Monday, February 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አስፈሪው ድርቅና እያገረሸበት ያለው የኑሮ ውድነት ያሳስባሉ!

በምሥራትና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች እንደገና ያገረሸው ድርቅ 5.6 ሚሊዮን ዜጎችን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል፡፡ ዘንድሮም የበልግ ዝናብ በመስተጓጎሉ ሳቢያ ድርቁ ከፍተኛ የሆነ የውኃና የግጦሽ እጥረት በመፍጠሩ እንስሳት እየሞቱ ነው፡፡ ድርቁ የፀናባቸው ወገኖችም ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡ በተለይ በሕፃናት፣ በነፍሰ ጡሮችና በሚያጠቡ እናቶች ላይ አደጋ እንዳይፈጠር ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም፣ የሚፈለገው ዕርዳታና እየቀረበ ያለው መጣጣም አልቻሉም፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ያጋጠመው ድርቅ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ቢያጠቃም፣ በመንግሥትና በረድኤት ድርጅቶች ርብርብ የዜጎችን ሕይወት መታደግ ተችሏል፡፡ የአገሪቱንም ችግር የመቋቋም አቅም አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ድርቁ ቶሎ ቶሎ ሲመላለስና የለጋሾች እጅ በሚፈለገው መጠን አልፈታ ሲል ለአገሪቱ ከፍተኛ ፈተና ነው፡፡ ይህ ፈተናም ከወዲሁ መታየት ጀምሯል፡፡ በጣም ያሳስባል፡፡ ያስፈራል፡፡

በቅርቡ በወጣው መረጃ መሠረት በምሥራቅ አፍሪካ 12.8 ሚሊዮን ሰዎች ፅኑ የሆነ የምግብ ችግር አጋጥሟቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ 5.6 ሚሊዮን፣ ኬንያ 2.7 ሚሊዮን፣ ሶማሊያ 2.9 ሚሊዮን፣ እንዲሁም ኡጋንዳ 1.6 ሚሊዮን ዜጎቻቸው አስቸኳይ ዕርዳታ ይፈልጋሉ፡፡ በሶማሊያ ረሃብ መግባቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በሁሉም አገሮች ሕፃናት በአልሚ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው፡፡ ድርቅ ሲያጋጥም በራስ አቅምም ሆነ በለጋሾች ድጋፍ ሕይወት እንዳያልፍ መረባረብ ዋነኛው ትኩረት ቢሆንም፣ ድርቅን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚቻልበት ተግባር ላይ መሰማራት ግን ተገቢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ድርቅ በተደጋጋሚ ለምን ይመላለሳል? የሚለውጥ ጥያቄ ዕድሜ ጠገብ ነው፡፡ ነገር ግን ለዓመታት ምላሽ አላገኘም፡፡ ድርቅን የመቋቋም አቅም መገንባትና በፈተና ጊዜ ማሳየት ከተቻለ፣ ምንም እንኳ በተፈጥሮ ክስተቶች ሳቢያ ድርቅ የሚያጋጥምበት አጋጣሚ ቢኖርም በተደጋጋሚ መመላለሱን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ አገሪቱ በግብርናው መስክ የምትከተለው ፖሊሲ ችግር ካለበት በሚገባ በማጥናት የማያዳግም ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ሌሎች ተያያዥ የፖሊሲና የስትራቴጂ ችግሮች ካሉም እንዲሁ መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡ ለአገርም ሥጋት ነው፡፡

አሁን እየወጡ ባሉ ሪፖርቶች መሠረት ድርቅ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው የምሥራቅና የደቡብ አርብቶ አደሮች አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ቢኖርም እንኳ ከመደበኛው በታች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይኼ ክስተት ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት አሥጊ ነው፡፡ ከፊል አርብቶ አደር በሆኑ አካባቢዎች ለእርሻቸው ዝናብ የሚጠብቁ ዜጎች መሬት ጦሙን ያድራል፡፡ ውኃና የግጦሽ ሣር ይጠፋሉ፡፡ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ድጋፍ አሁን ካለው ፍላጎት ጋር ስለማይጣጣም፣ ለመንግሥትም ሆነ ለረድኤት ድርጅቶች ፈተና ይሆናል፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎም የዜጎች ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በኦሮሚያ ክልል ከ117 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ላይ የነበረ ሰብል በውርጭ ወድሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ163 ሺሕ በላይ ቤተሰቦች ለችግር ይጋለጣሉ፡፡ ይህ ለአገር ትልቅ ችግር ነው፡፡ በዚህ ላይ ከሶማሊያ ረሃቡን በመሸሽ በየቀኑ በአማካይ 70 ስደተኞች ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ከ800 ሺሕ በላይ ስደተኞችን አስጠልላለች፡፡ ይኼ ሁሉ ሲደራረብ ድርቁን አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ በጣም ያሳስባል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የችግር ማጥ ውስጥ ለመውጣት በጥናት ላይ የተመሠረተ ዘለቄታዊ መፍትሔ ግድ ይላል፡፡

በሌላ በኩል አሁንም የሚያገረሸው የኑሮ ውድነት የአገሪቱ ዜጎች የራስ ምታት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በመላ አገሪቱ ምክንያት አልባ የሆኑ የዋጋ ንረቶች የዜጎችን ሕይወት እየተፈታተኑ ነው፡፡ ወትሮም የተበላሸው የግብይት ሥርዓት አሁንም መረን በመለቀቁ ብቻ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሕዝቡን እየተጫወተበት ነው፡፡ በግብይቱ ውስጥ የፍላጎትና የአቅርቦት መስተጋብር ጠፍቶ በዘፈቀደ ስለሚሠራ ሠራተኛው ሕዝብ በኑሮ ውድነት ይጠበሳል፡፡ የሠራተኛ ደመወዝ ጭማሪ ሲሰማ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከገበያው እንዲጠፉ ይደረግና ሰው ሠራሽ የዋጋ ጭማሪ ይፈጠራል፡፡ ገበያው በደላሎችና በሕገወጥ አቀባባዮች ስለሚመራ ሸቀጦችን መደበቅ፣ የተጋነነ ዋጋ መጨመር፣ ጥራታቸውን ማጓደል፣ ሚዛኖችን ማዛባትና የመሳሰሉት እኩይ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ መንግሥት ገበያው ውስጥ ገብቶ ዋጋ መወሰን በሕግ የማይፈቀድለት ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የትርፍ ህዳግ (Profit Margin) ማውጣት ይችላል፡፡ ይህ የሚመለከተው ተቋም እያንቀላፋ በመሆኑ ምክንያት ብቻ የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ ሆኗል፡፡ ከመሬት ተነስቶ ዕርምጃ እንወስዳለን ከማለት በፊት በሕግ የተደገፈ ሥራ ማከናወን ይጠቅማል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር በተለይ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪን አስመልክቶ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የታዩ ሕገወጥ የዋጋ ጭማሪዎች ለመከላከል መነሳቱን ጠቁሟል፡፡ በአጥፊዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድና የዕርምጃ አወሳሰድ ሥርዓት መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ በማተኮር በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በባለሙያዎች ማስጠናትና ለማያዳግም ዕርምጃ የሚረዱ ውሳኔዎች ላይ መድረስ ተገቢ ነው፡፡ የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ሥውር እጃቸውን ያስገቡ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ገበያውን በቡድን በመቆጣጠር እንደፈለጉ የሚወጫቱበት ናቸው፡፡ ኔትወርካቸው በጣም ሰፊና በሙስና ባለሥልጣናትን ሳይቀር የሚቆጣጠሩ በመሆናቸው፣ ጠንካራና ቁርጠኛ የሆነ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ለይስሙላ የሚደረጉ ጥናቶችና ሥር ነቀል ለውጥ የማያመጡ ውሳኔዎች በኑሮ ውድነት እየተንገበገበ ላለው ሕዝብ አይጠቅሙም፡፡ ችግር ፈጣሪዎችን በማሳሰቢያና በለብ ለብ የዘመቻ ማስፈራሪያዎች ማስታገስ አይቻልም፡፡ ይልቁንም ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት አደብ እንዲገዙ መደረግ አለበት፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሕዝብ ብሶትና ቁጣ ይቀሰቀሳል፡፡ ሌላ ችግር ይፈጠራል፡፡

ሕዝብ በከተሞች በቤት ኪራይ ዋጋ ንረት መከራውን ያያል፡፡ ከወር ወር ለመዳረስ አበሳውን ይቆጥራል፡፡ በዚህ ላይ በየደረሰበት እንደ እሳት የሚጋረፍ የኑሮ ውድነት አቅሉን ያስተዋል፡፡ ልጆችን አብልቶ፣ አጠጥቶና አልብሶ ትምህርት ቤት መላክ የብዙ ወላጆች ሰቆቃ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ላይ ትምህርት ቤቶች የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ፡፡ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረቶች በየአቅጣጫው ሲሠራጩ የመኖር ትርጉሙ ለዛውን ያጣል፡፡ በውጭ ምንዛሪ መጥፋትና በጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ማነስ እየተሳበበ ደግሞ ራሱን የቻለ ዘረፋ ይካሄዳል፡፡ መንግሥት በመጀመሪያ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን መሠረታዊ ችግር ለማወቅ መነሳት አለበት፡፡ ይህ መነሳሳት ደግሞ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎችና በሙያው በተካኑ አጥኚ ድርጅቶች መታገዝ ይገባዋል፡፡ በግዴለሽነትና ከአቅም በታች በሚጫወቱ ግለሰቦች ላይ መተማመን መቅረት አለበት፡፡ ራሳቸውን ለሙስና ባስገዙ ብልጣ ብልጦችም መጠለፍ አይገባም፡፡ የኑሮ ውድነትን የሚያመጡ መሠረታዊ ምክንያቶች መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም፣ አብዛኛው የሚታየው ግን ከሕገወጥነት ጋር የተያያዘው ነው፡፡ ይህንን ማስቆም አለመቻል ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ጠንቅ ነው፡፡ ሙስና የተንሠራፋበት የግብይት ሥርዓት ከአልባሌ ድርጊቶች ፀድቶ እንዲዘምንና ሸማቹ ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚፈለግ ከሆነ ሕገወጥነት ማብቃት አለበት፡፡ በአጠቃላይ ድርቁም ሆነ የኑሮ ውድነቱ እንደ አገር በጣም ሊያሳስቡ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...