Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢትዮጵያዊው ቀማሪ

ኢትዮጵያዊው ቀማሪ

ቀን:

ፊዚክስና ሒሳብ ከሌሎቹ በተለየ የሚወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከፊዚክስ የበለጠ ደግሞ ሒሳብ ደስ እንደሚለው ይናገራል፡፡ የሒሳብ ትምህርትን በልዩ ተመስጦ መሥራት የጀመረው የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር፡፡ የሒሳብ ሥሌቶችን ሲሠራ መጻሕፍ ላይ ያሉ ጥያቄዎችን አያስቀርም፡፡ ጠጠር ያሉ መልስ ያልተገኘላቸውን ጥያቄዎች ጭምር ከኢንተርኔት ላይ አድኖ ይሠራል፡፡ እንደሱ ሁሉ ለሒሳብ ልዩ ትምህርት ፍቅር ያላቸው ወላጅ አባቱም ያግዙት ነበር፡፡ ያልተመለሱ ውስብስብ ያሉ የሒሳብ ጥያቄዎችን አፈላልገው የሚሰጡትም እሳቸው ናቸው፡፡  

በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ሁንዴ ኤባ የተወለደው ወለጋ ውስጥ በምትገኘው ሻምቦ በተባለች ቦታ ነው፡፡ ወላጆቹ በሥራ ምክንያት ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ስለሚዘዋወሩ ሁንዴ በተለያዩ ከተሞች ነው የተማረው፡፡ የሦስት ዓመት ሕፃን ሳለ በከተማው ወደ ምትገኘው ጊምቢ የተባለች አካባቢ ከወላጆቹ ጋር ተዛወሩ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የጀመረውም ጊምቢ ነበር፡፡ እስከ ሁለተኛ ክፍል በጊምቢ ከተማረ በኋላ ወደነቀምት በመዛወር አብዲ ቦሪ የሚባል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደረገ፡፡

በትምህርቱ ደከም ያለ በመሆኑ ሁለተኛ ክፍልን ደግሞ እንዲማር ተደርጓል፡፡ ‹‹ብዙ አስጠኚዎች ነበሩኝ፣ ነገር ግን ፈጣን አልነበርኩም›› ሲል ወላጆቹ በትምህርቱ እንዲሻሻል ብዙ ይጥሩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ነገሮች ባልተጠበቀ ፍጥነት መልካቸውን ቀየሩ፡፡ ሦስተኛ ክፍል እንደገባ በደካማነቱ የሚታወቀው ሁንዴ ከክፍል አንደኛ በመውጣት ሁሉን አስገረመ፡፡ ይህ አጋጣሚ የፈጠረው ጠባብ ዕድል አልነበረም፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሉ ከተባሉ ብርቱ ተማሪዎች መካከል ግንባር ቀደም ለመሆን ችሏልና፡፡ ከክፍል አንደኛ መውጣትንም ልምዱ አድርጓል፡፡

ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የተማረው በጅማ ከተማ ነው፡፡ አፍ መፍቻ ቋንቋው ኦሮምኛ ለነበረው ሁንዴ ጅማ ገብቶ በአማርኛ መማር ከብዶት ነበር፡፡ ‹‹አፍ መፍቻዬ ኦሮምኛ ነው፡፡ አማርኛ ይቸግረኝ ነበር›› ይላል፡፡ አጋጣሚው ከተለመደው ደረጃው ዝቅ እንዲል አድርጎት ነበር፡፡

ቀስ በቀስ በማሻሻል ስምንተኛ ክፍል ሲገባ መልሶ አንደኛ መውጣት ጀመረ፡፡ በአገር አቀፍ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቦ ነው ወደ ዘጠነኛ ክፍል የተዘዋወረው፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን በኮከበ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር ጀመረ፡፡ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የተማረው በዚሁ ትምህርት ቤት እንደነበር ይናገራል፡፡

ትምህርቱ የሚሰጠው በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደመሆኑ ከተማ መቀየሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ በትምህርቱ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ አልነበረም፡፡ ዩኒቨርሲቲ እስኪገባ ድረስም ከክፍል አንደኛ በመውጣት በትምህርቱ ቀዳሚ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ በብሔራዊ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ከክፍለ ከተማው ተሸላሚ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው፡፡ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ለመማር የመረጠው የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት ስለሚያስደስተው እንደሆነ ይናገራል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በሚዘጋጀው ዓመታዊ የፈጠራ ውድድር ይሳተፋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት ወቅት ሦስተኛ ነበር የወጣው፡፡ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ሁለተኛ መውጣት መቻሉን ይናገራል፡፡ በመጀመሪያ ተሳትፎው የተወዳደረው በሠራው የሚራመድ ሮቦት፣ በሪሞት በሚሠራ መኪና፣ አቅጣጫን በራሱ ማስተካከል በሚችል አውቶማቲክ ዲሽ ነው፡፡ በራሱ ልብስ መጥለፍ የሚችል አውቶማቲክ የሽመና ማሽን ደግሞ ሁለተኛ የወጣበት ፈጠራው እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዚህኛው ዓመት በሚካሄደው የፈጠራ ውድድር ላይም ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ለፈጠራ ሥራ ያለው ፍቅር የሒሳብ ትምህርትን ግን አላስረሳውም፡፡ የጀመረውን ኤሌክትሮ ሜካኒካል ትምህርት እንዳጠናቀቀ ሒሳብን በዲግሪ የመማር ፍላጎት አለው፡፡ እስከዚያም ‹‹በጊዜው እደርስበታለሁ፤›› ብሎ አርፎ መቀመጥን አልመረጠም፡፡ ጠጠር ያሉ የሒሳብ ጥያቄዎችን አሳዶ ይሠራል፡፡ መልስ ያልተገኘላቸውን ደግሞ በሚችለው ሁሉ ይሞክራል፡፡ የራሱ አዲስ የሒሳብ ፎርሙላ ማግኘቱንም ይናገራል፡፡

‹‹የሠራሁት ፎርሙላ ቀላል ነው፡፡ 1፣ 2፣ 3፣ ብለው የሚቀጥሉ ናቹራል ቁጥሮችን እስከሆነ ቁጥር ብንደምር የምናገኘው መልስ ምንድን የሚል የ12ኛ ክፍል የሒሳብ ትምህርት ላይ የተማርነውን ነው፤›› ሲል ለሠራው አዲስ ፎርሙላ መነሻ የሆነውን ይናገራል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ከአንድ እስከ አንድ ሚሊዮን ያሉትን ቁጥሮች ለመደመር ካልኩሌተር በመጠቀም ግድ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አሰልቺና ረዥም ነው፡፡ በቀላሉ መልሱን ሊሰጠን የሚችል ቀመር (ፎርሙላ) መኖር አለበት፡፡ ይህም አሥራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርት ላይ የሚገኝ የጋውዝ ፎርሙላ የተባለ ቀመር አለ ይህንን ፎርሙላ ለማግኘት ግን በቅድሚያ አሰልቺና ውስብስብ የሒሳብ ሥሌቶችን መሥራት ግድ ይላል፡፡

‹‹እኔ የሠራሁት እነዚህን አሰልቺ ሥሌቶች አስቀርቶ በአንድ ፎርሙላ ብቻ ቀጥታ መልሱን ማግኘት የሚያስችል ቀመር ነው፡፡ ፎርሙላውን ብቻ በመጠቀም በትሪሊዮንና ከዚያም በላይ ያሉን ማግኘት ያስችላል›› በማለት አሰልቺና ውስብስብ የሒሳብ ሥሌቶችን የሚያስቀር ፎርሙላ መሥራቱን ይናገራል፡፡

ያገኘው ፎርሙላ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ 12 ገጽ የተለያዩ ደረጃዎችን (Proof) ሠርቷል፡፡ ግኝቱንም በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ የሒሳብ መምህራን አቅርቦ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋግጦ ተቀባይነት ማግኘቱን ይናገራል፡፡ በዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ ለመታተም የመጀመሪያ ደረጃ የሆነውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ ለሚገኙ መምህራን ለማቅረብ ቀጠሮ ሰተውት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝም ይናገራል፡፡ ከእነሱ ይሁንታን ካገኘ ለፎርሙላው በዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ ለመታተም አንድ ዕርምጃ ይሆናል፡፡ ሁንዴ ከዚህም ሌላ ሌሎችም የሒሳብ ቀመሮችን ሠርቷል፡፡ በመሥራት ላይም ይገኛል፡፡ የሒሳብ ትምህርት በዲግሪ ሲማር ደግሞ ምን ያህል ቀመሮችን ሊሠራ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

በአገሪቱ ጥቂት የማይባሉ ወጣትና ታዳጊዎች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ፈጠራዎቹ ከመወዳደሪያነት በዘለለ ርቀት ሲጓዙ አይስተዋልም፡፡ ለፈጠራ ሥራ ውድድር የሚሆናቸውን ሞዴል ሠርተው ከተጨበጨበላቸው በኋላ ሥራቸው ከዴስክ ማሞቂያነት በዘለለ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ሞዴሉን ወደ ቁስነት ለመቀየር ተፈላጊውን ግብዓት ከማግኘት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥማቸዋል፡፡ ሁንዴም ከእነዚህ መካከል ነው ‹‹ሞዴሉን ወደ ቁስነት ለመቀየር ገንዘብም ስፖንሰር አድራጊም ይፈልጋል፡፡ እኛ ጋር ደግሞ ይኼንን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እኛም ማፈላለግ አንችልም፤›› ሲል ከውድድር ባለፈ በፈጠራቸው ብዙም እንደማይጠቀሙበት ይገልጻል፡፡ ለፈጠራቸው የባለቤትነት መብት የሚያገኙበት አሠራር ቢኖር አሊያም ጠቋሚ መረጃዎች የሚያገኙበት ሁኔታ ቢመቻች ፈጣሪ አዕምሮን ማበርታት ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...