‹‹ማርች ኤይት›› ተብሎ የሚታወቀውና በያመቱ የካቲት 29 ቀን ላይ የሚውለው የዓለም የሴቶች ቀን፣ በቀዳሚዎቹ የደርግ ዘመናት ብሔራዊ በዓል ነበር፡፡ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፣ ከ39 ዓመት በፊት የካቲት 29 ቀን 1970 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በዓሉን ያስከበረው በ‹‹አብዮት›› አደባባይ ነበረ፡፡ በወቅቱ ሴት ላባደሮችና ተማሪዎች ጨምሮ በርካቶች በሠልፍ ትርዒቱ ላይ ተካፍለዋል፡፡ በፎቶዎቹ እንደሚታየው የአብዮቱ ‹‹የጡት አባቶች›› የካርል ማርክስ፣ የፍሬድሪክ ኤንግልስ፣ የቭላድሚር ኢሊዮች ኢሊዮኒቭ ሌኒን እንዲሁም የሊቀ መንበር ማኦ ሴቱንግ ፎቶዎች በሠልፈኞቹ ተይዘዋል፡፡ ከተያዙት መፈክሮች መካከልም ‹‹ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለዘላለም ይኑር››፣ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር››፣ ‹‹ምርታችንም ያድጋል ትግላችንም ያሸንፋል›› ይገኙበታል፡፡ (ፎቶ በሁበርት ታቡቲያ)
– ሔኖክ መደብር
* * * * * * *
‹‹አንድ ቀን›› መቼ ነው?
አይዞህ! ‹‹አንድ ቀን›› ይሳካል!!
ሁሉም ለበጎ ነው ነገር ሁሉ ያልፋል
ዛሬ ያልተቃናው ያልሆነበት ምስጢር
እንዲህ ነው… እንዲያ ነው…
እያልኩኝ ለ‹‹ራሴ›› ቀን በቀን ስነግር
እራሴን ስደልል ምክንያት ስደረድር
በሰውኛ ቋንቋ ‹‹ራሴ›› አፋ’ውጥቶ
‹‹መቼ ነው ‘አንድ ቀን?’ መቼ ይሆን ከቶ?››
ብሎ ቢጠይቀኝ
ምላሹን ስላጣሁ ግራ ስለገባኝ
‹‹ነገ ነግርሃለሁ ዛሬን ብቻ ተወኝ››
ብዬ መለስኩለት
‹‹ራሴን›› ደግሜ መልሼ ሸወድኩት
አንተም እንደ ‹‹ራሴ›› ሰውኛ ከገባህ
እስኪ መልስ ካለህ ንገረኝ እራስህ
አንድ ቀን! መቼ ነህ?
- ዳንኤል ቢሰጥ እቴቴ ‹‹አፈር ብላ›› (2006)
* * * * * * *
‹‹ድንቼ የሚሉሽ ሊልጡሽ እንጂ ነው››
አንዲት አጠር፣ ደልደል ያለች ደባካ መሳይ የአለቃ ገብረሐና ጎረቤት፣ ‹‹አባ ሰው ሁሉ ድንቼ፤ የኔ ድንች እያለ ያቆላምጠኛል›› ብትላቸው፣ ‹‹አዬ ሞኝት፣ እውነት መስሎሽ ነው? ድንቼ፤ ድንቼ የሚሉሽ ሊልጡሽ እንጂ ነው አሉዋት፡፡›› ድንቡሼዋ ጐረቤታቸው አዲስ ልብስዋን ልታስመርቅ እየሮጠች ወደቤታቸው ስትመጣ አመለጣትና መአዛው ቤቱን አወደው፡፡ አለቃ ገብረሐና ግን እንዳላወቀ ሰው ‹‹በውኃ ይለቅልሽ፤ ጥሎሽ ይሂድ›› ብለው ከመረቋት በኋላ ‹‹እንግዲህ ይህችን ከሰው ዘንድ ስትደርሽ ብን እያደረግሽ ኩሪ›› ብለው አሰናበቷት፡፡
ድንቡሼም ለአቅመ ሔዋን እንደደረሰች አንድ አህያ ነጂ አገባች፡፡ ታዲያ ገብረሐና ይንቁት ኖሮ አንድ ቀን ሰውየው አህዮች እየነዳ ባጠገባቸው ሲያልፍ፤ ‹‹ጤና ይስጥልኝ አባ›› ብሎ የግዜር ሰላምታ ቢያቀርብላቸው፤ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን፤ እንደምን ዋላችሁ?›› በማለት መለሱለት፡፡ አህያ ነጂውም በዚህ ተበሳጭቶ ስለነበር ቤታቸው እስኪገቡ ጠብቆ ገላጋይ በሌለበት ቀጠቀጣቸው፡፡ ዱላው ክፉኛ ጐድቷቸው ስለነበርም ታመው ተኙ፡፡ አመሻሹ ላይ እያነከሱ ከውጭ ሲመለሱ አህያ ነጂው ድንቡሼን አስከትሎ እንዳላወቀ ሰው ሊጠይቃቸው መጣ፡፡ ‹‹አለቃ ምን ሆኑ?›› ሲልም ጠየቃቸው፡፡ ‹‹አህያ ረግጦኝ ነው ልጄ›› አሉት ፈጠን ብለው፡፡
- አረፈዓይኔ ሐጎስ ‹‹አለቃ ገብረሐና እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው››
* * * * * * *
ውጤታማ መሣሪያን ላለማጣት
በቅርቡ የሰው ቤት እየሰበሩ በመዝረፍ ወንጀል ስለታሠሩት ሁለት ስኮትላንዳውያን ሰምታችኋል? የተያዙት የአንዱን ቤት መስተዋት የሰበሩበትን ጡብ ረስተው በመሄዳቸው ተመልሰው ሊወስዱ ሲሞክሩ ነው፡፡
- አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)
* * * * * * *
የመፀዳጃ ቤት ሽታ በረራ አስተጓጎለ
በህንድ ከባንጋሎር ወደ ኒው ደሊህ ከተማ ተሳፋሪዎችን ይዞ መብረር የጀመረው የስፓይስ ጀት አውሮፕላን ከመፀዳጃ ቤቱ ይወጣ በነበረ ከባድ ሽታ ምክንያት ወዲያው እንዲያርፍ መደረጉን የሚረር ዘገባ አመለከተ፡፡ አውሮፕላኑ ለጥቂት ደቂቃዎች እንደተጓዘ ተጓዦች በመፀዳጃ ቤት ሽታ ክፉኛ መቸገር ጀመሩ ቀጥሎ ደግሞ አውሮፕላን አብራሪዎቹም በሽታው በመቸገራቸው አውሮፕላኑ በቅርብ ወደሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያመራ ለማድረግ ወስነዋል፡፡ ይህ ቦይንግ 737 200 የሚሆኑ መንገደኞችን ይዞ የነበረ ሲሆን በመጨረሻ በሰላም ሊያርፍ ችሏል፡፡
* * * * * * *
በዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሴቶች የተባሉ ነገሮች
‹‹ሴትነታችን ልናሳካ ከምንችለው ነገር ሊገታን አይችልም››
ሚሼል ኦባማ
‹‹በፖለቲካ ምን እንደተባለ ማወቅ ከፈለጋችሁ ወንዶችን፣ ምን እንደተሠራ ደግሞ ሴቶችን ጠይቁ››
ማርጋሬት ታቸር
‹‹በዓለም ላይ የሴቶች መማርና የበቁ መሆን ሁሉም ሰው መተሳሰብ፣ መቻቻልና ሰላም የመላበት ሕይወት እንዳይኖር አያደርግም››
አን ሳን ሱቺ