Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያዊነት ታላቅ መስዕዋትነት የተከፈለበት የጋራ እሴት ነው!

ላለፉት 121 ዓመታት ኢትዮጵያን በታላቅ ግርማ ሞገሥ ስሟን የሚያስጠራት አንፀባራቂው የዓደዋ ድል በሚዘከርበት ሰሞን፣ ኢትዮጵያዊነት የሚባለውን የጋራ እሴት ደግሞ ደጋግሞ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የአገሪቱ ጫፎች ድረስና በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚገለጹበት ይህ ስያሜ፣ የአንድነትና የጀግንነት መገለጫ ነው፡፡ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ ኢትዮጵያዊነት በጠንካራ የአንድነት ገመድ አስተሳስሯቸዋል፡፡ ይህች አገር የኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤታቸው ስትሆን፣ ከልዩነቶቻቸው ይልቅ አንድነታቸው የጠነከረ እንደነበረው ነው የሚታወቀው፡፡ ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ ድል በመላው ዓለም አንፀባራቂ ሊሆን የቻለው፣ በጠንካራ አንድነት ለአገር ራሱን አሳልፎ በሰጠ ጥቁር ሕዝብ የተገኘ የመጀመሪያው ድል በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ታላቅ መስዕዋትነት የተከፈለበት የጋራ እሴት ነው የሚባለው፡፡

በዚህ ዘመን ከመጠን በላይ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ የትናንቱን የሕዝባችንን የአገር ፍቅርና ታላቅ የአርበኝነት ስሜት የሚያደበዝዙና ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ማንነት ላይ ብቻ በመንጠልጠል ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ሞልተዋል፡፡ ዘመን ያለፈባቸውና ከጊዜው ጋር የማይሄዱ አስተሳሰቦችን የበላይ ለማድረግ መከራ የሚያዩም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ታጋሽነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ርህራሔ፣ ጀግንነት፣ መከባበር፣ ወዘተ ያሉበት ትልቅ የጋራ እሴት መሆኑ እየተዘነጋ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ሲባል ብቻ ዘለፋ፣ ስድብ፣ ጥላቻ፣ ግጭትና የመሳሰሉት አላስፈላጊ ጉዳዮች አየሩን ሞልተውታል፡፡ እነዚህ ፈጽሞ የሕዝባችንን አርዓያነት ያለው ወግ፣ ልማድና ባህል የሚጋፉ ድርጊቶች በመሆናቸው በቶሎ መቆም አለባቸው፡፡ የፈለገውን ያህል ልዩነት ቢኖር እንኳ ከሚያጣሉ ይልቅ የሚያግባቡ በርካታ የጋራ ጉዳዮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት በአስተዋይነትና በታጋሽነት የተመሠከረለት የጋራ እሴት መሆኑ እየተረሳ ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ በዘመናችን በተለይ በፖለቲካው ጎራ የሚታየው መረን የለቀቀ ጭፍንነትና ፅንፈኝነት ለዚህ አባባል ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት በዚህ ዘመን የጋራ መገለጫ እሴት እንዲሆን የሚፈለግ ከሆነ፣ በመጀመሪያ ልዩነቶችን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ብልኃት በስፋት መለመድ አለበት፡፡ የአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ አዋጭነት ያላቸው መፍትሔዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፡፡ ሁሌም በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ ውጤት መጠበቅ ከአሰልቺነቱ በስተቀር የሚፈይደው የለም፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በተቃውሞ ጎራ ያሉ ኃይሎች ከገቡበት አዙሪት ውስጥ መውጣት አለባቸው፡፡ በሁለቱም ጎራ በኩል ባለፉት ዓመታት የተደረገው ጉዞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይመጥንም፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚያስቀድመው አገሩን ነው፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ልዩነቶች ቢኖሩት እንኳ ከልዩነቶቹ ይልቅ ለአንድነቱ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፡፡ በታላቁ ዓደዋ ድል መንፈስ ውስጥ የሚኖረው ይህ ኩሩ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ዋዘኛ አይደለም፡፡ ልዩነቶቹ መኖራቸው እስከማይታወቅ ድረስ የአገሩን አንድነት ያስጠበቀው፣ ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ፀጋ ስለሚበልጥበት ብቻ ነው፡፡

ይህች የኩሩዎችና የጀግኖች አገር የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤት ናት፡፡ ልጆቿ አክብረዋት ያስከብሯት ዘንድ የግድ ይላል፡፡ በዓለም ፊት ሊያዋርዷት ከሚፈልጉ ጠላቶቿ ጋር ማበር የክህደት የመጨረሻው ጣሪያ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ መወገዝ አለባቸው፡፡ በአገርና በኢትዮጵያዊነት ቀልድ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት መከበር አለበት ሲባል ለግልና ለቡድን ጥቅም ብቻ ሲሉ የሚሯሯጡ ወገኖች አደብ ይግዙ ማለት ነው፡፡ ለአገራቸው ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የሚያደርጉ፣ በክፉ ጊዜ ደራሽ የሆኑና እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ለአገራቸው ቀናዒ የሆኑ ዜጎች ያስፈልጋሉ፡፡ የኢትዮጵያዊነትን እሴት ላቅ ያለ ደረጃ የሚያደርሱ ትጉኃን ያስፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያችን በዓለም አደባባይ የሚያስከብሯት ታላላቅ ገድሎች ባለቤት ናት፡፡ ለዘመናት ላይዋ ላይ ሲጋልቡ ከኖሩት ድህነት፣ በሽታ፣ መሐይምነት፣ ኋላቀርነትና ተስፋ መቁረጥ በላይ የምትኮራባቸው ታሪኮች የተከናወኑባት ናት፡፡ የአገሪቱ ዜጎች አንገታቸውን ሲያስደፉ ከቆዩ መከራዎች በላይ፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ጥቁሮች ተምሳሌትነትዋ የላቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያችን እንደ መርግ ይከብዱ ከነበሩ ቀንበሮቿ በላይ፣ ታሪኮቿና ገድሎቿ ህያውና አንፀባራቂ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ክብር የሚገባት ታላቅ አገር ናት፡፡ ይህ ትልቅ ፀጋ በዋዛ መታየት የለበትም፡፡

ሕዝባችን በውስጡ ያሉትን ልዩነቶች ጥበባዊ በሆነ መንገድ ይዟቸው በእርስ በርስ መስተጋብሩ ተምሳሌታዊ አንድነቱን ይዞ ዘልቋል፡፡ ለዘመናት የዘለቀው ይኼ አስደናቂ አብሮነት ዛሬም አለ፡፡ ነገር ግን አደፍራሾች ከራሳቸው ጠባብ ዓላማ በመነሳት ይህንን ተዓምራዊ መስተጋብር ለመበጥበጥ ላይ ታች ይላሉ፡፡ ሕዝቡን በብሔር ከፋፍሎ ለማጋጨት የተደረገው ሙከራ አልሳካ ሲል፣ መጠራጠርና መፈራራት ለመፍጠር ያለማሰለስ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ይደረጋል፡፡ ለአገሩ ቀናዒ የሆነው ይህ ኩሩ ሕዝብ በደስታውም ሆነ በመከራው በአንድ ላይ መኖሩ እየታወቀ፣ አንዱን ገዥ ሌላውን ተገዥ አስመስሎ የማቅረብ እኩይ ድርጊቶች በብዛት ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት የራሱ ዓላማና የጋራ እሴት የሌለው ይመስል ከእውነታ ጋር መጋጨት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ይህንን የተበላሸና ወልጋዳ ዓላማ ይዞ ትርምስ ከመፍጠር ይልቅ፣ ብልሹው የፖለቲካ ዓውድ እንዲስተካከል በድፍረትና በቆራጥነት መሥራት ይበልጣል፡፡ በዓለም ታሪክ ውስጥ እንደተመዘገበው ዴሞክራሲ ዕውን መሆን የሚችለው መርህ ባላቸውና በቆራጥነት በሚሠሩ ብቻ ነው፡፡ እየደጋገሙ በስህተት ጎዳና ላይ መጓዝ ከውድቀት ውጪ ትርፍ የለውም፡፡ ለአገርም አይጠቅምም፡፡ ለአገር የሚጠቅመው ሕዝብ የሚፈልገውን ማድረግ ብቻ ነው፡፡

ዕድሜ ለታላቁ የዓደዋ ድል ኢትዮጵያ ከዜጎቿ አልፋ የአፍሪካውያንና የሌሎች ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ ሆናለች፡፡ ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ ለመላቀቅ የወኔ ስንቅ ያገኙት ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህንንም ደግመው ደጋግመው መስክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከገዛ ዜጎቿ በተጨማሪ ለአፍሪካውያን ቤታቸው ናት፡፡ በርካታ አፍሪካውያን ወንድሞችንና እህቶችን አስተምራለች፡፡ አስጠልላለች፡፡ ከቅኝ አገዛዝ ለመላለቅ ሲታገሉም አብራቸው ነበረች፡፡ ዛሬም አብራቸው አለች፡፡ በዚህም ከፍተኛ ክብር ተጎናፅፋለች፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት ይህ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ እሴት የማስከበር ኃላፊነት ወር ተራው የዚህ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ያለበት ዘመን እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን በጣም የሠለጠነና ለሰጥቶ መቀበል መርህ ዝግጁ የሆነ ነው፡፡ በዚህ በቴክኖሎጂ በተራቀቀ ዘመን ከኋላቀር አስተሳሰቦችና አንድም ዕርምጃ ከማያራምዱ ድርጊቶች መላቀቅ የግድ ይላል፡፡ በተለይ በፖለቲካው አካባቢ ያሉ የዚህ ትውልድ አባላት እከሌ ከእከሌ ሳይባባሉ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን ብቻ ማሰብ ለአገር አይጠቅምም፡፡ ይልቁንም ከምንም ነገር በላይ የአገሪቷና የሕዝቡ ጥቅም መቅደም አለበት፡፡ ይህ የጋራ ጥቅም መቅደም የሚችለው ደግሞ በመከባበርና በወዳጅነት መንፈስ ለበርካታ ዓመታት የተበላሸውን ግንኙነት ማደስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የመፈራረጅና የመጠላላት ፖለቲካ ለአገሪቱም ሆነ ለዚህ የተከበረ ሕዝብ እንደማይበጅ፣ ለዘመናት አንድነቱን አጠናክሮ የኖረውን ሕዝብ ሥነ ልቦና እንደማይገልጽና ፋይዳ ቢስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ጽንፍ በረገጡና የማይታረቅ ቅራኔ ባላቸው ሳይሆን፣ ለዴሞክራሲ በሚመጥኑ ኃይሎች ብቻ ነው፡፡ ይህ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ አገሩ በዴሞክራሲ ጎዳና እንድትጓዝለት አንድነቱና አብሮነቱ መቀጠል አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው! ኢትዮጵያዊነት ታላቅ መስዕዋትነት የተከፈለበት የጋራ እሴት ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...