Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በካይ ፋብሪካዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ተስኖታል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማን ወንዞች እየበከሉ የሚገኙ ፋብሪካዎች የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ እንዲተክሉ የተሰጣቸው ቀነ ገደብ ከተጠናቀቀ ሦስት ዓመታት ቢያልፉም፣ አሁንም ፍሳሻቸውን በቀጥታ ወደ ወንዝ መልቀቁን ቀጥለውበታል፡፡ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንም ዕርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡  

በአዲስ አበባ ከተማ በካይ ፋብሪካዎችን ለመቆጣጠር፣ አዲስ የሚቋቋሙ ፋብሪካዎች ደግሞ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዲያካሂዱ የማስገደድ ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በጥፋተኞች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ አልደፈረም፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከተማውንና አጎራባች አካባቢዎችን በመበከል ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች በተለይም የቆዳ ፋብሪካዎች፣ እስከ ታኅሳስ 2006 ዓ.ም. ድረስ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ እንዲገነቡና ብክለታቸውን እንዲቀንሱ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ግንዛቤና ብክለት ቁጥጥር ቡድን አስተባባሪ አቶ ለሜሳ ጉደታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሥሪያ ቤታቸው ሕጉን በሚተላለፉ አካላት ላይ ዕርምጃ እስካልወሰደ ድረስ ጥፋተኛ ነው፡፡

‹‹ማንኛውም ሰው ከተፈቀደለት ደረጃ በላይ አድርጎ ከለቀቀ ወይም እንዲለቅ ከፈቀደ ተጠያቂ ይሆናል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ለሜሳ፣ ‹‹ፋብሪካዎቹ እየበከሉ መሆኑን በላብራቶሪ ምርመራ አውቀናል፡፡ እንዳወቅንም ወዲያውኑ ማስቆም ነበረብን፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ አልቻልንም፤›› ሲሉ ባለሥልጣኑ በካይ ፋብሪካዎችን እያስታመመ መሆኑን አምነዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከአምስት ያላነሱ ወንዞች አሉት፡፡ ትልቁ አቃቂና ትንሹ አቃቂ በከፍተኛ ደረጃ መበከላቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በተለይ ከኢንዱስትሪ፣ ከሆስፒታሎችና ከንግድ ተቋማትና ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሾች የሚያደርሱት ብክለት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በከተማው ውስጥ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም በዋናነት ግን አምስት ቆዳ ፋብሪካዎች በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ጥናቶች በካይ መሆናቸው መረጋገጡን አቶ ለሜሳ ገልጸዋል፡፡ ለጊዜው ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

‹‹የቆዳ ፋብሪካዎች ለቆዳ ማለስለሻ የሚጠቀሙበት ክሮም የተሰኘ ኬሚካል የሰውን ልጅ የአስተሳሰብ ደረጃ ዝቅ ያደርጋል፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ለሜሳ፣ እነዚህ ፋብሪካዎች ይህንን ኬሚካል የያዘ ፍሳሽ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ወንዝ በቀጥታ ይለቃሉ ብለዋል፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንዱ ሊትር ሁለት ሚሊ ግራም ብቻ እንዲለቀቅ ይፈቀዳል፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ የሚገኙት የቆዳ ፋብሪካዎች ግን ዘጠኝ ሺሕ ሚሊ ግራም በሊትር ይለቃሉ፤›› ሲሉ አቶ ለሜሳ አስረድተዋል፡፡

በከተማው የሚገኙ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች ፍሳሻቸውን ሕክምና ሳያደርጉለት ወደ አካባቢ የሚለቁ በመሆናቸው፣ በተለይ በወንዝ ዳር የሚገኙ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢ ነዋሪዎችና እንስሳት ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየተጋለጡ ነው፡፡

በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ በሚጠበቀው የአዲስ አበባ ከተማ አሥረኛው ማስተር ፕላን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች በሙሉ ከከተማ ውጭ እንዲወጡ ለማድረግ አቅዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን ኮሚሽነር አቶ ማቲዮስ አስፋው ማክሰኞ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የመጨረሻው ውይይት ላይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በከተማው ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች ከከተማው ወጥተው እንደገና ይቋቋማሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች