እ.ኤ.አ. በ2016 በኢትዮጵያ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ይዞታ የዳሰሰው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት በዓመቱ ለእስር የተዳረጉ ከ10,000 በላይ ዜጎች ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ፣ የሕግ ማማከር አገልግሎት እንዳላገኙና ክስ እንዳልተመሠረተባቸው ገለጸ፡፡
ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. ባቀረበው የምርመራ ሪፖርት 28 የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ 173 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ ቢያደርግም፣ በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. የወጣው የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሞቱትን ዜጎች ቁጥር ከ500 በላይ እንዳደረሰው አስታውሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ብቻ የሟቾች ቁጥር ከ500 በላይ ሊሆን ይችላል ማለታቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ይኼው ሪፖርት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለመግባት ያቀረቡት ጥያቄ በመንግሥት ይሁንታ አለማግኘቱንም አመልክቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓመቱ በኢትዮጵያ ከተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚጠቀሙት ኃይል ያልተመጣጠነ መሆኑ፣ ለነበሩት ተቃውሞዎችና አመፆች የሚሰጠው ምላሽ የዘፈቀደ እስር መሆኑ፣ ፖለቲካዊ ሥሌቶች ያሏቸው ክሶች መቅረባቸውና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ያለው ገደብ መቀጠሉ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስፍሯል፡፡
ሪፖርቱ የዘፈቀደ ግድያና እስር፣ የሰዎች መጥፋት፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ በፍርድ ቤት ሥራ ውስጥ ጣልቃ መግባት፣ የዜጎች የግል ሕይወት መደፈር፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ጥሰት በዓመቱ ከተከሰቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡
ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