Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጎበዞች በሜዳቸው እንዳይሸነፉ

ጎበዞች በሜዳቸው እንዳይሸነፉ

ቀን:

ፈተና ሲቃረብ የተማሪዎች ሁሌም አብዝቶ መጨነቅ የተለየ ነገር አይደለም፡፡ እንዴት ላጥናና እንዴት አድርጌ ጥሩ ውጤት ላምጣ በሚለው ጉዳይ ላይም የተለያዩ ዕቅዶች ማውጣትም እንደዚሁ፡፡ ብዙዎች ጠንክረው በመሥራት እንደ ሐሳብና ዕቅዳቸው ውጤት ሲያስመዘግቡ ፈተናዎች ላይ ሲቀመጡ ፍርሃት ያለባቸው ተማሪዎችም አሉ፡፡

የስምንተኛ ክፍል ወይም የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች ውጤት የታወቀበትን ጊዜ ሲያስታውሱ ብዙዎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ብቻ ሳይሆን ውጤት ላይ ያልተሳካላቸውን ጐበዝ ተማሪዎችንም ያስታውሳሉ፡፡ በክፍል፣ በትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሚታወቁ ነገር ግን የስምንተኛ፣ የአሥር ወይም የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤታቸው በተቃራኒው መሆን ሁሌም ያስገርማል፡፡ ብዙ ጥያቄዎችን እንዲያነሱም የግድ ይላል፡፡

ለእንደዚህ ያሉ ተማሪዎች ውጤት ያልተጠበቀ መሆን በትምህርት ቤት ማኅበረሰብ፣ በጓደኛና በቤተሰብ ከሚቀመጡ መላምቶች ብዙ ጊዜ ቀዳሚ ሆኖ የሚሰማው ደንግጦ/ደንግጣ ነው የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል እመለስበታለሁ በሚል አንድ ጥያቄ ዘሎ በመሄድ ምክንያት ብዙ ጥያቄዎችን መሳሳት የሚለውም ይነሳል፡፡ እንደ ሁኔታውና እንደ ተማሪዎቹ የተለየ እውነታ የአጋጣሚዎቹ ትክክለኛ ምክንያት እንደሚለያይ አያጠራጥርም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጐበዝ ማን ነው? የሚል ጥያቄ ያነሱ ቢኖሩም የፈተና ፍርሃት ያለባቸው ተማሪዎች መኖራቸውን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች፣ መምህራንና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር የፈተና ፍርሃት ያለባቸው ተማሪዎች መኖራቸውን ያስረግጣሉ፡፡

አንድነት በለጠ (ስሙ ተቀይሯል) ከረዥም ዓመታት በፊት የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰደበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ ወደ አእምሮ ቀድሞ የሚመጣው ነገር ሁሌም አንድ ዓይነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህም በጣም ጐበዝ የሚለው ጓደኛው ፈተና በሚጀመርበት ዕለት ከባድ ፍርሃት ውስጥ ገብቶ መፈተን አለመቻሉ ነው፡፡ አንድነት አራት ነጥብ አምጥቶ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ያ ጓደኛው በዚያ ዓመት በድጋሚ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ ነገር ግን ያኔም ውጤት አልተሳካለትም፡፡ ‹‹ራሴን ከእሱ ጋር አላወዳድርም እሱ በጣም ጐበዝ ልጅ ነበር፡፡ አሥራ አንደኛ ክፍል ሆነን የኮሌጅ ፊዚክስ መጽሐፍ ያጠና የነበረ ተማሪ ነው›› በማለት ጓደኛው ምን ያህል ጐበዝ እንደነበር ለማስረዳት ይሞክራል፡፡

ጐበዞች ሆነው ምናልባትም አቅማቸውና ያደረጉት የፈተና ዝግጅት ከቀረበላቸው ፈተና በላይ የሆነ ተማሪዎች በድንጋጤ ውጤት የማያመጡበት አጋጣሚ ቢኖርም በራስ መተማመንና በመረጋጋት ያሰቡትን ውጤት የሚያመጡ ጐበዝ ተማሪዎችም በርካታ ናቸው፡፡ በራስ መተማመንና መረጋጋታቸው ረድቷቸው ተመሳሳይ ውጤት የሚያመጡ መካከለኛ የሚባሉ ተማሪዎች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡

በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት የሚጠየቁ እንደ ‹‹IELTS›› (International English Language Testing System) እንዲሁም GRE (Graduate Record Exam) ያሉ ፈተናዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ፈተናዎች ለወሰደው አንድነት ፈተና ላይ እንዴት ነህ? የሚል ጥያቄ አቅርበንለት ነበር፡፡ ፈተና ከመድረሱ በፊት ፈተናን ሲያስብ ፍርሃት ፍርሃት እንደሚለው ይናገራል፡፡ ቢሆንም ግን እንዲሁ ሁሉንም ሳይሆን ለፈተና ያስፈልገኛል የሚላቸውን ነገሮች በደንብ አጥንቶ በመዘጋጀት ተረጋግቶ እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ ደግሞ ፈተናዎች ላይ የሚመጡ ጥያቄዎች በደንብ ለተዘጋጀ ሰው የሚገመቱና የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ IELTS ለተዘጋጀ ሰው ጥያቄዎቹ ቀድሞ መገመት የሚቻልና ግልጽ ነው›› የሚለው አንድነት አሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 4.00፣ IELTS 7.5 ማምጣት ችሏል፡፡ በሕይወቴ በጣም ከበደኝ ባለው የGRE ፈተና ያመጣውን ውጤት ግን አያስታውስም፡፡ እሱ እንደሚያምነው ብዙ ጊዜ ፈተናን የመፍራት ነገር ቢኖርም የፈተና ጥያቄዎች ለተዘጋጀ ጐበዝ ተማሪ ‹‹ያን ያህል መልፋት ሁሉ አያስፈልገኝም ነበር›› የሚያስብሉ ናቸው፡፡

የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በየዓመቱ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ በርካታ ውጤት ይመርመርልኝ ጥያቄዎችን ያስተናግዳል፡፡ ተገቢነት አላቸው የሚላቸው ጥያቄዎችን በመቀበል ሲያስተናግድ አብዛኛውን ጊዜ ተማሪዎች የሚጠይቁት ፈተናቸው አንድ በአንድ እንደ አዲስ እንዲታረም በመሆኑ የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ማስተናገድ ከባድ መሆኑን አቶ አርአያ ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡ ውጤት ይመርመርልኝ ጥያቄዎቹ በአጠቃላይ የጐበዝ ተማሪዎች ናቸው ብሎ መደምደም ባይቻልም ጥቂት የማይባሉት የጐበዝ ተማሪዎች እንደሚሆኑ መገመት ስህተት ላይሆን ይችላል፡፡

ከጥናትና ከፈተና ጋር በተገናኘ አመለካከት ወሳኝ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአጠናን ዘዬ እንዲሁም ፈተና ላይ የሚኖር የሥነ ልቦና ሁኔታ ላይ ተጽእኖ ያሳድራልና፡፡ ጥናትና ፈተናን ከባድና አሰልቺ አድርጐ ማሰብ አሉታዊ ተጽእኖ ሲኖረው ጥናትና ፈተናን ቀለል አድርጐ መመልከት ውጤቱ መልካም እንደሚሆን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለጥናት የሚገባውን ትኩረት መስጠትና መውደድ እንዲሁም ሁሌም እችለዋለሁ የሚል ሥነ ልቦና ማዳበር ለውጤት ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነም ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል በፈተና ወቅት ውጥረት የተለመደ ቢሆንም ጊዜን በአግባቡ ተጠቅሞ ቀድሞ መዘጋጀት ትክክለኛው መፍትሔ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመጨረሻ ሰዓት የሚደረግ ጥናት ከባድ ጫና ስለሚያሳድር ሁሌም ጊዜን በአግባቡ ተጠቅሞ መሸፈን ያለባቸውን ርዕሶች ቀድሞ መመልከት የምርጫ ጉዳይም ብቻ ሳይሆን የግድም ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በባከነ ሰዓት ሁሉንም ላንብብ ላስታውስ ቢባል የሚቻል አይሆንም፡፡ እንዲህ ባለው አጋጣሚ አእምሮም በድካም ቀጥ ሊል እንደሚችል ሳይኮ ቴራፒስቷ ወ/ሮ ናርዶስ ማሞ ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ይህን ያህል ጐበዝ ተማሪዎች ፈተና በመፍራት ውጤት ሳያመጡ ይቀራሉ ለማለት ጥናት ቢያስፈልግም ግን ጐበዝና ከጓደኞቻቸው በላይ አቅም እያላቸው በፈተና የሚገባቸውን ውጤት የማያመጡ እንዲያውም ፈተና ማለፍ የማይችሉ ተማሪዎች ያጋጥማሉ፡፡

‹‹የጥናታቸውን ያህል ውጤት የማያመጡ፣ ፈተና ላይ ትንፋሻቸው የሚቆራረጥ የሚያለቅሱ ተማሪዎች ሁሉ ያጋጥማሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች አንዳንዴ ሊከፉም ይችላሉ›› የሚሉት ወ/ሮ ናርዶስ እውቀት እያላቸውና ጥሩ ዝግጅት አድርገው ሳለ ፈተና ላይ ከላይ የተገለጹት ነገሮች ለሚያጋጥሟቸው ተማሪዎች እንዲህ መሆን የተለያዩ ነገሮችን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡

ይህንን ያህል ውጤት ማምጣት አለብኝ ይህ ካልሆነ የሕይወት ህልሜ አይሳካም ብሎ የማሰብ ነገር በብዙ ተማሪዎች አለ፡፡ በሌላ በኩል ይህን ውጤት ማምጣት አለብህ በመባል በቤተሰብ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ የሚገቡ ተማሪዎችም በርካታ ናቸው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጫና በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባለው ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ላይ ይበረታል፡፡ ‹‹ቤተሰብ እንዲህ እምነት ጥሎብኝ ተስፋም አድርጐ ውጤት ባይመጣልኝስ የሚለው ነገር ተማሪዎችን ይረብሻል፡፡ ቀደም ሲል ምንም እንኳ ብቃት ቢኖራቸውም በፈተና ያልተሳካላቸው አጋጣሚ መኖርም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡››

ምናልባትም የመጀመሪያ ጥያቄ ከባድ ሲሆን ደንግጦ በቃ አለቀልኝ ፈተናው ሊከብደኝ ነው የሚል ነገርን ማሰብ እንኳ የራሱ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ በተቃራኒው ሁለተኛውና ቀጥሎ ያሉት ቀላል ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ቅጽበታዊ አመለካከት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ከባድ ጥያቄ ላይ ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ ቀላልና የሚችሏቸው ጥያቄዎች ላይ ማተኮር ለተማሪዎች ይመከራል፡፡

ቀድሞ በአግባቡና በሚችሉት መጠን በመዘጋጀት ፋንታ በመጨረሻ ሰዓት ላይ ራስ ላይ ጫና ማብዛት ምንም እንኳ እውቀት ቢኖር የፈተና መመርያ በደንብ እንዳይረዱ አሳስቶ የመሙላት ነገር እንዲኖር ሊያደርግም ስለሚችል የዚህ ዓይነቱን ጫና ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የመጨረሻውን ቀን በቂ እንቅልፍ ማግኘት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በመጨረሻዎቹ ሰዓታት ላይ ይህ ሊመጣ ይችላል ያኛው ዓይነት ወሬም አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ይህ መረበሽን እንጂ የሚቀይረው ነገር አይኖርም›› ይላሉ ወ/ሮ ናርዶስ፡፡

የፈተና ውጤት የማጥናት ብቻም ሳይሆን የሌሎችም ነገሮች ድምር ውጤት በመሆኑ ስለመረጋጋት በራስ ስለመተማመን ከማጥናት እኩል ማሰብ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ፈተና ሁሌም ፈተና ነውና መደንገጥ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የብዙዎች አጋጣሚ ነው፡፡ ምናልባትም ጥያቄው ምን ያህሎች ከድንጋጤአቸው ሲመለሱ ምን ያህል ተደናግጠው ይቀጥላሉ የሚለው ይሆናል፡፡

ወ/ሮ ናርዶስ እንደሚሉት በፈተና ላይ ከከባድ ድንጋጤ በኋላም ተረጋግቶ መቀጠል ይቻላል፡፡ ለዚህ ይረዳል የሚሉት ሰላሳ ሰከንድ ወስዶ በደንብ መተንፈስን (Deep breathing technique) ነው፡፡ እጅ ላይ ጨመቅ ለቀቅ የምትደረግ ኳስ ዓይነት ነገር ይዞ ጡንቻን ዘና ማድረግም ከመሰል ድንጋጤ ወጥቶ ፈተናን በደንብ ለመሥራት ያስችላል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ቀላል ነገሮች ፈተና ላይ ተማሪዎችን ሊረብሹ እንደሚችሉ የሚናገሩት ወ/ሮ ናርዶስ ‹‹ሌላ ተማሪ ትርፍ ሊሰጣት ሲችል እርሳስ በመርሳቷ በጣም ተረብሻ ፈተና መሥራት ያቃታት በጣም ጐበዝ ተማሪን አስታውሳለሁ›› ይላሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱን ነገር ለማስቀረት ተማሪዎች ቀደም ባለው ቀን ፈተና ላይ ይዘው መገኘት ያለባቸውን ነገሮች ዝርዝር በማውጣት ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይጠቅማል፡፡

ተማሪዎች ፈተና ላይ ከሚኖራቸው ሥነልቦና ጋር በተያያዘ የቤተሰብ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ናርዶስ ቤተሰብ ይህን ልታመጡ ይገባል ይህን ውጤት እንጠብቃለን እያለ ልጆች ላይ ያልተገባ ጫና እንዳያሳድር ያሳስባሉ፡፡ ልጆች በአንድ ፈተና ውጤት ብቻም ሳይሆን በሌላ ጊዜና በሌላም መንገድ ህልማቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ማሳየት መቻል እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

የመጀመሪያ ልጃቸው ኮምፒውተር ሳይንስ ምሩቅ ነች፡፡ ሁለተኛው ልጃቸው ደግሞ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሚባለውን ውጤት (621 ነጥብ) በማምጣት አሁን በጥቁር አንበሳ ሕክምና በማጥናት ላይ ይገኛል፡፡ አሥራ አንደኛ ክፍል የሆነው ልጃቸው ደግሞ ባለፈው ዓመት በአሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 3.6 አምጥቷል፡፡ ልጆቻቸው እንዴት እንዲያጠኑና ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚረዷቸው ለአቶ ጌቱ ዓለማየሁ ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ ፈተና ሲደርስ ሳይሆን ሁሌም ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ ትኩረታቸው ትምህርት ላይ እንዲሆን እንደሚነግሯቸው ይገልጻሉ፡፡

‹‹የሚገባቸውን ሁሉ ስለሚያደርጉ ፈተና ላይ በራስ መተማመን፣ እንሠራዋለን የሚል ሥነ ልቦና እንዲኖራቸው ነው የማዘጋጃቸው›› የሚሉት አቶ ጌቱ በተቃራኒው ውጤት ባላመጣ የሚል የቤተሰብ ወቀሳና ነቀፋ ፍራቻን ይዘው ፈተና ላይ የሚቀመጡ ተማሪዎች ምንም እንኳ ጐበዝ ቢሆኑ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ቤተሰብ ስለልጆቹ ጉብዝናና ማምጣት አለባቸው ብሎ ስለሚያምነው ውጤት የሚነግራቸው ነገር፣ የሚሰጣቸው አስተያየትም በልክ መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...