Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ 40 ብር ደርሷል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሁለት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከስምንት እስከ 12 ብር ሲሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ቲማቲም ሰሞኑን ከ32 እስከ 40 ብር እየተሸጠ ነው፡፡  ለአንድ ኪሎ ቲማቲም የዚህን ያህል ዋጋ መሰጠቱ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ቢገለጽም፣ የዋጋው መወደድ ጊዜያዊ እንደሆነ እየተገለጸም ነው፡፡

በአገሪቱ በከፍተኛ የቲማቲም አምራችነታቸው ከሚታወቁ አካባቢዎች አንዱ ከሆነው ከመቂ ባቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ሰሞኑን በከፍተኛ ደረጃ የቲማቲም ዋጋ ሊጨምር የቻለው የምርት እጥረት በመፈጠሩ ነው፡፡

150 የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የያዘው የመቂ ባቱ ዩኒየን ከፍተኛ የቲማቲም አምራቾች የሚገኙበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው መቅረብ ያለበትን ያህል ቲማቲም ለማቅረብ ያልተቻለው በቲማቲም በሽታና በአየር ንብረት ለውጥ ምርቱ ላይ ተፅዕኖ ስላሳደረ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በመቂና በአካባቢው ባሉ አምራቾች የቲማቲም እርሻ ላይ ከአንድ ወር በፊት ቱታ አብሱሉታ የተባለው የቲማቲም በሽታ ያስከተለው ጥፋት ምርቱን ቀንሶታል፡፡ ከበሽታው ከተረፈው ምርትም የተወሰነው ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተፈጠረ ውርጭ ምክንያት፣ በቂ ምርት ለገበያ ባለመቅረቡ የተፈጠረ ችግር ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በመቂና አካባቢው ያሉ አምራቾች በጅምላ ዋጋ አንዱን ኪሎ ቲማቲም አራት ብር ድረስ ይሸጡ እንደነበር የሚያስታውሱት የዩኒየኑ ኃላፊዎች፣ አሁን ግን እጥረቱ የጅምላ መሸጫው ዋጋን ሳይቀር ከ25 ብር እስከ 30 ብር ሰቅሎታል፡፡ ቲማቲም ዋጋ በዚህን ያህል ዋጋ የተሸጠበት ጊዜ እንዳልነበርም ገልጸዋል፡፡ ዩኒየኑ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ላሉ ትላልቅ ተቋማት በየዕለቱ ለማቅረብ የተዋዋለውን ቲማቲም አሁን ባለው የገበያ ዋጋ እየገዛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህ ችግር ግን ጊዜያዊ መሆኑን የሚጠቁሙት የዩኒየኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ አዲስ የሚደርሰው የቲማቲም ምርት በ15 ቀን ውስጥ ስለሚወጣ ዋጋው ይወርዳል ተብሏል፡፡

ሆኖም ግን ከመቂ አካባቢ ውጭ ያሉ የቲማቲም አምራቾች የገጠማቸው ችግር ባይኖርም፣ እየሸጡ ያሉበት ዋጋ አጋጣሚውን በመጠቀም ዋጋው እንዲሰቀል ምክንያት እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች