Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትየ60 ዓመቱ ተቋምና የ70 ዓመቱ አዛውንት

  የ60 ዓመቱ ተቋምና የ70 ዓመቱ አዛውንት

  ቀን:

  በዋናነት በሦስት የአፍሪካ አገሮች በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ እ.ኤ.አ. በ1957 በሱዳን ካርቱም የተመሠረተው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 54 በመደበኛነት፣ በጊዜያዊነት ደግሞ ሁለት አገሮችን በአባልነት ያስተዳድራል፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ አሁን በመንበረ ሥልጣኑ ላይ የሚገኙትን ካሜሩናዊ ኢሳ ሐያቱን ጨምሮ በአምስት ፕሬዚዳንቶች ሲመራ ቆይቷል፡፡ የ70 ዓመቱ ኢሳ ሐያቱ እ.ኤ.አ. መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም.  በአዲስ አበባ በሚካሄደው የካፍ ምርጫ ለቀጣዩ አራት ዓመትም የካፍን በትረ ሥልጣን ይዘው እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡

  የካፍን በትረ ሥልጣን እ.ኤ.አ. በ1988 ከአፍሪካ የእግር ኳስ አባት ተብለው ከሚታወቁት ይድነቃቸው ተሰማ የተረከቡት ካሜሩናዊው ኢሳ ሐያቱ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ለ29 ዓመታት ያህል በፕሬዚዳንትነት ቆይተዋል፡፡ ለቀጣዩ አራት ዓመትም ከአንዳንድ የደቡብ አፍሪካ ዞን አገሮች ተቃውሞ በስተቀር ካሜሩናዊው ምሥራቅ አፍሪካን ጨምሮ የብዙዎቹ ድጋፍ እንደማይለያቸው ቅድመ ግምት እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡

  ግብፃዊው አብዱልአዚዝ አብዱል ሰላም እ.ኤ.አ. ከ1957 እስከ 1958 የመጀመሪያው የካፍ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ሌላው ግብፃዊ አብዱል አዚዝ ሙስጠፋ ተረክበው እ.ኤ.አ. ከ1958 እስከ 1968 ድረስ ሁለተኛው የካፍ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ሦስተኛው የካፍ ፕሬዚዳንት ደግሞ ሱዳናዊው አብዱል ሐሊም መሐመድ ሲሆኑ፣ እ.ኤ.አ. ከ1968 እስከ 1972 ዓ.ም. በሥልጣን ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ በበኩላቸው እ.ኤ.አ. ከ1972 እስከ 1987 ዓ.ም. ለተከታታይ 15 ዓመታት ካፍን በመምራት ለዘመናዊ የአህጉሪቱ እግር ኳስ ዕድገት ትልቁን ድርሻ ማበርከታቸው ይታመናል፡፡ እንደ አንዳንድ መረጃዎች ከሆነ ካሜሩናዊው ኢሳ ሐያቱ የካፍን በትረ ሥልጣን የተረከቡት ከአቶ ይድነቃቸው እጅ እንዳልሆነ በመሀል ለአንድ ዓመት ያህል ሱዳናዊው አብዱል ሐሊም መሐመድ በጊዜያዊነት ማስተዳደር የቻሉበት አጋጣሚም እንደነበርም ይነገራል፡፡

  በካፍ በትረ ሥልጣን የሦስት አሠርታት ዕድሜ ያስቆጠሩት ካሜሩናዊው ኢሳ ሐያቱ ቀደምቱ ታሪካቸው ከእግር ኳስ ይልቅ ለአትሌቲክስ ፍቅር እንደነበራቸውና የመካከለኛ ርቀት ተወዳዳሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ በአትሌቲክሱም 800 እና 400 ሜትር በአገሪቱ የፈጣን ሰዓት ባለቤትም መሆናቸውን መዛግብቶች ያስረዳሉ፡፡ ከአትሌቲክሱ ጎን ለጎን በቅርጫት ኳስ ለአገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የነበሩ መሆኑም ይነርገላቸዋል፡፡

  ከ1988 ጀምሮ ግን የካፍን በትረ ሥልጣን የተቆናጠጡት የ70 ዓመቱ አዛውንት ኢሳ ሐያቱ፣ በተቋሙ ባሳለፏቸው የኃላፊነት ዓመታት ውስጥ ለእግር ኳስ ዕድገት እምብዛም መሆናቸውም ይነገርላቸዋል፡፡ ይልቁንም ከሙስና ጋር በተያያዙ የሥነ ምግባር ጉድለት ከሚጠቀሱ አንዱ እንደሆኑና በዚህ ረገድም ከሚጠረጠሩባቸው ድርጊቶች መካከል እ.ኤ.አ. በ1990 ጣሊያን ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ወቅት የቴሌቪዥን መብት ለአይኤስኤል (ISL) ለሚባል ድርጅት እንዲሰጠው 100,000 የፈረንሣይ ፍራንክ ተቀብለዋል መባሉ ‹‹የፊፋ ተገቢ ያልሆኑ ሚስጥሮች›› በሚል ርዕስ አንድሮ ጀኒንስ የተባለው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ካቀረባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡

  በተመሳሳይ ኳታር በ2022 ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የአዘጋጅነቱን ዕድል እንድታገኝ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ተቀብለዋል ተብለው ከሚጠረጠሩ የካፍና ፊፋ ኃላፊዎች አንዱ ስለመሆናቸው ጭምር ይነገራል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2002 ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው በሴፕ ብላተር መሸነፋቸው የሚነገርላቸው የካፍ ሊቀመንበር ኢሳ ሐያቱ ለአፍሪካ እግር ኳስ አልሠሩም ብለው ከሚተቿቸው መካከል የአፍሪካ ምርጥ ተጨዋችነትን ክብር ሦስት ጊዜ ያገኘው ጋናዊው አቢዲ ፔሌ ይጠቀሳል፡፡ የቀድሞ ኮከብ ጋናዊ አቢዲ ፔሊ በ2011 ለአፍሪካን ዋች ሜጋዚን በሰጠው ቃለ መጠይቅ የዕድሜ ባለፀጋው ኢሳ ሐያቱ ቦታውን ለተተኪው ትውልድ እንዲለቁ ጠይቋል፡፡ ፔሌ፣ ‹‹ኢሳ ሐያቱና ሌሎች በስራቸው የሚገኙ የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎች የአፍሪካን እግር ኳስ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይታይበት አስረጅተውታል፡፡ እነሱም በቤቱ ውስጥ አረጁበት፡፡ እግር ኳሱንም እንደ ቢዝነስ ተቋም የግላቸው አድርገውታል፡፡ አዲሱ ትውልድም በቃ ሊላቸው ይገባል፤›› ማለቱ ተዘግቧል፡፡  

  ኮንፌዴሬሽኑን ለሦስት አሠርታት ዓመታት የመሩት ካሜሮናዊው ኢሳ ሐያቱ እ.ኤ.አ. መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የካፍ ምርጫ ከማዳጋስካሩ አሕመድ አህመድ ውጪ ተፎካካሪ የላቸውም፡፡

   የካፍ ቀጣይ ፕሬዚዳንት ካሜሩናዊው ኢሳ ሐያቱ ለመሆናቸው ሌላው ማሳያ ተብሎ የሚነገረው ደግሞ ተቋሙ የሚመራባቸው ደንብና መመርያዎች ብዙዎቹ ራሳቸው ሐያቱ ነገሮችን በሚፈልጓቸው መልክ ማስኬድ ይችሉ ዘንድ ያመቻቿቸው መሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህም ለካፍ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆኖ መቅረብ የሚችለው በካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ መቆየት የግድ መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ የዕድሜ ባለፀጋው ኢሳ ሐያቱ ከዚህም በላይ ለካፍ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕድሜና የአገልግሎት ጊዜ ምንም ዓይነት ገደብ እንዳይኖረው ማድረጋቸውም የሚታወቅ ነው፡፡

  በካፍ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የዕድሜያቸውን ግማሽ የዘለቁት ኢሳ ሐያቱ ለተረጋጋው ወንበራቸው መዝለቅ ሌላው በትልቁ የሚነሳው፣ የሁሉንም አባል ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች ጥቅማ ጥቅሞችን በማመቻቸት የሚወዳደራቸው አለመገኘቱ ነው፡፡ ይኼውም ብዙዎቹ የአባል ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች ባላለፉበትና ባልዋሉበት የሙያ ዘርፍ ካፍ በሚያወዳድራቸው ማናቸውም የእግር ኳስ ጨዋታዎች በታዛቢ ዳኝነት እንዲመደቡ ማድረጋቸው በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በቅርቡ በጋቦን አስተናጋጅነት በተከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙ አገሮች ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች የጨዋታ ታዛቢ ዳኛ ሆነው የተመዱባቸው ውድድሮች ለአብነት ማንሳት ይበቃል፡፡ እነዚህና ሌሎች የኢሳ ሐያቱ እጅ መንሻዎች የካፍ መንበረ ሥልጣናቸውን ያለ ተቀናቃኝ አስጠብቀው እንዲቆዩ ምክንያት ስለመሆኑም የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል የሚል ትችትም እየተደመጠ ይገኛል፡፡

   

   

   

     

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...