Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በጥጥ ኤክስፖርት ላይ ጥሎት የነበረውን ገደብ አነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በአገሪቱ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሚያስፈልጋቸውን ጥጥ በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ በአገር ውስጥ የጥጥ ምርት ኤክስፖርት ላይ ጥሎት የነበረውን ገደብ አነሳ፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የካቲት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ፣ ከዚህ በኋላ የጥጥ አምራቾች የተዳመጠ ጥጥ ኤክስፖርት ማድረግ ሲፈልጉ ከኢንስቲትዩቱ የገበያ ዋጋ ማረጋገጫ ማቅረብ ሳያስፈልጋቸው ኤክስፖርት ማድረግ ይችላሉ፡፡

‹‹ሁሉም ባንኮች በዚህ መሠረት እንዲፈጽሙ መመርያው በእናንተ (በብሔራዊ ባንክ) በኩል እንዲደርሳቸው እንጠይቃለን፤›› ሲል ኢንስቲትዩቱ የጥጥ ኤክስፖርት መፈቀዱን ለብሔራዊ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ አመልክቷል፡፡

በጥጥ ላይ የኤክስፖርት ገደብ የተጣለው በ2003 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በአገሪቱ በጥጥ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅቱ ሰጥቶ በነበረው የሥራ መመርያ፣ ጥጥ አምራቾች ያመረቱትን አገር ውስጥ ያሉ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በወቅቱ ካልገዟቸው የተዳመጠ ጥጥ ኤክስፖርት የማድረጊያ ዋጋው ከዓለም የመገበያያ ዋጋ አኳያ በኢንስቲትዩቱ እየተነፃፀረ እንዲቀርብና ኤክስፖርት እንዲደረግ ወስኖ ነበር፡፡

ነገር ግን ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች የጥጥ ግብይት ገደብ እንዲነሳ ተወስኗል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የጥጥ ግብይት ለገበያ ኃይሎች መተው የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በጥጥ ግብይት ሒደት ውስጥ ጥጥ አምራቾች ላመረቱት ጥጥ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገዥ ቢያጡ፣ መንግሥት ጣልቃ በመግባት በዓለም የጥጥ ዋጋ መገበያያ መሥፈርት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ግዥ እንዲፈጽም በመወሰኑ ነው፡፡ ሦስተኛው ምክንያት የጥጥ አምራቾች ጥጥ ኤክስፖርት ማድረግ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቀድ በተደጋጋሚ እየጠየቁ በመሆኑ እንደሆነ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የ2009 በጀት ዓመት የጥጥና የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሰባት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ከባለድርሻዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ የቀረበ ሪፖርት በ2008/2009 ምርት ዘመን በጥጥ የሚሸፈነውን መሬት 250 ሺሕ ሔክታር ማድረስ፣ ከዚህ እርሻ 500 ሺሕ ቶን ጥጥ ለማምረት ዕቅድ መያዙን አመልክቷል፡፡

ከዚህ ዕቅድ ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት 78 ሺሕ ሔክታር መሬት በጥጥ መሸፈኑን፣ ከ138 ሺሕ ቶን ጥሬ ጥጥ 51 ሺሕ ቶን የተዳመጠ ጥጥ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከተዳመጠው ጥጥ ውስጥ ግብይት የተፈጸመው ለ25 ሺሕ ቶን ብቻ ነው፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን በእርሻ ሥራ የተሰማራው ሳግላ ትሬዲንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪጅ አቶ ደመወዝ ካሳሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የሰጠውን ያህል ትኩረት ለጥጥ ዘርፍ አልሰጠም፡፡ ዘርፉ በተለይ የግብይት ሰንሰለቱ አድሎአዊ በመሆኑ ጥጥ አምራቾች ላመረቱት ምርት ተገቢውን ዋጋ በወቅቱ እያገኙ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ዘርፉ ከግብይት ገደብ ነፃ እንዲሆን በመደረጉ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደሚጠብቁ አቶ ደመወዝ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች