ አደር ጉዳዮች ተደርገው በተጠቀሰው ዓረፍተ ነገር ውስጥ መደርደራቸውን፣ እንዲሁም ዴሞክራሲና ሌሎች መብቶቹ አርሶ አደሩ ተረጋግጠውለት ከትግል ስለመቦዘኑ መወራቱንም ልብ ይሏል፡፡

  የኢትዮጵያን መንግሥታዊ አውታራት ከኢሕአዴግ መለየት እስኪሳን ድረስ የተንሰራፋው የአንድ ፓርቲ አገዛዝ የፈጠረው አስመራሪነት በኢሕአዴግ አዕምሮ ምን ያህል አተረጓጎሙ ሊቀየር እንደሚችልም፣ ከመስከረም 2008 ዓ.ም. እስከ 2009 ዓ.ም.  የቆየው የሕዝብ ቁጣ ከመጣበት በኋላ ኢሕአዴግ ለቀየሰው ዳግም ተሃድሶ ምክንያት ብሎ ያስቀመጣቸው ነገሮች ቁልጭ አድርገው ያሳዩናል፡፡ አንደኛው የዳግም ተሃድሶ ምክንያት የተባለው የመጀመሪያው ተሃድሶ አዳዲስ ውጤት ማስከተሉ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ “ከአርሶ አደር ምርታማነት መጨመር ጋር ተያይዞ ለተጨማሪ የሥራ ሥምሪት ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው የሕዝብ ፍልሰት” እጅግ መጨመር ተቀምጧል (ገጽ 14)፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ፣ ለግብርና የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ቁጥር ቀንሶ አላስፈላጊ የሚያደርግ በመስመር መዝራትን፣ አጨዳን፣ ውቂያን፣ ምርትና ግርድ መለየትን በጥቂት ሰው መከናወን ያስቻለ ምን ቴክኖሎጂ ተዛምቶ ይሆን ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ ሌላው የተሃድሶው አዲስ ውጤት የተባለው ደግሞ የሕዝቡን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ መንግሥትን የመቆጣጠርና ኪራይ ሰብሳቢነትን የመታገል ንቃት ማሳደጉ ነው (ገጽ 13 እስከ 15)፡፡ በዚህ ሐሳብ መሠረት፣ ከቅርብ ጊዜ በፊት የታየው ብዙ ጥያቄና ብሶት ያዘለ የሕዝብ ቁጣ ሁሉ የተሃድሶው ፍሬ መሆኑ ነው፡፡

  ዳግም ህዳሴን አስፈላጊ ያደረገ ምክንያት ተብሎ በሁለተኛ ደረጃ ወደ ተቀመጠው የመንግሥትን ሥልጣን ለግል መበልፀጊያ የማዋል ችግር ስንመጣ ይበልጥ ወደ እውነት ብንጠጋም፣ ችግሩ መፈታተን ያመጣው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ተደርጎ ነው የቀረበው (ገጽ 15)፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ አንስቶ የፖለቲካ ችግሮችን በድቆሳ ማስተናገድ አንዱ ዘይቤው ሆኖ ሳለ፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ የተመለከትናቸው ኃይልን የተመረኮዙ የችግር አፈታት ጥረቶች” ማለቱም (ገጽ 23) ያው ራስን እንደ ገዢ የማዳን እብለት ነው፡፡ “የተሟላ ዴሞክራሲን ለማስፈን ጥረት ተደርጓል” (ገጽ 9) ከመባሉ ጋር አብሮ፣ ሕገ መንግሥቱ በ1986 ዓ.ም. 18 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ዜጎች የተወያዩበት ስለመሆኑ መጠቀሱ፣ ከቀድሞው የሕዝብ ውይይት እየተቀነጫጨበ ከቅርብ ጊዜ በፊት በተከታታይ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መቅረቡም፣ ሕገ መንግሥቱን ሕዝቡ ቢያንስ በወቅቱ ሻል ያለ ሊሆን በሚችለው በቀጥተኛ ድምፁ ሊያፀድቀው ሲገባ በወኪል ምርጫ ስም ኢሕአዴግና ደጋፊዎቹ አፅዳቂነቱን የተቆጣጠሩበትን ሥውር የድርጅታዊ ሥራ ገመና ለመሸፈንና ያንን ወቅት ያልደረሰበትን የቅርብ ትውልድ ለማቄል ሲባል ነው (ያኔ ሕዝቡ በደንብ አብላልቶ በ2/3 ድምፁ የራሱ አድርጎት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ባንዲራና ሕገ መንግሥቱን የኢሕአዴግ ባይ ተቃውሞ ባልተከሰተ ነበር)፡፡

  ያም ሆነ ይህ እነዚህን የመሳሰሉትን ነገሮች መጠቃቀሳችን ገመናን ለመሸፈንና ለፕሮፓጋንዳ እንደሚሆን አድርጎ እውነታን መተርጎም ለኢሕአዴግ የተለመደ መሆኑ እንዲጤን በማለት ነው

  አዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ የሠፈረውና የዳግም ተሃድሶው ፍኖተ ካርታ ነው ተብሎ የቀረበው ጽሑፍም ሆነ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከየካቲት 27 እስከ 28 (2009 ዓ.ም.) መደበኛ ስብሰባ መግለጫ ምንም አበረታች ዜና አልነገሩንም፡፡ ‹‹በተሃድሶው አገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም ያስገደዳትን አስከፊ ሁኔታ በመቀልበስ የተጀመረውን አገራዊ የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል መግባባት እንደተፈጠረም ኮሚቴው ገምግሟል›› ተብለናል፡፡ ይኼ ግን ምን ማለት ነው? የተቀለበሰው አስከፊ ሁኔታ ምንድን ነው? መስቀለኛው መንገድ ላይ (ትርጉም ወሳኝ ዕርምጃ የሚወስድበት ቀውጢ ሰዓት) ምን ወሰንን? የሕግ ተጠያቂነት በሌለበት በግምገማና ሰው በማለዋወጥ መላ የተልከሰከሰው የኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› የገዢውን ፓርቲ የሥር የመሠረት ችግር ወይም አደጋ (Original Sin) አዙሮ መመልከት አልቻለም፡፡

  የኢሕአዴግ ትልቁና የሥር የመሠረት ስህተቱና ኃጥያቱ ከበረሃ እንደመጣ በዚያው መቀጠሉ፣ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ኃይልነትና ተፎካካሪነት መለወጥ አለመቻሉ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብ ጨዋነትና ምግባር አለመያዙና አያስፈልገኝም ማለቱ ነው፡፡ ሥልጣን እንደያዘ ሰላማዊ የሐሳብ ትግል ጭምር ከተቀናቃኞች ጋር ማካሄድ ያለበት መሆኑን ዘንግቶ፣ እንዲያውም ፍርጃ አድርጎ ያለ ተቃዋሚ ሥራውን ማካሄድ አለመቻሉን በእሱ ላይ የተቀሰረ ልዩ ሴራና ተንኮል አድርጎ ወሰደ፡፡ በጠላትነት ፍረጃ ሕጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞን የማጥፋት ዘመቻም አወጀ፡፡

  ዛሬም ድረስ ጥርት ፍንተው ብሎ ያልወጣው የተቃዋሚነት ሚና ጭራቅ ሆኖ የተሳለው፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ቋንቋ ውስጥ እንዲወጣ በሌላ ቃል እንዲለወጥ መምከር ድረስ እያማረበት የመጣው ከዚህ ድኩም የኢሕአዴግ ያልተቀደሰ ጅምር አያያዝና እርግማን ምክንያት ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በፖለቲካው ሒደት ውስጥ ልክ እንደሱ እንደ ኢሕአዴግ የተነሱበትና የሚነሱበት ምክንያትና ሥፍራ እንዳላቸው በበጎ ዓይን ማየት አልቻለም፡፡ ከደርግ መውደቅ በኋላ የሚሰናዳውና የሚደላደለው መድረክ ለፍላጎቶቻቸውና ለዓላማዎቻቸው ዓርማ አበጅተው፣ የፖለቲካ ቀለም ቀብተውና ስም ሰጥተው ተከታዮቻቸውን አዝምተው የሚወዳደሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆኑን ኢሕአዴግ ከልቡ አላመነም፡፡

  ኢሕአዴግን ጨምሮ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በሕዝብ ፊት ታማኝነት አግኝቶ ተወዳጅነት አበጅቶ ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር የሥልጣን ባላደራ ሆኖ እንዲወጣ የሚንቀሳቀስበት፣ የሚራወጥበትና የሚፋለምበት የትግል መድረክ ቢሆንም ዴሞክራሲው በመሸበቡና ምኅዳሩ በመጥበቡ ብቻውን ሯጭ ብቻውን ቀዳሚ ኢሕአዴግ ሆኖ ቀረ፡፡

