Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ መቼ እንደሚወጣ አይታወቅም

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ መቼ እንደሚወጣ አይታወቅም

ቀን:

   – ዕጣ ከወጣባቸው 39,249 ቤቶች ጋር ቅዳሜ ይመረቃሉ

ግንባታቸው ሊጠናቀቅ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ የተገለጸው፣ በክራውንና ሰንጋተራ ላይ የተገነቡ 1,292 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ዕጣ መቼ እንደሚወጣባቸው እንደማይታወቅ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ገለጸ፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ቀንዓ ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደተናገሩት፣ በክራውን 8,825፣ በሰንጋተራ 410፣ በድምሩ 1,292 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ቤቶቹ ከ98 በመቶ በላይ ግንባታቸው ተጠናቆ አንዳንድ የማጠናቀቂያ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ሥራው ሙሉ በሙሉ በቅርብ ቀን ተጠናቆ የሚተላለፈው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆኑ፣ ባንኩ መቼ ዕጣ እንደሚያወጣ እንደማያውቁና በዚህ ቀን ብለው መናገር እንደማይችሉ አቶ ኃይል ተናግረዋል፡፡

ለ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮግራም ከተመዘገቡት ውስጥ ከ15 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ክፍያቸውን መቶ በመቶ ማጠናቀቃቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የዕጣ አወጣጡ ሙሉ በሙሉ ክፍያ ላጠናቀቁት ብቻ፣ ወይም ሁሉንም ተመዝጋቢዎች ያካተተ ይሁን አይሁን የሚለውን የሚመለከተው አካል ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ጊዜ 39,229 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች እየገነባ መሆኑንም አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ኃይሉ ሰጥተውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ‹‹ከአንድ ወር በኋላ በዕጣ ይከፋፈላሉ›› ማለታቸውን በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የካቲት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በ11ኛው ዙር በዕጣ የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የመገናኛ ብዙኃን እንዲጐበኙ አድርጓል፡፡

ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕጣ የወጣባቸውን 39,249 የባለ 20/80 እና 10/90 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚመረቁ ቢሮው ገልጿል፡፡ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ይመረቃሉ፡፡ በተለይ በመልሶ ማልማትና በመንገድ ግንባታ ምክንያት ለተነሱ ነዋሪዎች አያት ቦሌ ቁጥር 4 የገነባቸውን 1,811 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁን፣ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐረጐት ዓለሙ ገልጸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ማኅበራዊ ግንኙነታቸው እንዲቀጥል ለማድረግ ታስበው መገንባታቸውንና ከ150 ሱቆች ጋር ለእነዚህ ነዋሪዎች ብቻ መተላለፋቸውን አክለዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ቅጥር ግቢያቸው ያልፀዳና የሕንፃዎቹ አንዳንድ ክፍሎች ወለል የተሰነጣጠቀ መሆኑን የተመለከቱ ጋዜጠኞች፣ ‹‹ተጠናቋል የሚባለው ምኑ ነው?›› በማለት ጥያቄ ቢያነሱም፣ ‹‹አንዳንድ የማጠናቀቂያ ሥራዎች በነዋሪዎች የሚከናወኑ ናቸው፤›› በማለት አቶ ሐረጐት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በቦሌ አራብሳ በ192 ሔክታር ቦታ ላይ 20 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን አቶ ሐረጐት ገልጸዋል፡፡ በቂርቆስ፣ በልደታና በፕሮጀክት 15 የቤቶች ልማት ግንባታ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንደተገነቡ የጠቆሙት አቶ ሐረጐት፣ ለጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በ283 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ ሦስት የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ መገንባቱንም አክለዋል፡፡

ኤምቢአር ተብሎ በሚጠራ ቴክኖሎጂ የተሠራው ማጣሪያ ጣቢያ 10,500 ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም እንዳለውም አቶ ሐረጐት ገልጸዋል፡፡

በቦሌ አራብሳ የተገነቡ ቤቶች ግንባታቸው ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ እንዴት ለምረቃ ተዘጋጁ በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሐረጐት፣ ‹‹ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል ማለት ይቻላል፤›› ከማለት ባለፈ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

በቦሌ አራብሳ 21.5 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን ንጣፍ በ280,382,708 ብር፣ 13.1 ኪሎ ሜትር አስፋልት ደግሞ በ740,793,577 ብር መገንባቱን፣ ከመንገዶች ባለሥልጣን የተወከሉ ኃላፊ አስረድተዋል፡፡ በቂሊንጦ 1,269 የ20/80 ብሎኮች፣ 164 የ10/90 ብሎኮች የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተገነቡ ቢሆንም፣ ለቅዳሜ ምረቃ የሚሆን ፊት ለፊቱን በቀይ አሸዋ ለብሶ ከመታየቱ ውጪ ነዋሪዎችን ወደ ቤቶቹ የሚያስገቡ መንገዶች ያልተሠሩ መሆኑን ጋዜጠኞች ተመልክተዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በማሠራት ላይ ያሉ ኃላፊም ሥራው እንደተጠናቀቀ ከመግለጽ ውጪ ስለጉድለቱ መናገር አልፈለጉም፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የተሠሩ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ የ10/90 ቤቶች መጠናቀቃቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ የጉብኝቱ አካል ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...