Tuesday, December 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ በውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለሚሰማሩ ያለ ማስያዣ ብድር ለማቅረብ እየመከረበት ነው ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው የተቆፈሩ ጉድጓዶች ብክነት እየታየባቸው መሆኑ ተገለጸ

 በከርሰ ምድር የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለተሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ባለሙያዎች ለማሽነሪዎች መግዣ የሚሆን ብድር ያለ ተጨማሪ ማስያዣ ሊያገኙ የሚችሉበትን አሠራር ለመተግበር የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እየመከረ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና የማሽኖች ዋጋ ውድ የሚባል በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ውስን ናቸው ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለማሽኖች መግዣ ከባንክ ብድር ለማግኘት ተበዳሪዎች ከማሽኖቻቸው ውጪ ተጨማሪ ማስያዣ ስለሚጠየቁ፣ ባለሙያዎችም ሆኑ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ፈታኝ እንደሆንባቸው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንት የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአዳማ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተሳተፉ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ባለሙያዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ከብድር አቅርቦት ጋር ያለባቸውን ችግር በሰፊው ገልጸዋል፡፡ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎችም ማሽኖቻቸውን ብቻ በማስያዝ ያለ ተጨማሪ ማስያዣ ብድር ማግኘት የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ በባንኮች ጉዳዩን እየተፈተሹ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የከርሰ ምድር ውኃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ታደሰ በምክክር መድረኩ ላይ ብድርን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ በዘርፉ ለመሰማራት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ስለሚጠይቅ ጥቂት ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች እንጂ ሙያው ያላቸው አልሚዎች በብድር እንኳ በኢንቨስትመንቱ ውስጥ መሳተፍ አልቻሉም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በተለይ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን ጨምረው በኢንቨስትመንቱ (በከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ) ለመሰማራት ትልቅ ፈተና አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የመቆፈሪያ ማሽኖች ውድ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ለምሳሌ ከ500 እስከ 600 ሜትር ጉድጓድ መቆፈር የሚችል ማሽን ለመግዛት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

አክለውም ሥራው በቀላሉ ኪሳራ ሊያመጣ የሚችል ቢሆንም አትራፊም እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአንድ ጉድጓድ ከ60 እስከ 65 በመቶ ትርፍ ሊገኝበት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ግን ማሽኑ በቁፋሮ ላይ እያለ ተደርምሶበት ሊጠፋም የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን በመጥቀስ፣ አትራፊነቱንና ሥጋቱን ለማመላከት ሞክረዋል፡፡

 በነዚህና መሰል ምክንያቶች ባንኮች ማሽኑን ብቻ ይዘው ብድር ለመስጠት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በተለይ ንግድ ባንክ ማሽኖችን ወይም ሊብሬዎችን ብቻ በመያዝ ብድር መስጠት የሚችልበትን መንገድ ማጥናት ጀምሯል፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ የብድር አቅርቦቱን ለመጀመር ግን የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የዘገየ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙ ባለሙያዎች እንደገለጹትም፣ በጥልቅ የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮው የዓመታት ልምድና ዕውቀት ቢኖራቸውም፣ ከገንዘብ አቅም ውሱንነት ጋር በተያያዘ በራሳቸው አቅም ኢንቨስት አድርገው መሰማራት አለመቻላቸውን ነው፡፡ በአንፃሩ ዕውቀቱና ልምዱ ሳይኖራቸው ገንዘቡ ብቻ ስላላቸው በቁፋሮ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ተቀጥረው ለመሥራት ብቻ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ ደግሞ በባለሙያዎችና በባለሀብቱ መካከል ችግሮችን ማጫሩ ስለማይቀር፣ ብዙውን ጊዜ በከፍተኛ ወጪ የሚቆፈረው ጉድጓድ የታሰበውን ያህል የአገልግሎት ጥራት እንደማይኖረው የተናገሩት ባለሙያዎች፣ አልያም የአገልግሎት ዕድሜው ላይ እንከን እየፈጠረ መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

ከከርሰ ምድር ውኃ ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ‹‹አንገብጋቢ›› ከተባሉ ችግሮች መካከል፣  በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቀደም ብለው የተቆፈሩ ጉድጓዶች ከፍተኛ ወጪ ቢወጣባቸውም የሚፈልገውን ያህል አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም የውኃ ጉድጓዶች በአግባቡ አለመያዛቸውና በቂ መረጃና የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) የሌላቸው በመሆኑ፣ መልሶ ለመጠገንና ጥናት ለማካሄድ አስቸጋሪ አድርጎታልም ሲሉ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በአዳማው የምክክር መድረክ ላይ የመወያያ መነሻ ሐሳብ በማቅረብ በዘርፉ የዓመታት  ልምዳቸውን ካቀረቡ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት አቶ ሁሴን እንድሬ እንደገለጹት፣ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት ላይሰጡ ወይም የአገልግሎት ጊዜያቸው የሚጠበቀውን ያህል ሳይቆይ የተበላሹ የውኃ ጉድጓዶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም ባለሙያዎች ከዚሁ ችግር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች