Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልመሰናዶን በዲጂታል ማስታወቂያ

መሰናዶን በዲጂታል ማስታወቂያ

ቀን:

ብሩክ ሰውነትና ሲራክ ኃይሉ በአዲስ አበባና በሌሎች አጎራባች ከተሞችም የሚካሄዱ ዝግጅቶችን ከሚከታተሉ መካከል ናቸው፡፡ የጥበብ፣ የቢዝነስ፣ የጤና አልያም ሌላ መርሐ ግብሮች ሲዘጋጁ ስለ ዝግጅቶቹ መረጃ ለመሰብሰብ ይሞክራሉ፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባም ይሁን በሌሎች ከተሞች ዝግጅቶች ሲኖሩ በተዋቀረ መንገድ ለሕዝብ የሚደርሱበት መንገድ እምብዛም ስላልሆነ ይቸገራሉ፡፡ ችግሩ የሁለቱ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ነው፡፡ የተለያዩ መሰናዶዎች መቼና የት እንደሚከናወኑ ለማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ በእርግጥ በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ድረ ገጾችም የሚተዋወቁበት ጊዜ ቢኖርም፣ ለታዳሚዎች በሚያመች መልኩ በተዋቀረ ሁኔታ አይቀርቡም፡፡

የአይቲ ባለሙያዎቹ ብሩክና ሲራክ የነሱና የሌሎችንም ችግር ለመቅረፍ በሚል ኢቨንትስ ኢትዮጵያን የመሠረቱት ከአሥር ዓመት በፊት ነበር፡፡ ኢቨንትስ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካይነት ክንውኖች የሚተዋቁበት ሲሆን፣ ትዊተርና ፌስቡክ ቫይበርና ቴሌግራምን ይጠቀማሉ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ የሞባይል አፕልኬሽን አዘጋጅተዋል፡፡ በትዊተር 16,200፣ በፌስቡክ 5,000፣ በቫይበርና ቴሌግራም 600 ተከታዮች አሏቸው፡፡ የሞባይል አፕልኬሽኑን 4,500 ሰዎች በስልካቸው ጭነዋል፡፡ በተጨማሪም 500 ሰዎች ኢቨንትስ ኢትዮጵያን ሰብስክራይብ አድርገው የኢሜይል መልዕክት ይላክላቸዋል፡፡

በነዚህ ድረ ገጾች የሚለቀቀው መረጃ እንደየአስፈላጊነቱ አዳዲስ መረጃ በማቅረብ አፕዴት ይደረጋል፡፡ ተከታዮቹ የተለያዩ መሰናዶዎችን መታደም ፈልገው ድረ ገጾቹን የተቀላቀሉ መሆናቸውን ብሩክ ይናገራል፡፡ እያንዳንዱ ድረ ገጽ ከሌላው የሚለይ እንደመሆኑ፣ የተጠቃሚዎች ተደራሽነት መጠኑም ይለያያል፡፡ በድረ ገጾቹ የሚለቀቁትን መረጃዎች ተመልክተው መርሐ ግብሮችን ከሚታደሙ ሰዎች ቀና ምላሽ ማግኘታቸውን ያስረዳል፡፡

   ብሩክ እንደሚለው፣ መርሐ ግብሮችን አፈላልገው በድረ ገጻቸው በመልቀቅ እየታወቁ ሲመጡ፣ አዘጋጆችም መሰናዷቸውን በገጻቸው ፖስት እንዲያደርጉላቸው ይጠይቋቸው ጀመሩ፡፡ አንዳንዶች ስላዘጋጁት መርሐ ግብር ኢሜይል በመላክ በኢቨንትስ ኢትዮጵያ እንዲተዋወቅላቸው ያደርጋሉ፡፡ ‹‹ የተለያዩ መርሐ ግብሮች መታደም ለሚፈልጉ ሰዎች ምን፣ የት እየተከናወነ እንደሆነ እያሳወቅን ነው፤›› ይላል፡፡

በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በርካታ መርሐ ግብሮች ይካሄዳሉ፡፡ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የምግብና መጠጥ ፌስቲቫልና ኮንፈረንሶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ መርሐ ግብሮቹ ካለው የሕዝብ ብዛት አንፃር በቂ ባይሆኑም፣ ያሉትንም የሚታደሙ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር እንደ ኢቨንትስ ኢትዮጵያ ያሉ የማስታወቂያ መንገዶች ያስፈልጋሉ፡፡

መርሐ ግብሮች የሚያዘጋጁ ሰዎች በተለያየ መንገድ መሰናዷቸውን ማስተዋወቃቸው አይቀርም፡፡ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮና ጋዜጣ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹ማኅበራዊ ድረ ገጽ በአነስተኛ ወጪ በማስተዋወቅ ጎን ለጎን ይሄዳል፤›› ይላል ብሩክ፡፡ ሥራው  የተጋነነ ገቢ ባያስገኝም፣ ቢያንስ የሥራውን ወጪ የሚሸፍን ገንዘብ እንደሚያመነጭ ይገልጻል፡፡

 ሆኖም የኢንተርኔት ዋጋ መወደድ፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ውስን መሆንና ኢንተርኔት በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡ ለሥራቸው እንቅፋት ሆኗል፡፡ ‹‹መርሐ ግብር ለሚያዘጋጁ ሰዎች፣ ዝግጅታቸውን በስፋት የማስተዋወቅ ሚና አለን፡፡ ኢንተርኔት ሲዘጋ ግን በስልክና በዴስክቶፕም መረጃዎችን የሚከታተሉ ሰዎች ይቀንሳሉ፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ ኢንተርኔት በየምክንያቱ ከመቆራረጡ ባሻገር የቪዲዮ መልዕክት አፕሎድ ለማድረግ የሚወጣው ወጪ ብዙ ነው፡፡ ከአብዛኛው ሰው ኢኮኖሚያዊ አቅም አንፃር እነዚህን መረጃዎች ዳውንሎድ ለማድረግም ውድ ነው፡፡ የአገሪቱ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ማነስም ሌላው መሰናክል ነው፡፡

እንደ ኢቨንትስ ኢትዮጵያ ሁሉ መርሐ ግብሮችን ከአዘጋጆች፣ ከጋዜጣ፣ ከመጽሔት፣ ከሬዲዮ፣ ከጋዜጣዊ መግለጫዎችና ከድረ ገጾች በማሰባሰብ ለሕዝብ የሚያቀርቡ እየበዙ መጥተዋል፡፡ ኋትስ ሀፕኒንግ ኢን አዲስ፣ ኋትስ አውት አዲስና ዋን ሚሊየን ሀፕኒንግስ ኢን አዲስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብሩክ እንደሚናገረው፣ ድረ ገጻቸው ለመርሐ ግብር ታዳሚዎች ብቻ ሳይሆን ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ የሚሰጥበት ጊዜም አለ፡፡

በርካታ ክንውኖች የሚያስተናግዱት የውጭ የባህል ማዕከሎች የጣሊያን ባህል ተቋም፣ ጎተ እና አሊያንስ ኢትዮፍራንሴዝ ናቸው፡፡ በነዚህና በሌሎችም ማዕከሎች የሚካሄዱ መሰናዶዎችን የማስተዋወቅ ሥራ አሁን ካለውም መስፋት እንደሚችልም ያምናል፡፡

ወደ ናኤል ኢቨንትስ የቴሌግራም ቻናል ሲገቡ፣ ኅዳር 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል የሚካሄደው ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት ማስታወቂያ ይገኛል፡፡ ከዛ ቀደም ብሎ ባለፉት ሳምንታት የተካሄዱ መርሐ ግብሮችም ፖስት ተደርገዋል፡፡ አሸሸ ገዳሜ ኮንሰርት፣ ቴስት ኦፍ አዲስ (የምግብ ፌስቲቫል)፣ የሞሞና ሆቴል ፑል ፓርቲ፣ ኦፕንኤር (ከሲኒማ ቤት ውጪ ባለ ክፍት ቦታ) ሲኒማ፣ በጥቅምት አንድ አጥንት የሥጋና ቢራ ፌስቲቫልና የዓለም የስኳር ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የእግር ጉዞ ይገኙበታል፡፡

ከፌስቡክና ትዊተር በተጨማሪ የቴሌግራም፣ ቫይበርና ዋትስአፕ ግሩፖች በመፍጠር መርሐ ግብሮች የሚያስተዋውቁ እየበዙ መጥተዋል፡፡ የተለያዩ መሰናዶዎችን በጽሑፍ፣ በምስልና አንዳንዴም በቪዲዮ ይተዋወቃሉ፡፡ የናኤል ኢቨንትስ ሥራ አስኪያጅ ናትናኤል አዳነ፣ ቀድሞ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ያዘጋጅ ነበር፡፡ ዝግጅቶችን ለማስተዋወቅ በራሪ ወረቀት ማሳተምና ሬክላም መስቀልም ያስፈልግ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ እነዚህ የማስታወቂያ መንገዶች አሁንም ጥቅም ላይ ቢውሉም፣ በአጭር ጊዜ ብዙዎችን ለመድረስ ማኅበራዊ ድረ ገጽ አዋጭ መሆኑን ይናገራል፡፡

‹‹ድርጅቶች መርሐ ግብራቸው እንዲተዋወቅላቸው ይጠይቁናል፡፡ የቅርብ ጊዜውን ጊዜ ኮንሰርት 2 መጥቀስ ይቻላል፡፡ የድረ ገጻችንን ተከታዮች ከማብዛት ባለፈ ብዙ ገንዘብ አናገኝም፤›› ይላል፡፡ በቴሌግራም 3,900 ተከታዮች ያሏቸው ሲሆን፣ እንደ ፌስቡክ ያሉ አማራጮችንም ይጠቀማሉ፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ኮንሰርቶች ሲዘጋጁ በተለያየ መንገድ ስለሚተዋወቁ ተደራሽነታቸው የሰፋ ነው፡፡ ሆኖም ስለ ውይይቶች፣ ሴሚናሮችና ኮንፈረንሶች ከጥቂት ሰዎች ባለፈ መረጃው አይሠራጭም፡፡ ‹‹ሰዎች ስለዝግጅቶቹ መኖር በእጃቸው ባለ ስልክ መረጃ ሲደርሳቸው ለመካፈል ይነሳሳሉ፤›› ይላል፡፡ ድረ ገጾቹ በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት መርሐ ግብሮችን መታደም የሚያዘወትሩ ሰዎችን ታሳቢ እንዳደረጉ ያስረዳል፡፡ በድረ ገጾቹ የሚተላለፉ መረጃዎች በዓይነት እየበዙ የሄዱት ብዙ አዘጋጆቹ በድረ ገጾቹ መሰናዶዎቻቸው እንዲተዋወቅላቸው በመፈለጋቸው ነው፡፡ ሕዝቡም ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲኖሩ የመሳተፍ ባህሉ እየጎለበተ መጥቷል፡፡

በአዘጋጆችና ታዳሚዎች መካከል ያሉት ድረ ገጾች፣ በኢንተርኔት ዋጋ መወደድና አገልግሎቱ በመቆራረጡ መፈተናቸውን ይስማማበታል፡፡ ቢሆንም መርሐ ግብሮችን ለማግኘት ቀላል እንዲሆን የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ማስታወቁ መቀጠል እንዳለበት ይናገራል፡፡

‹‹አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በዲጂታል ማስታወቂያ ብቻ ለመመርኮዝ የተመቸ አይደለም፤›› የሚለው ናትናኤል፣ የኦንላይን ክፍያ ሥርዓት አለመዘርጋት ሌላው መሰናክል እንደሆነባቸው ይገልጻል፡፡ ፌስቡክ ላይ መርሐ ግብሮች የሚያስተዋውቅ ገጽ ከፍቶ 10,000 ሰው ለማግኘት ለተቋሙ በየቀኑ ይከፈላል፡፡ ማስታወቂያ እንደሚደርሰው ሰው ብዛት ከአምስት ዶላር ጀምሮ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ውጣ ውረዶቹ እንዳሉ ሆነው፣ የድረ ገጾቹ መኖር ለመርሐ ግብር አዘጋጆችና ለታዳሚዎችም የጎላ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

