Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሮሚያ ክልል የአልሚዎችን የማዕድን መሬት ነጥቆ ለወጣቶች በማዋሉ ቅሬታ ቀረበ

የኦሮሚያ ክልል የአልሚዎችን የማዕድን መሬት ነጥቆ ለወጣቶች በማዋሉ ቅሬታ ቀረበ

ቀን:

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የሚገኙ ኢንቨስተሮች ያለሙትን የማዕድን መሬት በመንጠቅ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ቅሬታ አስነሳ፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ በዱከምና በገላን ከተማዎች የሚገኙ 42 ጠጠር አምራቾች፣ የኦሮሚያ ክልል እየወሰደ ያለው ዕርምጃ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ላይ የተደነገገውን ንብረት የማፍራት መብት ይጥሳል በማለት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

እነዚህ ጠጠር አምራቾች የካቲት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጻፉት ደብዳቤ፣ ዕቅዱም ሆነ ዕርምጃው ፍትሐዊ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢንቨስተሮችን ይዞታና ንብረት በመንጠቅ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ሥራ በማስገባት ሥራ አጥነትን ለመፍታት መሞከር ፍትሐዊ አይደለም ሲሉ ባለንብረቶቹ አቤቱትቸውን አሰምተዋል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(1) ላይ እንደሚጠቅሰው ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆን ይከበርለታል፡፡ ይኼ መብት የሕዝብ ጥቅም ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን ዜጎች መብቶች አስካልተቃረነ ድረስ ንብረት የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል፡፡ እነዚህ በገላንና በዱከም ከተሞች የሚገኙ ባለንብረቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲነሱ ትዕዛዝ መሰጠቱ አግባብ አለመሆኑን፣ የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አዲስ በቀረፀው ስትራቴጂ 1.2 ሚሊዮን በሚጠጉ ሥራ አጥ ወጣቶችን ሥራ ለማስያዝ፣ ቀደም ሲል ከተለመዱ ዘርፎች ውጪ አዳዲስ ዕቅዶችን ነድፏል፡፡

በተለይ በምሥራቅ ሸዋና በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ለሚገኙ ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር የተጠቀመበት ስትራቴጂ በማዕድን ሥራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶችን በማስወጣት፣ በቦታው ወጣቶችን አደራጅቶ ማስገባት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንትና የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓብይ አህመድ በቅርቡ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን በማዕድን ማውጫዎች ላይ ወጣቶችን ለማሰማራት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ባካሄደው ስትራቴጂካዊ ጥናት ከዚህ በፊት ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ስም የተፈጥሮ ማዕድናትን እሴት ሳይጨምሩ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ ክልሉ በአሁኑ ወቅት ይኼን አሠራር በማስቀረት ባለሀብቶች እሴት ወደሚጨምሩባቸው ዘርፎች መሄድ አለባቸው ብሏል፡፡ በተለይ ቀይ አፈር፣ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ፑሚስና ታንታለም ለማምረት ብዙ ካፒታል የሚያስፈልግ ባለመሆኑ ከዚህ የሥራ መስክ እንዲወጡ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡

ክልሉ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ባካሄደው በዚህ ጥናት ካፒታል ቢያስፈልግ እንኳ ምርትን በመሸጥ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን መግዛትም ሆነ መከራየት እንደሚቻል ይገልጻል፡፡

አቶ ዓብይም እንዳረጋገጡት፣ በኦሮሚያ ክልል የመሬትና የሰው ሀብት ካፒታል አለ፡፡ የሚጎድለው ማሽንና ትራንስፖርት ነው፡፡ ይኼን ጉድለት ከባለሀብቶች ጋር በመነጋገር ለመፍታትና ለወጣቶችም ሥልጣና በመስጠት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን ከይዞታቸው እንዲነሱ ከመጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ብቻ የሚቆይ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውና በዚህ ጊዜ ውስጥ ካልተነሱ ለንብረታቸው ዋስትና የሚወስድ አካል እንደሌለ የተነገራቸው ባለንብረቶች አቤቱታቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

አቤቱታ በማቅረብ የክልሉን ሐሳብ ከሚሞግቱት መካከል የመንዳሎት ጠጠር ማምረቻ ኩባንያ ባለቤት አቶ አቡ ጄላ ይገኙበታል፡፡       

አቶ አቡ ከ15 ዓመታት በፊት በገላን ከተማ ጠጠር ማምረት ውስጥ መግባታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ኢንቨስትመንት 60 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውም ያስረዳሉ፡፡

አቶ አቡ እንደሚሉት፣ የኦሮሚያ ክልል ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ሀብት የማፍራት መብት ይጥሳል፡፡ በተጨማሪም ከኦሮሚያ፣ ውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በነበራቸው ውል መሠረት ውሉ በሚፈርስበት ወቅት ተግባራዊ መደረግ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉም አስታውሰዋል፡፡ ሥራው ተጨማሪ እሴት የሚደረግበት፣ ከፍተኛ ባለሙያና ካፒታል የሚጠይቅ ሥራ ሆኖ ሳለ ተገቢው ዕውቅና አለመሰጠቱ፣ ለወጣቶች የባለሀብቱን ቦታ ነጥቆ መስጠት ወደፊት የሚፈጥረው አሉታዊ አንድምታ ከግምት አለመግባቱን በማስረዳት መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡

‹‹በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎችን በማስወጣት ለኪሳራና ለውድቀት በመዳረግ፣ ምንም ላልለፉ ወጣቶች ማከፋፈል በፍፁም ተቀባይነት የለውም፤›› ሲሉ አቶ አቡ ይናገራሉ፡፡

በገላን ከተማ የጠጠር አምራች የሆኑት አቶ አለማየሁ መንገሻም በአቶ አቡ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡

‹‹ወጣቱ በራሱ የሚተማመን ጠንካራና ልማታዊ ኃይል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ ያልሠራበትንና ያልደከመበትን ሀብት እንዲወርስ ማድረግ፣ በራሱ የማይተማመን ጥገኛ ኃይል እንዲፈጠር በር መክፈት ነው፤›› ሲሉ አቶ አለማየሁ ጉዳዩ በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

‹‹ነገ እየተመረቀ የሚወጣው ሥራ ፈላጊ ወጣት መንግሥት ከባለሀብት ነጥቆ ይሰጠኛል የሚል የጥገኝነት ተስፋ እንዲይዝ አደገኛ መልዕክት የሚያስተላለፍ ነው፤›› ሲሉ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

በአንፃሩ ግን እነዚህ ባለሀብቶች የመፍትሔው አካል መሆን የሚችሉባቸው የተለዩ መንገዶች ስላሉ፣ ክልሉ ዕቅዶችን አዘጋጅቶ እንዲያነጋግራቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...