አቶ ዘውዱ ወንድም፣ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን፣ የትምህርትና የሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር
የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ ከአምስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የሦስተኛ ወገን መድን ላይ አተኩሮ የተቋቋመው ኤጀንሲው በሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ በኩል የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ይሠራል፡፡ ሆኖም ችግሮች አሁንም ይስተዋላሉ፡፡ ኤጀንሲው የሚስትዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን፣ የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ዘውዱ ወንድም፣ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ከአምስት ዓመት በፊት የሦስተኛ ወገን መድን አስገዳጅ ሲደረግ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች መድኑን ለመግባት ብዙም ፍላጎት አላሳዩም ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ አመለካከት ተቀይሯል?
አቶ ዘውዱ፡- ኤጀንሲው በተለይ ወደ ተግባር ከገባ ከአምስት ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በእያንዳንዱ ዘርፎች ለውጦች ይታያሉ፡፡ በ2004 ዓ.ም. ላይ ካሳ መክፈል ስንጀምር የነበረውንና አሁን የደረሰበትን ስናይ መሻሻሎች አሉ፡፡ በፊት በነበሩ ሕጐችም አንድ ተሽከርካሪ ጉዳት ሲያደርስ አሽከርካሪው ተይዞና ተጠይቆ ተጐጂውን የማሳከምና የማስካስ ሥራዎች የመድን ፈንድን አስመልክቶ በ559/2000 የወጣውና በኋላም በ799/2005 የተሻሻለው ነበር፡፡ አዋጅ መውጣቱ ያስገኘው ጠቀሜታ ለተሽከርካሪ ባለቤቱም ነው፡፡ በፊት በነበረው አሠራር ጉዳት አድራሹ ይያዛል፣ ክስ ይመሠረትበታል፣ ይወሰንበታል፡፡ ለሕክምናና ለካሳ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህ ተጐጂው ሕክምናና ካሳ እንዲያገኝ ሲያደርግ፣ ጉዳት አድራሹ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ጉዳት በማድረሱ ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህም የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ያደርግ ነበር፡፡ አዋጁ መውጣቱ የተሽከርካሪ ባለቤቶች በዓመት አንድ ጊዜ በሚያወጡት ተመጣጣኝ የአረቦን ክፍያ መሠረት ዓመቱን በሙሉ እነሱን ተክቶ ኡንሹራንስ ኩባንያው እንዲከፍላቸው ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ወደ መጀመሪያው አካባቢ ይህን ካለመረዳት ብዙ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ አደጋ ለማናደርሰው በየዓመቱ ለምን እንከፍላለን የሚሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን አደጋ ቢያጋጥመንስ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ባጃጅ ወይም ባለሦስት ጐማ ተሽከርካሪ በዓመት ለሦስተኛ ወገን የሚያዋጣው ወደ 348 ብር ነው፡፡ በከፈለበት ዓመት ውስጥ ድንገት አደጋ ቢያጋጥም የኢንሹራንስ ኩባንያው በአንድ ሰው ላይ ለሚደርስ የሞት አደጋ ከ5 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ብር ካሳ ይከፍላል፡፡ በአካል ላይ ለሚደርስ ጉዳት እስከ 40 ሺሕ ብር ካሳ ይከፍላል፡፡ በንብረት ላይ ለሚደርስ እስከ 100 ሺሕ ብር ይከፍላል፡፡
ሪፖርተር፡- የሕክምናውስ?
አቶ ዘውዱ፡- ሁለት ዓይነት ሕክምና አለ፡፡ አንደኛው አስቸኳይ ሕክምና ሲሆን ሦስት ቦታዎች ላይ ይሰጣል፡፡ አደጋው በደረሰበት ቦታ፣ ወደ ሕክምና በሚጓጓዝበት ጊዜ በአምቡላንስ ውስጥና ሆስፒታል ደርሶ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ የሚሰጥ ሕክምና አስቸኳይ ሕክምና ይባላል፡፡ ይህ ሕይወትን ለማቆየት ለአልኮል፣ ለኦክስጅንና ለሌሎችም የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምናዎች ሲሆን እስከ 2 ሺሕ ብር በሚደርስ መታከም ይቻላል፡፡ ሁለተኛው ጉዳቱ ከፍተኛ ሆኖ ተመላልሶ ወይም ተኝቶ እንዲታከም ሐኪሙ በሚያዝበት ጊዜ አስቸኳይ ሕክምና መሆኑ ያበቃል፡፡ ተጐጂው ለካሳ ከሚሰጠው ገንዘብ ላይ እየታሰበ ቋሚ ሕክምና የሚከታተልበት አሠራር አለ፡፡ መድን መግባቱ ይህን ጥቅም ስለሚሰጥ አሁን ላይ ከአስገዳጅነቱ ባለፈ ይጠቅመናል በሚል ብዙ መሻሻሎች አሉ፡፡ ይህ ማለት ግን አመለካከቱ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፎ፣ ሁሉም አስፈላጊነቱን አምኖበታል ማለት አይደለም፡፡ የተሽከርካሪ ባለንብረት መድን ገብቶም አተገባበሩ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፡፡ የአስቸኳይ ሕክምና ወጪን ለመሸፈን ከኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ከኤጀንሲው በአገሪቱ ይኖራሉ የሚባሉ ተጐጂዎችን መሠረት አድርጐና ገንዘብ ተዋጥቶ፣ የክልል ጤና ቢሮዎች በከፈቱት አካውንት ገብቶላቸዋል፡፡ ሆኖም ከክልል ክልል አተገባበሩ ላይ ልዩነቶች አሉ፡፡ የተሽከርካሪ ባለቤት የሦስተኛ ወገን መድን ገብቶ እያለ አደጋ ሲያደርስ ከኪሱ ከፍሎ የሚያሳክምበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለሆነም የተሽከርካሪ ባለንብረቶች መድን መግባታቸው የሰጣቸው ጠቀሜታ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ እውነታም አላቸው፡፡ አሠራሩን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው ሪፖርት ስታቀርቡ አንዳንድ ክልሎች በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች እንዲያውሉ የተሰጣቸውን ገንዘብ አለመጠቀማቸው ተነስቷል፡፡ ችግሩ ምን ነበር?
አቶ ዘውዱ፡- ሁሉም ክልሎች የሦስተኛ ወገን መድንን ሙሉ ለሙሉ ይተገብራሉ ወይም አይተገብሩም ማለት አይቻልም፡፡ ታዳጊ ያልሆኑ ክልሎች ተልዕኮ ወስደዋል፡፡ አፈጻጸሙ ከቦታ ቦታ ልዩነት ቢኖረውም ሕክምና ተቋማት አስቸኳይ ሕክምናውን ከሰጡ በኋላ ቅጽ ሞልተው ገንዘባቸው እንዲመለስ ሲጠይቁ ገንዘቡን መመለስ ጀምረዋል፡፡ እያንዳንዱ የተሽከርካሪ አደጋ ተጐጂ በየትኛውም ጤና ተቋማት ሄዶም ያለምንም ወጪ ሕክምና የማግኘት መብት እንዳላቸው እየተረዱ ነው፡፡ የሕክምና ተቋማትም ገንዘቡን እንዴት ማስመለስ እንደሚችሉ ሙሉ ግንዛቤና በራስ መተማመናቸው ዝቅተኛ ቢሆንም ይህንን ሕክምና በነፃ መስጠት እንዳለባቸው ተረድተው በነፃ የመስጠት ሁኔታዎች አሉ፡፡ ሆኖም ታዳጊ ክልሎች ሆነውም ገንዘቡን ያስቀመጡ፣ አዋጁን በቅጡ የማይተገብሩ አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ዘውዱ፡- የግንዛቤ ክፍተት አለ፡፡ አሳማኝ ምክንያት ባይሆንም አደጋ ብዙ ጊዜ አይከሰትም የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል በሆስፒታሎች በኩል መተማመን አልተፈጠረም፡፡ ሕክምናውን ሰጥተን ቅጹን ሞልተን ገንዘቡን ማስመለስ እንችላለን ብለው መተማመን አላዳበሩም፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን ገንዘብ ለማስመለስ ፖሊስና ሕክምናውን የሰጠው ተቋም ቅጽ መሙላት አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ አደጋ ሲደርስ ፖሊስ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ ግን ሁልጊዜ እውነት አይሆንም፡፡ በመሆኑም የተጐዳውን ሌሎች ሰዎች ወደ ሕክምና ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ ሌላም ሰው ቢወስደው ገንዘቡን ማስመለስ ይቻላል፡፡ በፖሊስ በኩል አደጋው ሲከሰት አልነበርኩም፣ ጤና ተቋሙ ያወጣውን ብር ለማስመለስ ቅጹን አንሞላም የሚሉ አሉ፡፡ አደጋ ቦታም ተገኝቶም ቢሆን በዕለቱ አደጋው መድረሱን ቅጹ ላይ ሞልቶ ሕክምና እንዲያገኝ ከረዳ በኋላ ሕክምናው አልቆ ጤና ተቋሙ ያመጣውን ወጪ ለማስመለስ በሚሞላው ቅጽ ላይ ፖሊስም እንዲሞላ ሲጠራ አለመገኘት አለ፡፡ ገንዘቡ በፍጥነት እንዳይመለስ ጤና ተቋማት ፖሊሲን፣ ፖሊስ ጤና ተቋማትን የማሳሰብ ነገር አለ፡፡ ይህ የሚታየው ወደ ሥራ የገቡት ክልሎችና ተቋማት ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ክልሎች ላይ ደግሞ ገንዘቡን ባንክ አስቀምጠው የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስን ተግባራዊ ያላደረጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ኢንሹራንስ አልጠቀመኝም እንዲሉ ረድቷል፡፡
ሪፖርተር፡- የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ከፍለው ነገር ግን አደጋ ባጋጠመ ጊዜ ተጠቃሚ የማይሆኑበት ሁኔታ በአንዳንድ ክልሎች ታይቷል፡፡ አሠራሮች እንዲቀየሩ ምን አድርጋችኋል?
አቶ ዘውዱ፡- የኛ ባለድርሻዎች አብረውን መሥራት እስካልቻሉ ኤጀንሲው የቱንም ያህል ቢፍጨረጨር አንድ ስንዝር መራመድ አይችልም፡፡ ለምሳሌ የአስቸኳይ ሕክምናን በሚመለከት ኤጀንሲው ገጭተው ባመለጡና መድን ሽፋን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች የተጐዱ ወገኖችን መሠረት በማድረግ፣ 17ቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ ባላቸው ደንበኞች ልክ ገንዘብ እናዋጣለን፡፡ ኤጀንሲውና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያዋጡት ገንዘብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በከፈተው አካውንት ገቢ ተደርጓል፡፡ ክልሎች ምን ያህል ተጐጂ ይኖራቸዋል በሚል ተሰልቶ ገንዘቡ ለአዲስ አበባና ለክልሎች ገቢ ተደርጓል፡፡ ኤጀንሲው በሕክምና ተቋማት ሥራ ስለማይገባ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለው መዋቅር ታች ድረስ ወርዶ ካልሠራ አንድ ስንዝር መራመድ አይቻልም፡፡ ገንዘብ ማስቀመጡ የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ ለተጐጂዎች መዋል አለበት፡፡ ኤጀንሲው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ክትትል እያደረገ ያሉትን ክፍተቶች ያሳያል፡፡ በዚህ ዓመትም ሁሉም ክልሎች ላይ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ችግር ምንድን ነው ብለን ዳሰሳ አድርገናል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ገቢ የተደረገን ብር አደጋ ቢኖርም ጥቅም ላይ ያላዋሉ አሉ፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ሥራው ላይ ስላልገቡ በ2007 ዓ.ም. ገቢ ተደርጐላቸዋል የተባለው ብር ገቢ አለመሆኑ የታወቀው በዚህ ዓመት ነው፡፡ ገቢ የተደረገውም ከሁለት ዓመት በኋላ ነው፡፡ አዋጁ የኅብረተሰብ ጥያቄን የሚመልስ፣ ሰዎች ጉዳት ተሸክመው ለሌላ ውጣ ውረድ እንዳይዳረጉ የሚያግዝ ስለሆነ የሚመለከተው በሙሉ ተባብሮ መሥራት አለበት፡፡ ኤጀንሲው ችግሮችን ለይቷል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ 23 የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን አዘጋጅተናል፡፡ ከጤናውም ሆነ ከኢንሹራንሱ የሚመጡ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ላይ እንወያያለን፡፡ ነገር ግን ተሽከርካሪዎች እስከገጠር ቀበሌ ከመግባታቸው አኳያ ሌላው ባለድርሻ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ኤጀንሲው ብቻውን ለውጥ አያመጣም፡፡ ጥሩ መግባባቶችና ለውጦች ቢኖሩም ብዙ መሥራት ይጠይቀናል፡፡
ሪፖርተር፡- ጤና ተቋማት ያከሙበትን ብር ለማስመለስ የሚሞሉትን ቅጽ ፖሊስም መሙላት ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም ጤና ተቋማት ገንዘባቸውን ለማስመለስ በሚሞሉት ቅጽ አንዳንዴ የፖሊስን ትብብር ማግኘት አለመቻላቸው እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ምን ስልት ዘረጋችሁ? ፖሊስ በሌለበት መንገደኞች ተጐጂዎችን ሆስፒታል ቢያደርሱ እነሱን እማኝ ማድረግስ ይቻላል?
አቶ ዘውዱ፡- ፖሊስ ራሱ በባለቤትነት ሥራው የኔ ነው ብሎ መውሰድ አለበት፡፡ አደጋው ላይ የግድ መገኘት የለበትም፡፡ ሆኖም አደጋውን መመዝገቡ አይቀርም፡፡ በአደጋነት እስከተመዘገበ ድረስ፣ ጤና ተቋማት ለተጐጂው ያወጡትን ሕክምና ወጪ ተመላሽ እንዲያደርጉ ለሕክምና ተቋማቱ ማረጋገጫ መስጠት አለበት፡፡ ፖሊስ ካልመጣ ተጐጂ ከቦታው መነሳት የለበትም የሚል አሠራር የለንም፡፡ ተጐጂውን ይዞ የሄደ ሰው ተጐጂው ሕክምና እንዲያገኝ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ተቋሙ ያከመበትን ገንዘብ ለማስመለስ ግን ፖሊስ የሚፈርመው ነገር ካለ ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ አደጋው እስከተመዘገበ ድረስ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ላይ ጥሩ ተሞክሮ አለ፡፡ የኦሮሚያን ልምድ ለማለዋወጥም እየሠራን ነው፡፡ በአስቸኳይ ሕክምናና በአዋጁ ላይ በአብዛኞቹ ክልሎች የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ አዘጋጅተናል፡፡ ሥልጠናም ተሰጥቷል፡፡ እስከ ወረዳ ድረስ ሁሉም በባለቤትነት ወስዶ መሥራትም አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ጤና ተቋማት አይከፈለንም በሚል ፍርኃት የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ለመስጠት አይፈልጉም ነበር፡፡ ይህ አመለካከት አሁን ላይ ተቀይሯል?
አቶ ዘውዱ፡- መሻሻሎች አሉ፡፡ በ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያው ስድስት ወር ውስጥ ከ100 በላይ ጤና ተቋማት ብር እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የግል ሕክምና ተቋማት ላይ ከሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ መሻሻልም አለ፡፡ ይህ የሚያሳየው ወደ ሥራው እየተገባ መሆኑን ነው፡፡ ወደ ሥራ ባልተገባበት ጊዜ ችግሮችን እንኳን ለመለየት ተቸግረን ነበር፡፡ አሁን ብዙ ሕክምና ተቋማት አዋጁን ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ወደ ሥራ ያልገባ ክልል ብለን ከጥቂት ወራት በፊት ሪፖርት አቅርበን ነበር፡፡ ሆኖም ባለፈው አንድ ወር 60 ለሚሆኑ የተሽከርካሪ አደጋ ተጐጂዎች አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ ወደ ሥራው እየገቡ ስለመሆኑም ማሳያ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ገንዘቡ ለጤና ተቋማት ተመላሽ የሚደረገው ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነበር፡፡ ይህም ችግሮች ነበሩበት፡፡ አሁን ያለው አሠራር ምን ይመስላል?
አቶ ዘውዱ፡- ባልታወቀና መድን በሌለው ተሽከርካሪ ይጐዳሉ ተብሎ ለሚታሰበው ኤጀንሲው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ አዋጥቷል፡፡ 17 ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባላቸው ደንበኛ ልክ አዋጥተዋል፡፡ በጤና ጥበቃ አካውንት ተከቶ እያንዳንዱ ክልል ምን ያህል ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል የሚለው ተሰልቶ የየክልልና የከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች አካውንት እንዲከፍቱ ተደርጐ ገንዘቡ ተልኮላቸዋል፡፡ አንድ የሕክምና ተቋም የግልም ሆነ የመንግሥት፣ በመኪና አደጋ ለሚጐዱ ወገኖች የሚሰጠውን አገልግሎት በገንዘብ አስልቶ ቅጽ በመሙላት ቅርብ ላለ ጤና ጽሕፈት ቤት ይሰጣል፡፡ አሥር ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ገንዘቡ እንዲተካም ይደረጋል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር መሄድ አያስፈልግም፡፡ ሦስተኛ ወገን ስንል ካሳ ለመክፈል እንጂ አስቸኳይ ሕክምና ለመስጠት አይደለም፡፡ በፊት በነበረው አዋጅ 559/2000 ኢንሹራንሶች ይከፍሉ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ከመሆኑ አንጻር በርካታ ክፍተቶች ስለነበሩበት እንደገና አዋጁ ተሻሽሎ 799/2005 ከ2005 ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በፊት በነበረው አዋጅ አንድ የሕክምና ተቋም አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ጉዳት ላደረሰው ተሽከርካሪ ሽፋን የሰጠው ኢንሹራንስ የትኛው ነው ብሎ፣ ቅጹን ሞልቶ ከ17ቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ አንዱ መሄድ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ጉዳት ያደረሰው ተሽከርካሪ ያልታወቀ ከሆነ ብሩን ለማስመለስ መድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ መምጣት ይጠበቅ ነበር፡፡ አሁን ገንዘቡ እስከ ክልል ጤና ቢሮዎች አካውንት ስለገባ ቅጹን ሞልተው ወረዳ ጽሕፈት ቤት በመሄድ ገንዘቡ በአጭር ጊዜ እንዲመለስ ይደረጋሉ፡፡ አዲስ አበባ ላይም ጤና ቢሮ ገቢ የተደረገ ገንዘብ አለ፡፡ የግልም ሆነ የመንግሥት ጤና ተቋማት፣ አስተዳደሩ የሚያስተዳድራቸው ከሆኑ ከጤና ቢሮው፣ ፌዴራል የሚያስተዳድራቸው ደግሞ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስመለስ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ካሳን በተመለከተስ?
አቶ ዘውዱ፡- ካሳ ሁለት ቦታ ይከፈላል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ ሦስት መሠረት ማንኛውም ተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ሊኖረው ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ እውነት አይሆንም፡፡ ኢንሹራንስ የገቡ ተሽከርካሪዎች ጉዳት ካደረሱ ኢንሹራንሳቸው እነሱን ተክቶ ካሳ ይከፍላል፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተሽከርካሪዎች ጉዳት አድርሰው የሚሰወሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ስለዚህ በተሰወረ ተሽከርካሪ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ኤጀንሲው ይከፍላል፡፡ ተሽከርካሪው መድን ያልገባ ከሆነም የሚከፍለው ኤጀንሲው ነው፡፡ እኛ የምንክሰውን ከፖሊስ ጋር በመተባበር ተሽከርካሪው እንዲያዝ ተደርጐ ተጠያቂ ይደረጋል፡፡ ገንዘቡን ይከፍላል፣ ገጭቶ በማምለጡ በሌሎች ወንጀሎች በሚመለከተው አካል ተጠያቂ ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ካሳ ክፍያ ላይ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ አንዳንዶችም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር መመላለስን በመጥላት ካሳቸውን ሳይወስዱ ይቀራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች እናንተ ጋር ይመጣሉ? እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የእናንተ ሥራ ምንድን ነው?
አቶ ዘውዱ፡- እንዲህ ዓይነት ችግሮች ያጋጥሙናል፡፡ ካሳ በኤጀንሲውና በኢንሹራንስ በኩል የሚፈጸም ቢሆንም አስፈጻሚው ኤጀንሲው ነው፡፡ ስለዚህ ዜጐች ኢንሹራንስ ኩባንያ ሄደው ካሳ በሚጠይቁበት ጊዜ የሚገጥማቸውን ችግሮች ኤጀንሲው ጋር ይዘው ይመጣሉ፡፡ የሕግ ክፍላችንም ወደ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እየደወለ የተሳሳቱ አሠራሮችን እናርማለን፡፡ አዋጁ የወጣው የተሽከርካሪ አደጋ ተጐጂ ሳያስብበት አደጋ አጋጥሞታል፣ አደጋ ተሸክሞ ሕክምናና ካሳ ለማግኘት መጉላላት የለበትም ከሚል ነው፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታም ሕክምናና ካሳ ማግኘት አለበት፡፡ በተሽከርካሪ ስለመጐዳቱ የፖሊስ ማረጋገጫ፣ የሞተ ከሆነ ደግሞ የሟች ወራሽነት ማረጋገጫ፣ የአካል ጉዳት ከሆነ የሕክምና ቦርድ ማስረጃ አሟልቶ እስከሄደ ተጐጂ ካሳውን ማግኘት አለበት፡፡ ተከራክሮ፣ ፍርድ ቤት ሄዶ የሚያገኝ ከሆነ የአዋጁ መውጣት አስፈላጊ አልነበረም፡፡ አዋጁን በተሳሳተ መልኩ ከመረዳትና ከመተርጐም በመነሳት በአንዳንድ ኢንሹራንሶች ችግር ይታያል፡፡ ከአሽከርካሪው ወይም ከተሽከርካሪው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማንሳትና ምክንያት በማስቀመጥ የተጐጂውን ካሳ መከልከል አይቻልም፡፡ ሆኖም በተገላቢጦሽ ሲደረግ ይታያል፡፡ ለምሳሌ መንጃ ፈቃድ ደረጃዎች አሉት፡፡ በዓይነትም ተከፋፍሏል፡፡ የደረቅ ተሽከርካሪ መንጃ ፈቃድ ኖሮት የሕዝብ ሲያሽከረክር ጉዳት አድርሷል በሚል ካሳ የሚከለክል አለ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ መድን ገቢውና መድን ሰጪው ተዋውለዋል፡፡ ከውለታ አንጻር የተፈጸመ ስህተት ቢኖር እንኳን ካሳውን ከፍለው ጉዳያቸው ሊሆን የሚገባው ኢንሹራንሱን ከገባው ጋር ነው፡፡ ተጐጂው በተሽከርካሪ መጐዳቱ ብቻ ከተረጋገጠ ካሳው ሊከፈለው ይገባል፡፡ መንጃ ፈቃድ በሌለው አሽከርካሪ፣ ከጭነት በላይ በጫነ ተሽከርካሪ የመጣ ጉዳት ካለ ለተጐጂ ካሳ ከፍለው የተሽከርካሪውን ባለቤት መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ከኢንሹራንስ ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች ወደ ኤጀንሲው ሲመጡ በተናጠል ቅሬታ የቀረበበት ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር እንነጋገራለን፡፡ በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር ውይይት አድርገን መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ቀንሷል እንጂ አልቆመም፡፡ በተደጋጋሚ የምንወያይበት ይሆናል፡፡ የአዋጁ ጽንሰ ሐሳብ ተጐጂው ጉዳት ተሸክሞ ለሕክምናና ለካሳ ጥያቄ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥበት አይገባም የሚል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በንብረትም ሆነ በሰው ላይ ለሚያደርሱትና ለሚደርስባቸው ጉዳት ሙሉ ኢንሹራንስ (Comprehensive) ለሚገቡ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የሦስተኛ ወገን መድንም እንዲገቡ ይገደዳሉ፡፡ ለአንድ ተጐጂ ሁለት ካሳ የማይከፈል ቢሆንም መድን ለሚገባው ሁለት ወጪ ነው፡፡ ይህን ለማስታረቅ ምን ተሠርቷል?
አቶ ዘውዱ፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ እየተከሰተ ያለ ችግር አለ፡፡ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ሦስተኛ ወገን ላይ ለሚደርስ ጉዳት ካሳ ለመክፈል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሙሉ ኢንሹራንስ (በኮምፕርሄንሲቭ) አካተው ይሠሩ ነበር፡፡ አዋጁ ሲወጣ የራሱ አሠራር፣ ስቲከር ይዞ መጥቷል፡፡ አንዳንድ ኢንሹራንሶች በኮምፕሪሄንሲቭ አካተው ሲሰጡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከኮምፕሪሄንሲቩ በተጨማሪ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስም ያስከፍላሉ፡፡ ተገልጋዮች ሁለት ጊዜ ኢንሹራንስ እየከፈልን ነው ብለው ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ አዋጁ አስገዳጅ ስለሆነ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከኮምፕሪሄንሲቩ ውስጥ ሦስተኛ ወገንን ነጥለው እንዲያወጡ እየተነጋገርን ነው፡፡