Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅባለበርኖሶቹና የሲኒማ ሰሌዳ

ባለበርኖሶቹና የሲኒማ ሰሌዳ

ቀን:

ይህ ፎቶ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ከመውረሯ አንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ (ፒያሳ) የነበረውን ገጽታ ያሳያል፡፡ አዲስ አበቤዎቹ ባለበርኖስ ለባሾቹ በአሜሪካ ቡና ቤት (CAFÉ..BAR AMERICAIN) ደጃፍ የተሰቀለውን የሲኒማ (የፊልም) ሰሌዳ ማስታወቂያን ሲያዩት ምን ብለው ይሆን?

* * *

ላይበቁ ለደቦው

ፎቅ በፎቅ ደረቡ

መርቸዲዝ ተንጋለሉ

በቄሳሩ መዲና ናጠጡ ሸለሉ

ሰርቀው እንዳልከበሩ

ገርፈው እንዳልበሉ

አሰቃይተው ያመለጡ ሁሉ

ተደባለቁን በየሠርጉ

በየስደት ቤቱ

ለሙሾው በየቀብሩ

አልቅሰው ሊያላቅሱን

አብረውን ሊጨፍሩ

ተፅዕኖ ሆነና ያለፈን መወደስ

ወኔ ጠፋና ከህሊና ለመዋቀስ

ንፅህና ደብቦ፣ እውነት እንዳይካስ

መርሳት ልማድ ሆኖ አይከፉት – ክፋት ሲደርስ

እንዳልጋጡን ሁሉ አብረውን ሲበሉ

የተበሉትም ብር ብለው ጨፈሩ

  • ሰሎሞን ዴሬሳ ‹‹ዘበት እልፊቱ ወለሎታት›› (1991)

* * *

ቅንጫቢ

በቀስታና በዝግታ የተበጀ መዘውር ኋላ ጉልበት ይሆናል። ወረቀት መልካም እርሻ ነው ብዙ ነገር ይዘራልና። ጐታም አይሻ እርሱ ከቶት ይኖራልና።

ማር ሁለት ጊዜ ያገለግላል አንድ ጊዜ መጠጥ አንድ ጊዜ መብራት ሆኖ። ምነው ቢሉ የብልሕ ሥራ ነውና አሰርም የለው።

ሕዝብና ሕዝብ ደጋና ቆላ ናቸው ንጉሡ ግን ገበያ ነው ሁሉን ያገናኛልና። ሸክላ ከተሰበረ በኋላ ገል ነው መኳንንትም ከተሻሩ በኋላ ሕዝብ ናቸው።

ክፉ ሰው ሽንቱን በሸና ጊዜ ኋላ ጉንፋን ይሆናል ምነው ቢሉ ግብሩ ተጉድፍ የተዋሐደ ነውና። ማርና እሬትን ቢመዝኑ ማን ይደፋል እሬት ምነው ቢሉ ክፉ መራራ ነውና።

ከብዙ ቀን ደስታ የአንድ ቀን መከራ ይበልጣል። ንጉሥ ምሰሶ ነው ሠራዊት ግድግዳ ናቸው መኳንንት ግን ማገር ናቸው። ለንቋጣ ልጡ እንዲማልግ እንጨቱም ቀሊል እንደሆነ ወስላታም ወዳጅ እንደዚያ ነው።

ጨው በዓለሙ ሁሉ ይዞራል ምናልባት ሰልችተው ይተውኛል ብሎ ነውን? ከሬት ጋራ ይጋባ እንደሆነ ነው እንጂ የሚለቀው የለም።

አንድ ዓይንና አንድ ዓይን ያላቸው ተጋብተው ሁለት ዓይን ያለው ልጅ ወለዱ። ይህ ነገር ምንድር ነው? አንድ ከአባቱ አንዱ ከእናቱ ነዋ። የዚህ ዓለም ትርፉ ምንድር ነው? መብላት መጠጣት ጥጋብና ኩራት ነው። ኩራት ምንድር ነው? እንደርሱ ሆኖ የተፈጠረውን ሰው መናቅ ነው።

ሰው ፍሪዳን አብልቶ አብልቶ ያሰባዋል በመጨረሻውም ይበላዋል። ምነው ቢሉ አብልቶ መብላት እንጂ ገበያ ነው። ወርቅ ቢያብረቀርቅ ብር ያብለጨልጫል ምነው እናንት መናፍቃን ጥቂት ጥቂት ብልኃት አታዋጡምን።

የዝንብ ብልኃቷ ምንድር ነው ሌላው የሠራውን መብላት ነው። ሰነፎች ሰዎችም እንደዚሁ ሌላ ሰው የሠራውን መብላት ይወዳሉ።

ድሃ ከመሆን ሀብታም መሆን ይሻላል ምነው ቢሉ አይቸግርምና። በምድር ከመኖር በሰማይ መኖር ይሻላል ምነው ቢሉ የዚህ ዓለም መከራው ብዙ ነውና።

ከባለጌ ፍቅር የንጉሥ ቁጣ ይሻላል። የረሃብ ጌትነቱ መቼ ነው እህል በታጣ ጊዜ ነው ምነው ቢሉ የሌለውን አምጡ ይላልና። የማጣትስ ጌትነቱ መቼ ነው የፈለጉት ነገር በታጣ ጊዜ ነው። የጥጋብስ ጌትነቱ መቼ ነው መብልና መጠጥ በተገኘ ጊዜ ነው። የመብላትስ ትርፉ ምንድር ነው ጥጋብ ነው።

  • አለቃ ዘነብ ‹‹መጽሐፈ ጨዋታ– 1856 ዓ.ም.›› አንድምታ መጻሕፍት (2010)

* * *

መልካምነት ለ20 ሺሕ ዶላር ያበቃው በረንዳ አዳሪ

ኬት ማክሉር ከጓደኛዋ ጋር ፊላደልፊያ የሚኖሩ ጓደኞቿን ለመጎብኘት መንገድ ትጀምራለች፡፡ ነገር ግን ከመዳረሻቸው ሳይደርሱ የተሽከርካሪው ነዳጅ በማለቁ አጉል ቦታ ላይ ለመቆም ይገደዳሉ፡፡ መኪናዋን አቁማ ስትጨነቅ ነበር ጆኒ ያገኛት፡፡ ጆኒ ለራሱ ምንም የሌለው በረንዳ አዳሪ ነው፡፡ ጭንቀቷን ተመልክቶ ግን ሊያልፋት አልቻለም፡፡ ያቆመችበት ቦታ አደገኛ መሆኑን ነግሯት በኪሱ ውስጥ የነበረውን 20 ዶላር አውጥቶም ለመኪናው ነዳጅ ገዛ፡፡ በሌለው ገንዘብ ያለውን አውጥቶ ይረዳኛል ብላ ያልጠበቀችው ኬት ገንዘቡን መልሳ እንደምትከፍለው ቃል ገብታና አመስግናው ነበር የተለያዩት፡፡ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር በመሆንም ጆኒን ከችግር ማውጣት የሚቻልበትን መንገድ ዘየዱ፡፡ በስሙም ገቢ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡ እስካሁንም 20 ሺሕ ዶላር ያሰባሰቡለት ሲሆን፣ ጆኒ መኖርያ ቤትና የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያገኝበትን መንገድ እያፈላለጉለት እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

* * *

በተፈጥሮ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠሩት የምሽት መብራቶች  

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች መሳካት ያልቻለው የመቶ በመቶ ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ባደጉት አገሮች አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ የቢቢሲ ዜና ያመለክታል፡፡ የዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ማዕከል (ናሳ) በተገኘ የሳተላይት መረጃ መሠረት በፕላኔቷ ላይ ያለው የብርሃን መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በዓለም ላይ በብርሃን መጠናቸው ቀዳሚ የሚባሉት ስፔንና አሜሪካ የአርቲፊሻል ብርሃን መጠናቸው ልዩነት አላሳየም፡፡ ይሁንና የደቡብ አሜሪካ፣ የአፍሪካና የእስያ አገሮች የብርሃን መጠን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡

አጠቃላይ የብርሃን መጠኑ በየዓመቱ በሁለት በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡ ይህም የተፈጥሮን ዑደት እየበጠበጠ የሚገኝና ሕይወት ባላቸው ነገሮች ጤንነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጥናቱ አሳይቷል፡፡ በምሽት ያላቸውን የብርሃን መጠን መቀነስ ያሳየው የየመንና ሶሪያ ሲሆኑ፣ ሁለቱ አገሮች የጦርነት አውድማ መሆናቸውን የብርሃን መጠናቸው እንዲቀንስም ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

* * *

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...