  በዚህ ላይ ኢሕአዴግ የተቃዋሚዎች ትግል በሰላማዊ የትግል ክልል እንዲቆይና በዚያው ውስጥ ብቻ እንዲገታ የሚያደርግ አያያዝ ከመከተል ይልቅ፣ በርካታ የማይጠገን ጉዳት ያደረሱ አፍራሽ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ክፉ አርዓያም ሆኗል፡፡ ዛሬ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ክፉ ባህርይ የሆነውን ዋናው ነገርና ችግር ሥልጣን መያዝ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሥልጣንን ይዞ ማቆየት ቀላል ነው፡፡ ትምህርቱ የተገኘው ከኢሕአዴግ ነው፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ኢሕአዴግ ከሕገወጡ ይልቅ ሕጋዊውን መንገድ ይበልጥ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ ፖለቲካ ማልማት ባለመቻሉ፣ በሕጋዊነት መቀጠል ወይም ወደ ሕገወጥነት መዞር እያለ ‹የጫካን መንገድ› በሚያመላክት ፕሮፓጋንዳ እየቀሰቀሰና በ‹‹ሕግ ማስከበር›› ዕርምጃ እያስፈራራ፣ ተቃዋሚዎች ተመርረው ወደ ስደትና ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደተገላገላቸው መቁጠርን ፖሊሲው አድርጎ በመያዙ የደረሰው ችግርና ጉዳት በቀላሉና በለበጣ የሚጠገን አይደለም፡፡

  የውስጥ ተቃውሞን ማድከም ለኢሕአዴግ ጥንካሬ አልሆነውም፡፡ የውስጥ ተቃውሞን አስደንግጦ ወደ ውጭ እንዲፈረጥጡ ማድረግ መገላገል እንዳልሆነ ሁሉ፣ ተቃውሞን ማፈንና የመንግሥት ዋናው ሥራ ማድረግም አደጋ ነው፡፡ ተቃውሞ ውስጥ ለውስጥ እየተገነባ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡ ተደጋግሞ እንደታየው በሰላም ሊፈታ ያልቻለ የውስጥ ተቃውሞ ከጎረቤት ባለጋራነት ጋር ይሸራረባል፡፡ ለውጭ ጠላት ይመቻል፡፡ በአጠቃላይ የ2008 እና የ2009 ዓ.ም. ተቃውሞ ያስተማረን በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት የደረሰው መከራ የመከረን ተነጋግሮና ተደማምጦ መፍትሔ የመሻት ሥልጡንነት አልፈጠረባችሁም ብሎ ነው፡፡ አገራችሁን የሚያጠፋው መተንፈሻና መመለሻ ያለው ቅሬታ ሳይሆን ታምቆ የኖረ ብሶት ነው እያለ ነው፡፡

  ኢሕአዴግ ‹‹አገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ አንድትቆም ያስገደዳትን አስከፊ ሁኔታ›› ስለመቀልበስ ከመናገሩ በፊት፣ የሚሉትን ለመስማት ሙሉ ‹‹የጤና ምርመራ›› ማድረግ አለበት፡፡

  ኢሕዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለቱም በየጎራቸውና እንደ አቅማቸው፣ እንደራረስም ማለታቸውን ትተው ቅድመ ሁኔታዎቻቸውን አራግፈው ውይይትና ድርድር (ወይስ ድርድር ብቻ?) ውስጥ መግባታቸውን ሰምተናል፡፡

  ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ይኼ ድርድር/ውይይት ከሁሉም በፊት የጠላትነት ፖለቲካን መናድ አለበት፡፡ ይኼን ለማድረግ ከሕገ መንግሥቱ በላይ ማዕቀፍ አያስፈልግም፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታ ዴሞክራሲን የማጥለቅም ሆነ ከዴሞክራሲ ጎን ቆሞ የመታገል ጉዳይ ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተደነገጉት መብቶችና ነፃነቶች ሕይወት እንዲያገኙ፣ ከየትኛውም ፓርቲ የቁርጠኝነት መሀላም ሆነ መልካም ፈቃድ ውጪ ህልውና ያላቸው እንዲሆኑ መታገል ነው፡፡  

  የሕዝብን ድጋፍ የማግኘት ሚስጥሩ ቀላል ነው፣ ከላይ ደጋግመን ገልጸነዋል፡፡ ከሕግ በላይ ለመሆን በማያመች ለውጥ ውስጥ ገብቶ የሕገ መንግሥቱን መብቶችና ኃላፊነቶች በገሐዱ ዓለም ውስጥ የሚዳሰሱ (ከኢሕአዴግ የቁርጠኝነት መሀላ ውጪ የሚኖሩ) ማድረግ፣ የማይዋሽ መንግሥት በዓለማችን የሌለ ቢሆንም ሕዝብን ማፈርንና ማክበርን፣ አፍና ተግባርን ማቀራረብን፣ በአስተዳደር ውስጥ ባህል ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img