Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን በስም ማጥፋት ከሰሰ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን በስም ማጥፋት ከሰሰ

ቀን:

– ዩኒቨርሲቲው 200 ሺሕ ብር የሞራል ካሳ ጠይቋል

አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለዓመታት የኦዲት ሒሳብ አለማከናወኑን የሚያትቱ ዘገባዎች በ2007 እና 2009 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሁለት ጊዜ በመታተማቸው፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትንና የጋዜጣውን አዘጋጅ በስም ማጥፋት ክስ መሠረተባቸው፡፡ እንዲሁም የሐበሻ ወግ የተሰኘው የግል መጽሔት በራሱና አዲስ ዘመንን ዋቢ አድርጎ ለኅትመት ባበቃቸው ተመሳሳይ ዘገባዎች በስም ማጥፋት አሳታሚውና አዘጋጆቹ የሞራል ጉዳት ማድረሳቸውም በክሱ ተመልክቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት በጽሑፍ የመሠረተው የክስ ሰነድ እንዳመለከተው፣ ሁለቱ የኅትመት ተቋማትን ጨምሮ አምስት ተከሳሾች በሐሰት የኅትመት ሥራ የተቋሙን ስምና ዝና፣ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ሆነን ብለው አስበው ያደረጉትን ድርጊት ለማሳረምና ከሳሽ ላይ ለደረሰው የሞራል ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 41(2) መሠረት ክስ መሥርቷል፡፡

በተጠቀሰው የአዋጁ አንቀጽ መሠረት ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የዘረዘራቸው ተከሳሾች ጠቅላላ ድምሩ 200 ሺሕ ብር የሆነ የሞራል ካሳ እንዲከፍሉት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ክስ የተመሠረተባቸው አንደኛ ተከሳሽ ቴዲአብ መልቲ ሚዲያና ኢንተርቴይንመንት (የሐበሻ ወግ መጽሔት) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ከፍተኛ አዘጋጅ አቶ ዮናስ ወልደሰንበት፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ዋና አዘጋጅ ወ/ሮ ጽጌሬዳ ገብረ ማርያም፣ አራተኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (አዲስ ዘመን ጋዜጣ)፣ አምስተኛ ተከሳሽ አቶ አጎናፍር ገዛኸኝ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ የስም ማጥፋት ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነሐሴ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲውን አስመልክቶ፣ ‹‹ለአምስት ዓመታት ኦዲት ያልተደረገ ተቋም››፣ እንዲሁም ኅዳር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ‹‹የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስድስት ዓመታት የኦዲት ሪፖርት አይታወቅም›› የሚሉ ዘገባዎችን ለኅትመት በማብቃቱ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

አምስተኛ ተከሳሽ በተጠቀሱት ሁለቱ ዘገባዎች ዩኒቨርሲቲው ኦዲት ለማስደረጉም ሆነ ስላለማስደረጉ ሳያረጋግጡና ምንም ዓይነት መረጃ ሳይኖራቸው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴና የፌዴራል ዋና ኦዲተር አመራሮችን የዘገባ ምንጭ በማድረግ ያልተጠቀሰ መረጃን በመያዝ ሆን ብሎ ተቋሙን በሕዝብ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ለማሳጣት ከአሳታሚው ድርጅት ጋር በመተባበር ባወጡት የኅትመት ውጤት፣ በከሳሽ ላይ ከፍተኛ የህሊና ጉዳት ማድረሳቸው በክሱ ጠቅሷል፡፡

በተለይ አምስተኛ ተከሳሽ አቶ አጎናፍር የከሳሽን ስም ሆን ብለው በሐሰት የኅትመት ጽሑፍ ለመጉዳት ሲሠሩ እንደቆዩ የዩኒቨርሲቲው ክስ ያስረዳል፡፡

እንዲሁም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከሳሽን አስመልክቶ ይኸው ክስ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ዮናስ ወልደሰንበትና ሦስተኛ ተከሳሽ የሐበሻ ወግ መጽሔት አዘጋጅ ወይዘሮ ጽጌረዳ፣ ኅዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በሳምንታዊ መጽሔት ዕትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ ምርመራ ለአምስት ዓመታት አስደርጎ እንደማያውቅ፣ ነሐሴ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. እና ኅዳር 7 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ለጽሑፋቸው ቀኑ ባልተጠቀሰ ጊዜ ማለትም የካቲት 2007 ዓ.ም. ከ2,700 አልጋዎች ውስጥ 750 አልጋዎች ለተማሪዎች ሳይተላለፉ በወር 400 ብር በአጠቃላይ ሲሰላ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በድብቅ ለተማሪዎች በማከራየት ግለሰቦች ኪስ ውስጥ እንደሚገባ በውሸት ባዘጋጁዋቸው ዘገባዎቻቸው በሐበሻ ወግ መጽሔት የፊት ገጽ ታትሞ እንዲወጣ አድርገዋል ይላል፡፡

በተጨማሪም ሦስተኛ ተከሳሽ (ወይዘሮ ጽጌረዳ) በሁለተኛ ተከሳሽ ተቀነባብሮ የቀረበውን የውሸት ዘገባ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በዩኒቨርሲቲው በድብቅ አልጋ እየተከራየ የግለሰቦች ኪስ ገንዘብ እንደሚገባ የወጣ ዘገባ ስለመኖሩና አለመኖሩ ሳያረጋግጡ፣ በአንደኛ ተከሳሽ መጽሔት ላይ እንዲወጣ ከመደረጉ በፊት ማረጋገጥ ሲገባቸው የአዘጋጅነት ሙያዊ ተግባራቸውን ባለመወጣታቸው፣ በከሳሽ ላይ ከፍተኛ የሞራል ጉዳት እንዳደረሱ ተጠቅሷል፡፡

የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2044 እና ተከታዮቹ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በመጥቀስ ከሳሽ መብቱን ለማስከበር ወደ ክስ ለመግባት መገደዱንም አመልክቷል፡፡ በመሆኑም ሁለቱም የሚዲያ ተቋማት በየኅትመቶቻቸው ላይ ያወጧቸውን አርመው እንዲያሳዩ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡ የስም ማጥፋትና ማጉደፍ ደርሶብኛል ላላቸው በደሎች ሁሉም ተከሳሾች እንደድርጅቶቻቸው ቅደም ተከተል መሠረት በተናጠልና በጋራ ከሁለቱም ወገኖች የ100 ሺሕ ብር በድምሩ 200 ሺሕ ብር የሞራል ካሳ እንዲከፈለው በክሱ ጨምሮ ጠይቋል፡፡

ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የተዘረዘሩት ሁሉም ተከሳሾች ለቀረበባቸው የፍትሐ ብሔር ክስ የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የጽሑፍ መልስ እንዲያቀርቡ መጋቢት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ በአካል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የጽሑፍ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...