Friday, May 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምንድነው ጭርታው? ምንድነው ድብርቱ?

ሰላም! ሰላም! ‹‹የዚህ ዓለም ደስታ ደካማ ነው›› ማን ነበር ያለው? አዎ፣ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥታችን ናቸው። ይኼውላችሁ ያ አብዮት ፍሬውንም ገለባውንም ጥሩ አድርጎ ከትውስታችን ገርስሶታል ማለት ነው። አለመታደል ሆነና ደግሞ ‘የእኛ ታሪክ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስንሠለፍ መታወስ የሚጀምር ነው’ የሚል አባዜ ይዞን፣ እንኳን ታሪካችን የባለታሪኮቹም ስም ይዘነጋን ጀመር። አደራ ደግሞ ይህን የ‘ሚሞሪ’ ችግር በ‘ቴሌ’ እንዳታላክኩትና የታሪክ ውዝግባችንን እንዳታጦዙት። የምሬን ነው! ዘንድሮ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መቧቀስ የዴሞክራሲ ‘ትሬዲንግ’ መስሏላ። እውነቴን ነው! ‹‹ቆይ ግን እኛ በስንቱ ተቧቅሰን ነው ሰው የምንሆነው?›› ብዬ የባሻዬን ልጅ ባዋየው፣ ‹‹አንተማ ምኑን አይተኸው?›› አለኝ። ነገር ነገር ሲለው እንደኔ የሚገባው የለም አይደል? ‹‹እንዴት እኔ ሳልሰማ የዓደዋ ዘመቻ በድጋሚ ታውጆ ነበር እንዴ?›› ብለው፣ ‹‹እንዲያም ልትለው ትችላለህ። ሥራ እያጣደፈህ ‘ፌስቡክ’ አላዘወትር አልክ እንጂ እኮ ሰው በኪሱ ‘ዓደዋን’ ይዞ መዞር ሆኗል ሥራው። ደግሞ የሚያሳዝንህ ይኼኛው የስድብ ፍልሚያ እርስ በርስ መሆኑ ነው፤›› አለኛ።

እምዬ ምኒልክና ፈረሳቸው ያልሰሙት ጉድ አልኩ። ይህን እያልኩ የባለሥልጣን ፈቃድና የተቋም ደብዳቤ በማያሻው ምናቤ ምኒልክን እዚህ እኛ ዘመን ላይ ሳልኳቸው። በሚወዷቸና እንቁ የሴቶች አርዓያ በሆኑት ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ልዩ ትዕዛዝ አዲስ ሻሽ ጠምጥመው የተነሱትን ፎቶ ገጭ አድርገው (ልጅ አዋቂው በ‘ፌስቡክ’ የግል ፎቶ ቤት ሲከፍት እሳቸውስ ለምን ይቅርባቸው?) የፌስቡክ አካውንት ሲከፍቱ። አይዟችሁ የማሰብ ነውር የለውም። የሚያስብ ሰው መፍራትና ማስፈራራት ነው ከባዱ ነውር። ተሳሳትኩ? እና እምዬ ምኒልክ ‘ላይካቸውን’ እና ‘ዲስላይካቸውን’ እየቆጠሩ እቴጌን፣ ‹‹ወዲህ ነይማ!›› ሲሏቸው። ‹‹ምን ሆንክ?›› ሲሏቸው እቴጌ። ‹‹አየሽልኝ ብርሃን የተመኘንለትን ሕዝብ?›› ሲሉ ‘ኮሜንት’ እያነበቡ በትካዜ ሰጥመው። እቴጌ ደግሞ፣ ‹‹እኔ ድሮም አንተ አለህ ብዬ እንጂ ወትሮም ለአንዲት ነፍሴ እየሩሳሌምን እንደምመኝ ታውቃለህ፤›› ሲሏቸው ለምን እንደሆነ አላውቅም ታዩኝ። ትግ ትጉ ለዳኝነት ይከብዳላ!

የእኛ ጨዋታ በወግ ነውና የሚዘወረው ጥቂት ገጠመኞች ጣል ላድርግባችሁ እስኪ። ‘ሰው መቼስ ያለውን ከሰጠ ንፉግ አይባልም፡፡’ ተርፎኝ ከኮሚሽኔ ባልዝቅላችሁም ወግም ስንቅ ነው ላወቀበት። አይደል እንዴ? ታዲያ ማጣፊያው አጥሯቸው ሳይወዱ የሰው ፊት የሚገርፋቸውን ትተን በግልጽም በሥውርም ልመና ላይ የተሰማሩት ወገኖቻችን ይኼ አይገባቸውም። አንዱ ባለፈው ‹‹በሁዳዴ?›› አለኝ። ‘ልመና ያበላል’ ተብሎ እንጂ ቸግሮት ጎዳና እንዳልተሰደደ ‘በሁዳዴ’ ሲለኝ ነቅቻለሁ። አይገርማችሁም? በሁዳዴ ብሎ ልመና እስኪ። ‹‹እግዜር ይስጥልኝ!›› አልኩ። አላወቀም እንጂ ትህትናና ትዕግሥቴ ራሱ ጥሩ ምፅዋት ነበር። ማንጠግቦሽ ኋላ ሳገኛት እንዲህ ብላት፣ ‹‹ትዕግሥትና ትህትና የምህረትና የፍቅር ክፍያ መሆኑ ያልገባቸውን ግብዞች ዓይቶ ነዋ፤›› ብላኝ ነበር። ምን ለማለት ነው ብዬ አልጠየቅኳትም።

እንዴ! በአግቦ ፍቺ ዛልን እኮ! ‹‹አንተን ጠየቅኩ እንጂ እሱማ ይሰጠኛል፡፡ ደግሞ በሁዳዴ የሚመፀውት ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በፋሲካ ሲነሳ በቀኙ ይቀመጣል’ ይላል መጽሐፉ፤›› አለኝ። ‘ይብላኝ ላልተማረ’ እያልኩ በሆዴ ቶሎ ለመገላገል ኪሴ ስገባ አሥር ሳንቲም ማግኘት። አሥር ሳንቲም መኖሯን ለብዙ ጊዜ ዘንግቼ መቆየቴ ገርሞኝ የብራችን ዋጋ ማጣት አስተከዘኝ። ምሳጤዬ ውስጥ ሳለሁ እጄን ዘርግቻለሁ (ልብ አድርጉ)፡፡ ‹‹ምንድነው ይኼ?›› አለኝ እንደ አራጣ አበዳሪው ሻርሎክ ዓይኑን አፍጥጦ። ኦ ለካ ጊዜው እንኳን የሼክስፒርን ሥራዎች የራስን የሕይወት ሞራ በጥሞና እንዲያነቡ አይፈቅድም። ይቅርታ! ይቅርታ!

ከደንበኞቼ ጋር ተደዋውዬ ሚሊዮንን እንደ ሽልንግ ወደ አቃለለው ቤት ሸመጠጥኩ። ስደርስ ገዢና ሻጭ ‘ባልኮኒው’ ላይ ‘ብሉ ሌብል’ ቺርስ እየተባባሉ ደረስኩ። ሰዓቴን ሳየው ገና ማንጠግቦሽ ቡና አላቀራረበችም። እንዳልቀደም ላቤ በጀርባዬ እየተንቆረቆረ ያገናኘኋቸው ደንበኞቼ በሞቀ ፈገግታ ተቀበሉኝ። ቢሸጥ ኮንቴይነር ሙሉ ሰልባጅ ገዝቶ የሠፈሬን ነዋሪ በሚያንበሸብሽ ብርጭቆ ተራዬን ቀድተውልኝ ‘ቺርስ’ አሉኝ። ‘ግድ የለም ይቅርብኝ’ ብል የ‘ቦነሴ’ ነገር አሳሰበኝ። ስለዚህ ባዶውን እየጮኸ አሲድ በሚተፋ አንጀቴ ላይ አሲድ ቸለስኩበት። መስማማታቸውን ባልጠራጠርም ለማረጋገጥ ስለፈለግኩ፣ ‹‹እንዴት ነው ታዲያ?›› እያልኩ እጠይቃለሁ። አንዴ ወልዳ እንድትመጣ ወደ አሜሪካ ስላሳፈሩዋት ሚስታቸው (ወደ አሜሪካ ሲሉ አሁን እዚህ ጉለሌ እዚህ መካኒሳ እንጂ አትላንቲክን አቋርጠው የሚደርሱበት አኅጉርና አገር የሚጠሩ ይመስላል እናንተ?)

አንድ ዓመት ሳያሽከረክሯት ስላልተመቸቻቸው አውቶሞቢልና ሊቀይሩት ስላሰቡት የቅርብ ጊዜ ሞዴል መኪና በሰፊው ይጫወታሉ። ከተጠመቀ ቆየት ካለ ውስኪያቸው እየማጉ ከቁብ አልቆጠሩኝም። ‘ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በአምስት ዓመት አንዴ ከቆጠረህ አይበቃህም?’ ይመስላል። ነገሩን ላሳጥረውና (እንኳን አንዛዝተውን እንዲሁም አልቻልነው) አንደኛው ‘ቼክ’ አውጥቶ ፈረመና ‘ኮሚሽኔን’ ከባንክ እንድወስድ ሰጠኝ። ‘በቼክ’ መቀበሌን አደራ ለማንም አልተናገርኩም፣ እናንተም ለማንም አታውሩ። ደግሞ በኋላ ‹‹አንበርብር በ‘ቼክ’ ነው የሚጫወተው…›› ብሎ አንዱ ማጅራቴን ቢለኝ ማን አለኝ? ትቀልዳላችሁ እንዴ! ነው ወይስ ውዷ ማንጠግቦሽ ‘አንበርብር ቢሞትም ‘ቼኩ’ አይሞትም’ በሚለው ትፅናናለች ብላችሁ ታስባላችሁ? ኧረ እንዴት ተቀለደ!

ቀልድ ብል አንዲት ሰሞነኛ ቀልድ ትዝ አለችኝ። ማን ያለኝ ያለእናንተ? ልንገራችሁና ሳቁልኝ እንጂ። የዘንድሮ ሰው ገንዘቡን፣ ገመናውን፣ ውሎውንና አዳሩን መሸሸግ ክፉኛ ተላምዶ ጥርሱንም ይደብቀው ይዟል። ነው ወይስ ንብረት ሲመዘገብ ጥርስም ተካተተ? እኔስ አልሰማሁም። እናንተ ከሰማችሁ ንገሩኝ ብዬ እኮ ነው። ሰው ዙሪያውን፣ በእነ ‘ጋሽ እኛ ብቻ እናውቃለን’ ኩርፊያና ቅሬታ ወፍሮ፣ የእግዜር ሰላምታ ሲሰጥም ተናዶ ነው። ፈገግ አይልም። ታዲያስ! ቢቸግር አይደል እንዴ ‘ኑ ሳቅ እናስተምራችሁ’ የሚሉ ሰዎች ‘ቢዝነስ’ የጀመሩት። ኦኦ! ቀልድ አወራለሁ ብዬ ቀንድ የሚያስበቅል ሀተታ ጀመርኩላችሁ።

ይኼውላችሁ አያ አንበሴ (የዱር አራዊት አለቃው አንበሳ ማለቴ ነው) ዶሮንና አሳማን በአዋጅ ነጋሪ ቶሎ ድረሱ ብሎ ጠራቸውና ፊቱ ቀርበው እጅ ይነሳሉ። አንበሳም፣ ‹‹እጅ መንሳት ብቻውን ሆድ አይገባም፣ ኢኮኖሚ አያሳድግም፣ ግድብ አይገነባም!›› ካላቸው በኋላ ተቆጥቶ፣ ‹‹አሁን በጣም እርቦኛል ያላችሁን ስጡኝ፤›› ሲል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ። ዶሮ ፈጣኗ ቀልጠፍ ብላ እንቁላሏን ዱብ አድርጋ፣ ‹‹ይኼው እኔ ያለኝን ሰጥቻለሁ፣ አንተ ደግሞ ያለህን ስጥ፤›› ብላ አሳማው ላይ ፍጥጥ። የገባው ይስቃል። ያልገባው ቀልዱን እንዲያብላላው ተፈቅዷል። ‘ማን ነው ዶሮ? ማን ነው አሳማ?’ እያሉ መራቀቅና ማሰብ ግን በፈጠራችሁ ይዣችኋለሁ (ታዲያ በምኔ አስይዛችኋለሁ?) ክልክል ነው! ምነው? ማሰብ መከልከል በእኔ አልተጀመረ!

በሉ እስኪ ነገር ሳናመጣ እንጠጣና እንሰነባበት። ያን ጉደኛ ቤት ካሻሻጥኩና ደህና ገንዘብ ካገኘሁ በኋላ ልክ አልነበርኩም። ዱባይ፣ ካሪቢያን ደሴት ሄዶ መዝናናት አምሮኝ ነበር። ይህቺን የነተበች ካፖርቴን በአዲስ ካፖርት ቀይሬ መዘነጥ ልቤ ቋምጦ ነበር። ከዚያ ‘ቤትሽን ከቤቴ ላይ አንሺልኝ’ ከሚባልበት ሠፈር ወጥቶ አፓርትመንት መከራየትም አሰኝቶኝ ነበር። ሳስበው ዓይን ውስጥ መግባት ነው፣ ዓይን ውስጥ መግባት ደግሞ እንደምታውቁት ከዓይን ያጠፋልና አርፌ፣ እንደ ወትሮዬ፣ ወደ ተለመድችዋ ግሮሰሪ አመራሁ። ስገባ ግሮሰሪያችን ቀዝቅዛለች። ባለቤቱም በገበያው መቀዛቀዝ ተጨንቆ መንፈሱ ቀዝቅዟል። ከደጅ አየሩ ይቀዘቅዛል። ውስጥ ሙዱ። ጥቂት ቆይቶ የባሻዬ ልጅ ከች አለ።

ሁለታችን ብቻ አንድ አንድ ቢራ ይዘን (በ‘ብሉ ሌብል’ አስጀምሮ በቢራ አያስጨርሳችሁ ከማለት ውጪ ሌላ የለኝም)፣ ‹‹አንበርብር ይኼን ፍራ!›› አለኝ። ‹‹የቱን?›› ስለው ‹‹ይኼን! ጭርታውን!›› አለኝ። ‹‹ለምን እፈራለሁ? እንዲያውም የመሠልጠን ምልክት ነው! ይኼ የሚያሳየው የቁጠባ ባህላችን እያደገ እንደሆነ ነው!›› አልኩት። የግሮሰሪዋ ባለቤት እንዳይሰማኝ ድምፄን ዝቅ አድርጌ። ‹‹እኮ ቁጠባ? እኮ የእኛ ባህሪ በአንድ ቀን ተቀይሮ? እኮ ሥልጣኔ አልከው? እውነት ኖሮን ነገን አስበንና ለነገ ተጨንቀን እያልከኝ ነው? መልስልኝ እንጂ! እየቆጠብን ወይስ እየተቆጠብን?›› ቢለኝ ግን መልስ ከመመለስ እኔ ራሴ ተቆጠብኩ። እስኪ እናንተ አግዙኝ ጎበዝ፡፡ ምንድነው ጭርታው? ምንድነው ድብርቱ? ‘እየቆጠብን ወይስ እየተቆጠብን?’ መልካም ሰንበት!   

             

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት