Thursday, May 30, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሊቢያ የሰው ልጆች የምድር ገሃነም

በዳዊት ከበደ አርአያ

ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ የሙአመር ጋዳፊ ሥርዓት እ.ኤ.አ በ2011 መውደቁን ተከትሎ፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት በማጣቷ ቅጥ ወደ አጣ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህ እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ የተፈጠረላቸው በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ድርጊት የተሰማሩት ቡድኖች ደግሞ፣ ብዙዎችን እያሰቃዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያፈሱባት ነው፡፡ ይህች በሜድትራንያን ባህር ጫፍ የምትገኝ አገር ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ጣሊያን በሕገወጥ መንገድ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች ተመራጭ ያደርጓታል፡፡ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችም በዚህች ማዕከላዊ መንግሥት በሌላት አገር ከምሥራቅና ከምዕራብ አፍሪካ የሚሄዱ ስደተኞችን እየተቀበሉ፣ የሰው ልጅ በገዛ አምሳያው ፍጡር ሊፈጽመው የማይገባ አስነዋሪ የጭካኔ ተግባር ይፈጽሙባቸዋል፡፡

በቅርቡ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ባወጣው ሪፖርት፣ በዓለም ላይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚታወቁት አካባቢዎች በስደተኞች ላይ ከሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ተግባራት 80 በመቶ፣ ከሱዳን እስከ ሊቢያ ባለው የሰሀራ ምድረ በዳ እንደሚፈጸም ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ስደተኞች ወዳሰቡበት ሳይደርሱ በሰሀራ ምድረ በዳና ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሜዲትራንያን ባህር በሚደረግ ጉዞ እንደሚሞቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ 2017 ዓ.ም ከገባ በኋላ ባሉት 53 ቀናት ብቻ 366 ስደተኞች ባህር ውስጥ እንደሞቱ፣ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችም ከምንጊዜውም በከፋ ሁኔታ ከፕላስቲክና ከእንጨት በተሠሩ ትንንሽ ጀልባዎች ከአቅም በላይ በመጫን በግድ የለሽነት ወደ ባህር እንደሚወረውሩዋቸው የድርጅቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የዛሬ ሁለት ሳምንት 120 ስደተኞችን ጭና ከሊቢያ የተነሳች አነስተኛ የፕላስቲክ ጀልባ በሜድትራንያን ባህር ሰጥማ ተሳፍረውባት የነበሩት ስደተኞች በሙሉ አልቀዋል፡፡ በወቅቱ የ87 ስደተኞች ሬሳ በሊቢያ የባህር ዳርቻ ተንሳፎ የተገኘ ሲሆን፣ የቀሪዎቹ አስከሬን እስከ አሁን ሊገኝ አለመቻሉን የተለያዩ የዓለማችን ትልልቅ መገናኛ ብዙኃን ዘግበውታል፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾችና መገናኛ ብዙኃን እንደሚገልጹት ከሆነ፣ እነዚህ ሕገወጥ ቡድኖች በዚያች አገር በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ያለምግብ፣ መፀዳጃና በቂ አየር እንኳን በማያገኙበት መጋዝን አሽገው ቁም ስቅላቸውን ያሳዩዋቸዋል፡፡ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች አያያዝን በተመለከተ ለመዘገብ ወደ ሥፍራው የተጓዘ ቫይስ ኒውስ የተባለ የሚድያ ተቋም ጋዜጠኛ፣ ‹‹በሕይወቴ ከአየሁዋቸው እጅግ በጣም አስፈሪና አደገኛ ሥፍራ፣ መሬቱ፣ አየሩና ንፋሱ ሁሉ ሞት ሞት ይሸታል፤፡፡›› በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹በአካባቢው በምጓዝበት ወቅት በየሥፍራው የተጣሉ ሻንጣዎች፣ ጫማዎች፣ የሕፃናትና የጎልማሶች አልባሳት፣ እንዲሁም ሥጋቸው አልቆ አጥንት ብቻ የቀሩ አስከሬኖች ማየት ሌላው አስፈሪ ትዕይንት ነው፤›› በማለትም ምስክርነቱ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ከሁሉም በላይ እስካሁን ድረስ ከአዕምሮዬ ያልጠፋው በሰሀራ በረሃ ያየሁት የሁለት ሕፃናትና የአንዲት እናት አጥንት ብቻ የቀረው አስከሬን ነው፡፡ ይህች እናት በዚያ አደገኛ በረሃ ሁለት ልጆቿን ይዛ ስትጓዝ ነው ረዳት አጥታ ሁለት ልጆቿን እንደታቀፈች ወድቃ የቀረችው፡፡ በጣም ዘግናኝ ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡

‹‹ከሱዳን እስከ ሰሀራ ምድረ በዳና እስከ ሊቢያ ሜድትራንያን ባህር ጠረፍ የተበተኑት ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ርህራሔ ያልፈጠረባቸው የሰው ደም የጠማቸው፣ በሰው ልጅ ስቃይና ፍዳ እርካታ የሚሰማቸው የተለዩ ፍጡራን ናቸው፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹የሰው ልጅ በአካሉ ብቻ ሰው የሚባል ካልሆነ በስተቀር በመንፈሳቸውና በኅሊናቸው ግን ‘መልዓከ ሞት’ ናቸው ብል ይሻለኛል፤›› ሲልም ይገልጻል ጋዜጠኛው፡፡

ወደ እንደዚህ ዓይነቱ የመቅሰፍት ምድር ነው እንግዲህ ብዙዎች የአፍሪካ ወጣቶች ወደ አውሮፓ ለመሻገር በየቀኑ ሳይሆን በየሰዓቱ የሚጓዙት፡፡ ብዙዎቹ ግን ያሰቡትን ሳያገኙ አስፈሪው በረሃ በልቷቸዋል፡፡

ዓምደ ማርያም በርሃ ይባላል የ34 ዓመት ጎልማሳ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሊቢያ እስር ቤት ውስጥ ከአንድ ወር በላይ ግፍና መከራው አሰቃይቶት የ60 ዓመት አዛውንት መስሏል፡፡ እሱ እንደሚለው ከሆነ ከሱዳን ካርቱም ውስጥ በሾፌርነት ተቀጥሮ በሚሠራበት ወቅት አንድ ሱዳናዊ ጓደኛው ሊቢያ ቢሄድ በቀላሉ ወደ አውሮፓ እንደሚሻገርና የተሻለ ገቢ እንደሚያገኝ ከነገረው በኋላ፣ ከሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ጋር ያገናኘዋል፡፡ ከዚህ በፊት ያጠራቀመውንና ከቤተሰቡ ተበድሮ አምስት ሺሕ ዶላር ከከፈላቸው ጣሊያን እንደሚያደርሱት ተናግረው ጉዞ ወደ ሊቢያ ይጀምራል፡፡ ሊቢያ እስኪደርስ በሰሀራ በረሃ ያጋጠመው የስቃይና የሞት ትዕይንት ግን ከሚገልጸው በላይ ነው፡፡ ሲያስታውሰው ያንቀጠቅጠዋል፡፡

‹‹በምድረ በዳው ሽፍቶች ወይም ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ብቻ አይደለም የሚሰቃዩህ፡፡ የመንግሥት ድንበር ጠባቂ ወታደሮችና ፖሊሶችም ጭምር ናቸው፤›› የሚለው ዓምደ ማርያም፣ ‹‹ይህን ሁሉ ስቃይና መከራ ከማየት መሞት ብትፈልግ እንኳን እነሱ የተለያዩ እገዛ አድርገው ከሞት አፋፍ አውጥተው ዳግም ያሰቃዩሃል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹በሰው ልጅ ስቃይ ደስታና እርካታ የሚሰማው ፍጡር ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም፤›› የሚለው ዓምደ ማርያም፣ ‹‹ሚስት ባሏ እግሩና እጆቹ ታስሮ ዓይኑ እያየ ለሁለትና ለሦስት እየተፈራረቁ ሲደፍሯት፣ እርጉዝ ሴት አምጣ አሸዋ ላይ ደሟ ሲፈስና ስትወልድ እያዩ ምንም ዓይነት ርህራሔ አይሰማቸውም፤›› ብሏል፡፡

በቅርቡ የወጣ አንድ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ ሴቶች እርጉዝ ሆነው ከቤታቸው እንደማይሰደዱ ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች በየቦታው ከሚደፍሩዋቸው ሽፍቶችና ደላሎች ነው የሚያረግዙት፡፡ ለዚህም ነው እነዚህ ደላሎች የ13 ዓመት ሕፃናት ሴቶችን ሳይቀር ገና ከአገራቸው ከመውጣታቸው በፊት በጉዞው እንደሚደፈሩ ስለሚያውቁ፣ የእርግዝና መከላከያ እንደሚሰጥዋቸው የተረጋገጠው፡፡

በቅርቡ በዚህ በርሃ አልፈው በጣሊያንዋ ላምፔዱዛ ደሴት የደረሱት በዚሁ የዕድሜ ክልል የሚገኙት ሕፃናት ሴቶች ላይ በተደረገው የማህፀን ምርመራ እንደተረጋገጠው፣ በጨቅላ ዕድሜያቸው የእርግዝና መከላከያ መድኃኒት እንደተሰጣቸው ነው፡፡ በደሴቷ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር የሚሠሩት ዶ/ር ሔለን ሮድሪጌዝ፣ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የእርግዝና መከላከያ መስጠት በጣም አደገኛና ያለ ዕድሜቸው የወር አበባቸው እንዲቆምና ልጅ መውለድ እንዳይችሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሔለን ምርመራ ካደረጉላቸው ሴቶች አምስቱ ለዚህ ችግር እንደተጋለጡና ያለዕድሜያቸው የመውለድ ተፈጥራዊ ፀጋቸው እንደተነጠቁ አረጋግጠዋል፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በሕገወጥ መንገድ በደላሎች ውሸትና የማይጨበጥ ተስፋ ተታለው ከአገራቸው የሚሰደዱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በጉዟቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ፈተናና ስቃይ በዚህ ጽሑፍ ለመግለጽ ይከብዳል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ የሰሀራ በረሃ አደገኛ ጉዞ ጨርሰው በዕድል ተርፈው ሊቢያ ሲደርሱ የሚያጋጥማቸው ደግሞ ከድጡ ወደ ማጡ ነው፡፡ ሌሎች ሰው በላ አውሬዎች ይቀበሉዋቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ስደተኞች ሙቀቱ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሚደርስ ምድረ በዳ ከቆርቆሮ በተሠሩ እስር ቤቶች ታጉረው የድረሱልን ጥሪ ያሰማሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው ይቆጠራል፡፡ የቁም አስከሬን መስለዋል፡፡ ገሚሶቹ በተኙበት የሞት ጣር ያሰማሉ፡፡ ያረገዙ ሴቶች ያለ ረዳት ወለል ላይ በተነጠፈ ሰሌን ወድቀው ያለቀናቸው በምጥ ይሰቃያሉ፡፡ አንድ ከጋምቢያ የመጣ ስደተኛ መፀዳጃ ቤት እንደማያውቁ፣ ሽንታቸውንና ዓይነ ምድራቸውን በተኙበት እንደሚያመልጣቸው ሲናገር ለማመን ይከብዳል፡፡ ‹‹የምድር ገሃነም ውስጥ ነው ያለነው፤›› ሲል ለጋዜጠኛው መልሶለታል፡፡ ለዚህ ነው የጽሑፌን ርዕስ ከዚህ ስደተኛ አባባል የተዋስኩት፡፡ ጋዜጠኛው ይቀጥላል፡፡

…… እስር ቤቱ ውስጥ ሕፃናት አቅፈው ፍዝዝ ብለው እንባቸውን እንደ ዝናብ የሚያፈሱ ኢትዮጵውያን ሴቶች በማውቀው የአገሬ ቋንቋ በአማርኛ፣ ‹‹እባካችሁ ከዚህ ጉድ አውጡን፤›› ስትል ትማፀናለች፡፡ ሰውነቴ ራደ፡፡ እኔም እምባዬን ቪዲዮው ውስጥ ከማያት የአገሬ ልጅ ጋር ለቀቅኩት፡፡ ምንም እንኳን አቅም ኖሮኝ ደርሼ ካለችበት የመከራና የስቃይ ሕይወት ባላወጣትም ብዕሬን ላንሳና ልናገርላት፣ እሷን ማዳን ባልችልም ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤው ሳይኖራቸው በደላሎችና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለው ለመጓዝ እየተደራደሩ ያሉትን የአገሬ ልጆች ስለጉዞው አደገኛነትና ዘግናኝነት ለመግለጽ እየሞከርኩኝ ነው፡፡ አዎ እየሞከርኩኝ ነው ብል ይሻላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሉበት ዘግናኝ ሕይወት በጽሑፍና በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል፡፡ የቱን ጽፈን የቱን እንደምተው ግራ ያጋባል፡፡

እዚህ ላይ ግን አንድ ሳልገጸው ማለፍ የማልፈልገው ጉዳይ የአገራችን ሚዲያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ሥራ አለመሥራታቸው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የትኛውም በዓለማችን ያሉ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት ከቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸው እስከ ድረ ገጻቸው በዚህ ጉዳይ ይዘግባሉ፣ መረጃ ያሠራጫሉ፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ሚዲያዎች ለአውሮፓ የእግር ኳስ የሚሰጡትን የአየር ሰዓት እንኳን ለዚህ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እያጠፋ ያለውን ሕገወጥ ስደትን አንድ አሥረኛው ጊዜ ሊሰጡት አለመፈለጋቸው ያሳዝናል፡፡ በእውነት አገራችን ውስጥ የሚዲያ የአየር ሰዓት በማይጠቅምና ምንም ዓይነት አገራዊ ፋይዳ በሌለው ጉዳይ ላይ ኅብረተሰቡን ማደንቆሩ በጣም ያሳዝናል፡፡

አገራችን ውስጥ የሚዲያ የአየር ሰዓት መጫወቻ ሆኗል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ እባካችሁ ሚዲያው፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ቢያንስ በችግር ውስጥ ያሉትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ማዳን እንኳን ባንችል፣ አሁንም ብዙ ወገኖቻችን በማይጨበጥ ባዶ ተስፋ እየተታለሉ ገንዘባቸውን አፍስሰው ሕይወታቸውን ለዚህ አደገኛ ጉዞ ለመገበር እየተንደረደሩ ነው፡፡ እውነታውን እንዲውቁትና የጉዞውን አደገኛነት እንዲገነዘቡት በማድረግ ረገድ በተለይ ሚዲያው ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅበታል ………… ቸር እንሰንብት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles