‹‹ቆሼ›› ተብሎ በሚጠራው የከተማው ግዙፍ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ የደረሰው አደጋ ከአንድ መቶ በላይ ወገኖቻችንን አሳጥቶናል፡፡ ብዙዎችንም ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ዳርጓል፡፡ ከሃምሳ ዓመታት በላይ የአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻ የሚከመርበት ይኼ ሥፍራ አንድ የሚያስታውሰኝ ጉዳይ አለ፡፡ የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ ለሥራ ጉዳይ እዚያ እሄዳለሁ፡፡ ከዚህ በፊት በአካል ዓይቼ ስለማላውቀው በቆሻሻው ብዛት በጣም እገረማለሁ፡፡ በወቅቱ እኔ በደረስኩበት ቦታ በኩል በግምት 30 ያህል ሰዎች የተደፋውን ቆሻሻ እያገላበጡ የተለያዩ ዓይነት ዕቃዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ የንግድ ቤቶችና ከመሳሰሉት የተሰባሰበው የቆሻሻ ክምር ውስጥ የሚጠቅሙ የሚመስሏቸውን ነገሮች የሚሰበስቡት ሰዎች በጣም ጎስቋላ፣ እጆቻቸው በጣም ከመቆሸሻቸው የተነሳ ቆዳቸው የተሰነጣጠቀና ጣቶቻቸው የተጎዱ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ የዕለት እንጀራቸውን የሚፈልጉት እነዚህ ወገኖች ከቆሻሻው ባልተናነሰ በጣም የቆሸሹ ናቸው፡፡
አብረውኝ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሁለት ወጣቶች ወደ ሰዎቹ ተጠግተው ሲያነጋግሯቸው ብዙዎቹ ታማሚ ይመስሉ ነበር፡፡ አንድ የሕክምና ሰው አብሮን ስለነበር እነዚህ ሰዎች በቆሻሻው ጠረንና በሚያመነጨው ለጤና ጠንቅ የሆነ መርዛማ ጋዝ ምክንያት ሊጎዱ እንደሚችሉም መናገሩ አይዘነጋኝም፡፡ በቆሻሻው ክምር ሥፍራ እንዳሁኑ በርካታ ቤቶች ባይኖሩም፣ ራቅ ራቅ ያሉ ደሳሳ መጠለያዎች ይታያሉ፡፡ በአካባቢው ኳስ ይጫወቱ የነበሩ ልጆችም እንዲሁ ቁሽሽ ያሉና ሁኔታቸው በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡ ብዙዎቹ በማያቋርጥ ሳልና አክታ ይሰቃዩ ነበር፡፡ ሁኔታው በጣም ልብን የሚነካ ነበር፡፡ ልጆቹን ስናነጋግራቸው ምግባቸውን የሚያገኙት ከሚጣለው ቆሻሻ ውስጥ ሲሆን፣ ጤና ጣቢያ ወይም ክሊኒክ ሄደው አያውቁም፡፡ ከቆሻሻው ክምር ውስጥ ውድቅዳቂ ነገሮችን የሚፈልጉትን ሰዎች ስለኑሮአቸው ስንጠይቃቸው በመገረም እርስ በርስ ይተያዩ ነበር፡፡ በኋላ የገባን ጥያቄአችን ቅንጦት እንደሆነባቸው ነው፡፡
ከቆሻሻ ውስጥ የዕለት እንጀራን መፈለግ በብዙ ታዳጊ አገሮች የተለመደ ሥራ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ህንድን ከመሰለች በቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ ባለች አገር ሚሊዮኖች እንጀራቸውን የሚፈልጉት ቆሻሻ ውስጥ ነው፡፡ ቆሻሻ ለጤናና ለአካባቢ እጅግ በጣም ጠንቅ ቢሆንም፣ ለአገር ዕድገት ለግለሰቦች ደግሞ ሲሳይ ነው፡፡ ነገር ግን የቆሻሻ ተራራ ተፈጥሮ ዝም ተብሎ ሲታይ ደግሞ አንድ ቀን መቅሰፍት ያመጣል፡፡ ይህም ሰሞኑን ታይቷል፡፡ እርግጥ ነው ከዚህ ክምር ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ኩባንያ ውል ገብቶ ግንባታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ የቆሼን የቆሻሻ ክምር በርካታ ኩባንያዎች ቢሰማሩበት ከኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ይጠቅማል፡፡
አንድ ጓደኛዬ እንደነገረኝ ቆሻሻ ከኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች የሚያግዙ ብሎኮችን ለማምረትና ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ግብዓት መሆን ይችላል፡፡ ሌላው የገረመኝ ግን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች በጣም ጠቃሚ ነው መባሉ ነው፡፡ ቆሻሻ ሚቴን የሚባል ጋዝ የሚያመነጭ በመሆኑ ይህ ጋዝ ለሲሚንቶ ምድጃ የኃይል ምንጭ ይሆናል፡፡ በአግባቡ ይህንን ጥቅም መረዳት ባለመቻሉ ብቻ የቆሼ ቆሻሻ እንደ ተራራ ተኮፍሶ ውስጥ ለውስጥ እየተብላላ ሲደረመስ የሰው ሕይወት ማጥፋቱ ያናድዳል፡፡ ወደፊት ደግሞ በዚህ ቆሻሻ ሳቢያ ውኃ ይበከላል፣ የወባ ትንኞች ይራባሉ፣ አየሩ የበለጠ ይበከላል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ቆሻሻ አገርና ሕዝብ ገዳይ እንዳይሆንና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ኢንቨስትመንት አማራጭ ማድረግ ሲገባቸው ለምን ዝም ይላሉ?
ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ለማስወገድና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዱ ምርጥ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ ልምድ ያለው ጓደኛዬ እንደነገረኝ በሀብታሞቹ አገሮች ያለው አሠራር ከወጪ አንፃር የማይሞከር ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ፣ ከፍተኛ የቴክኒክ ብቃትና ክህሎት የሚፈልግ፣ ከሙስና የፀዳ አሠራር የሚሻና ብርቱ ክትትልና ቁጥጥር የሚፈልግ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል አዋጭና ቀለል ባለ ዘዴ የሚመራ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በማኅበረሰቦች የሚደገፍ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ ማዘጋጀት፣ በቆሻሻው የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠሩ ኩባንያዎችን ወደ ሥራ ማስገባትና ለጤናና ለአካባቢ ጠንቅ ሊሆኑ የማይችሉ አሠራሮችን ማስፈን ጠቃሚ መሆኑን ጓደኛዬ በአፅንኦት አስረድቶኛል፡፡ ምንም እንኳ እንደሚወራው ቀላል ባይሆንም፣ ጥርስን ነክሶ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ የግድ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ቆሻሻን በአግባቡ መያዝና ማስወገድ ላይ ያለው ማኅበረሰባዊ ግንዛቤም መፈተሽ አለበት፡፡ በአንድ ወቅት ኮተቤ አዲስ የተሠራ የኮብልስቶን መንገድ ላይ እጓዛለሁ፡፡ ግራና ቀኝ የውኃ ማስወገጃ ቦይ ተገንብቶለታል፡፡ የሚያሳዝነው ግን የፍሳሽ ማስወገጃው በደረቅ ቆሻሻ ማለትም በጫት ገራባ፣ በፌስታሎች፣ በውኃ ፕላስቲኮች፣ ወዘተ ተሞልቷል፡፡ ግራና ቀኝ ደግሞ ንግድ ቤቶች (ምግብ ቤቶች፣ መደብሮች፣ ፀጉር ማስተካከያ፣. . .) ተደርድረዋል፡፡ እነዚህ የንግድ ቤቶችን የሚያስተዳድሩ ሰዎች ከአንድ ከተማ ውስጥ ከሚኖር ከተሜ የማይጠበቅ ድርጊት ሲፈጽሙ፣ አካባቢውን የሚያስተዳድረው ወረዳ ወይም ክፍለ ከተማ ዝም ማለቱ አያሳፍርም? በሌላ ጊዜ ግን ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ መውረጃ በማጣቱ ብቻ እነዚህ የንግድ ቤቶች ተጥለቅልቀው ከፍተኛ የንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየን ቸልተኝነት መዘዙ የከፋ መሆኑን ነው፡፡ ሰሞኑን በዜጎቻችን ላይ የደረሰው መቅሰፍትም የአጠቃላይ ችግራችን ማሳያ ይመስለኛል፡፡
(ቢንያም መርጊያ፣ ከአዲሱ ገበያ)