የኢኤምኤል ኢቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢዩኤል ልዑልሰገድ እንደሚናገረው፣ ከ60 እስከ 70 በመቶ ማስታወቂያ የሚሠራው በማኅበራዊ ድረ ገጽ ነው፡፡ ‹‹መርሐ ግብር ስናዘጋጅ ታሳቢ የምናደርገው ታዳሚ ከ16 ዓመት ጀምሮ ያለውን ወጣቱን ክፍል ስለሆነ በፌስቡክና በኢንስታግራም ቤታቸው ሆነው መረጃው ይደርሳቸዋል፤›› ይላል፡፡ በራሪ ወረቀት ማዘጋጀት፣ ባነር መትከልና በጋዜጣ ማስተዋወቅ ከሚጠይቀው ወጪ አንፃር ማኅበራዊ ድረ ገጽ የተሻለ መሆኑንም ያክላል፡፡

እንደ መርሐ ግብር አዘጋጅነቱ ኮንሰርት አልያም ሌላ መሰናዶ ሲኖረው በራሱ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ያስተዋውቃል፡፡ ለመርሐ ግብሮች ብቻ ተብለው በተከፈቱ ገጾች ማስተዋወቅ ተደራሽነቱን እንደሚያሰፋውም ያምናል፡፡ በአዘጋጆችና በታዳሚዎች መካከል ያሉ ተቋሞች የማስተዋወቁን ሥራ ማገዛቸውንም ይገልጻል፡፡ ‹‹ሰው ላይክ በማድረግ፣ ሼር በማድረግና ድረ ገጾችን በመጎብኘትም መሳተፍ አለበት፤›› በማለት ታዳሚዎችም የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ያክላል፡፡

የማኅበራዊ ድረ ገጾች የማስታወቂያ ሥራ የሚፈለገውን ታዳሚ ላይ ማነጣጠር እንዳለበት ኢዩኤል ይናገራል፡፡ በቴሌግራም፣ ቫይበር ወይም በሌሎች ግሩፖች የሚቀላቀለው ሰው፣ መርሐ ግብሮችን የሚሳተፍ ከሆነ ውጤታማ መሆን ይችላል ይላል፡፡

‹‹የቴስት ኦፍ አዲስ፣ የቢራቢሮ ኮንሰርትና የጊዜ ኮንሰርት ታዳሚዎች የማኅበራዊ ድረ ገጽ ማስታወቂያ ውጤት ናቸው፤›› ሲል ማኅበራዊ ድረ ገጾች ያላቸውን አቅም ይገልጻል፡፡ አንድ መርሐ ግብር እስከሚከናወን ድረስ ባሉት ሳምንታት ለወጣቱ በስፋት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ማስተዋወቅ አዋጭ ቢሆንም፣ ለሕፃናትና ለአዋቂዎች ለሚዘጋጁ መርሐ ግብሮች ሌሎች አማራጮችን መጠቀም የግድ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የሥዕል ዐውደ ርዕይ፣ የፋሽን ትርኢት፣ የመጻሕፍት ዳሰሳና ቢዝነስ ተኮር ውይይቶችን የምታዘወትረው ሊንዳ ዘመድኩን፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የዝግጅቶች ማስታወቂያ ከሚከታተሉ አንዷ ናት፡፡ ‹‹በቴሌግራም፣ ቫይበር፣ ትዊተር፣ ፌስቡክና በሌሎችም ድረ ገጾች የተከፈቱ ግሩፖች አባል ነኝ፤›› ትላለች፡፡ በየሳምንቱ ዓርብ በድረ ገጾቹ የተለቀቁ መረጃዎችን ተመልክታ ቅዳሜና እሑድ የምትታደመውን ትመርጣለች፡፡

‹‹ያን ያህል ብዙ ዝግጅቶች የሉም፡፡ ባሉት ዝግጅቶች አዘውትረው የሚሳተፉትም ጥቂት ሰዎች ናቸው፤›› የምትለው ሊንዳ፣ የማኅበረሰብ ድረ ገጽ ማስታወቂያ መስፋፋቱ ምናልባትም ታዳሚዎችን እንደሚያበራክት ታምናለች፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም መሰናዶዎች እንዲበራከቱ የማድረግ ሥራ መቅደም አለበት ትላለች፡፡ በመቀጠልም የተሳታፊዎችን ቁጥር ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ታምናለች፡፡ በሁለቱ መካከል ድልድይ በመሆን በማኅበራዊ ድረ ገጾች የማስተዋወቅ ሥራ የሚሠሩ ተቋሞች ድርሻንም አያይዛ ታነሳለች፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...