Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት የ269 ኢንቨስተሮችን መሬት ነጠቀ

የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት የ269 ኢንቨስተሮችን መሬት ነጠቀ

ቀን:

የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ፣ ነገር ግን ደካማ የሥራ አፈጻጸም ውጤት አስመዝግበዋል ያላቸውን 269 ኢንቨስተሮች መሬት መንጠቁን አስታወቀ፡፡

የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ኢንቨስተሮቹ ባስመዘገቡት በጣም ደካማ ውጤት ምክንያት ክልሉ የ269 ኢንቨስተሮችን መሬት መንጠቁን አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ የክልሉ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ ሲያብራሩ፣ የኢፌዴሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የጋምቤላ ክልል የግብርና ኢንቨስትመንትን ሁኔታ በተመለከተ በባለሙያ እንዲጠና ማድረጉን አስታውሰው፣ ጥናቱ ተጠንቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አመልክተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተካሄደው ጥናት ውጤት መሠረት በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ያልቻሉና በጣም ደካማ ውጤት ያስመዘገቡ 269 ኢንቨስተሮች ላይ፣ የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ቦርድ የካቲት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ከዚህ በፊት የተገባው የግብርና ኢንቨስትመንት ውል እንዲቋረጥና የተረከቡት የግብርና ኢንቨስትመንት መሬትም እንዲነጠቅ መወሰኑን፣ አቶ ጋትሉዋክ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ካቢኔም የካቲት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ የኢንቨስትመንት ቦርዱን ውሳኔ አፅድቋል ሲሉ አቶ ጋትሉዋክ አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን የጋምቤላ ክልል ግብርና ኢንቨስተሮች የክልሉ መንግሥት ውሳኔ መሠረት የሌለውና በፍፁም ሊተገበር የማይችል ነው ብለውታል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ክልሉ መሬት መስጠትና መንጠቅ ላይ ማተኮር የለበትም፡፡ በክልሉ የመሠረተ ልማት ባልተሟላበት፣ የፀጥታ ችግር ባለበት፣ የፋይናንስ አቅርቦትና የገበያ ዋስትና በሌለበትና የመልካም አስተዳደር ችግር በተንሰራፋበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያለ መጠነ ሰፊ ዕርምጃ መወሰድ አግባብ አለመሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኢንቨስተሮች ተናግረዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ኢንቨስተሮች መካከል ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያካፈሉት እንደገለጹት፣ ሰኔ 2008 ዓ.ም. የተካሄደውን ጥናት መቶ በመቶ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን በግዮን ሆቴል በተካሄደው ስብሰባ አስረድተዋል፡፡

ያላቸውን ልዩነት በተለያዩ መንገዶች በመግለጽ ላይ እያሉና መፍትሔዎችም እየቀረቡ ባለበት ወቅት ይህ ዕርምጃ መወሰዱ አግባብ አለመሆኑን ኢንቨስተሮቹ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ይታጠፋል የሚል እምነት የላቸውም፡፡

ለዓመታት መሬት ይዘው ወደ ልማት ባልገቡና የመረጃ ችግር ባለባቸው ኢንቨስተሮች ላይ ዕርምጃ መወሰዱ አግባብ ቢሆንም፣ በጅምላ የሚወሰድ ዕርምጃ ግን ለማንም እንደማይበጅ ኢንቨስተሮቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት በጋምቤላ ክልል የግብርና መሬት ላይ የተደረገው ጥናት መሬት ማዘጋጀትና ማስተላለፍን በተመለከተ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ አመልክቷል፡፡ ከተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ የይዞታ ካርታ የሚሠራው በቢሮ ሳይሆን በመኖሪያ ቤትና በጫት ቤት መሆኑ፣ የ381 ባለሀብቶች 45,531.11 ሔክታር መሬት መደራረብ፣ የክልሉን ባለሀብቶች ማበረታታት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ የካፒታል ችግር መኖር፣ የባንክ ብድር አለመኖርና የአመራር ድጋፍ አለመኖር ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡

መሬቱን በማልማት ሒደት በሚታዩ ችግሮች ላይ በተካሄደው ጥናትም፣ 623 ባለሀብቶች 630,518 ሔክታር መሬት ተረክበው መልማት የሚጠበቅበት 405,572.84 ሔክታር መሬት ሲሆን፣ መልማት የቻለው ግን 64,010.62 ሔክታር ብቻ መሆኑን አመልክቷል፡፡

200 ባለሀብቶች (12 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና 188 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ) ብድር አግኝተዋል፡፡ ከብድሩ ውስጥ 4.96 ቢሊዮን ብር ተፈቅዶ፣ 4.27 ቢሊዮን ብር የተለቀቀ ነው፡፡

አገር በቀል ኩባንያዎች ከፍተኛ ቅሬታ ከሚያቀርቡበት ጉዳይ መካከል በአጠቃላይ ለአገር በቀል ኩባንያዎች የቀረበው ብድር 1.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሆኖ ሳለ ከተለቀቀው ገንዘብ የአንበሳውን ድርሻና ከፍተኛ መጠን ያለው መሬት የወሰዱት የውጭ ኩባንያዎች መሆናቸውን ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች የሥራ አፈጻጸማቸው ደካማ መሆኑ እየታወቀ አንድ ላይ ወቀሳ እየቀረበ መሆኑን ይቃወማሉ፡፡

የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ጉዳይና የሥራ አፈጻጸም ተለያይቶ ሊቀርብ እንደማይገባም ኢንቨስተሮቹ እየጠየቁ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...