ለዱር እንስሳት ቁጥር መመናመን የደን ምንጠራ፣ ሕገወጥ አደን፣ ድርቅና ሌሎችም ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የዱር እንስሳት መጠኑ ቢለያይም አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አልባትሮስስ የተባለው የአዕዋፋት ዝርያ አንዱ ነው፡፡ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ውስጥ በሚገኘው ውቅያኖስና በሰሜናዊው የሰላማዊ (ፓስፊክ) ውቅያኖስ ላይ በብዛት ይኖራል፡፡
ሰሞኑን ቢቢሲ እንደዘገበው የአዕዋፋቱ ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ከነበረው ቁጥር አንፃር ሲታይ በአሁኑ ወቅት የአልባትሮስስ ቁጥር በግማሽ ቀንሷል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥና በዘፈቀደ የሚተገበር የዓሳ ማጥመድ ጉዳይ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