Friday, April 19, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባና በኢንተቤ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ደቡብ ሱዳን በዕድሜ የዓለም ትንሿ አገር መሆኗና በተወሳሰቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ መዘፈቋ፣ አጎራባች አገሮችና ሌሎች አገሮች ትኩረታቸውን ከእሷ እንዳይነጥሉ ከማድረግ አልገታም፡፡ አገሮቹ በደቡብ ሱዳን በተናጠልና በጋራ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ለደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ጥቅም ሲባል የሚያደርጉት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲጠቅሱ ይሰማል፡፡

በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የደቡብ ሱዳን የቀድሞ ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ጄኔራል ኦያይ ዴንግ አጃክ ግን፣ አገሮቹ ጣልቃ የሚገቡት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በማለም ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ‹‹እየንዳንዱ አገር ከራሱ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር ነው እየሠራ ያለው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ መከራከሪያ በደቡብ ሱዳን ላይ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ላላቸው በርካታ አገሮች የሚሠራ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲፈተሽ ግን በአብዛኛው የብሔራዊ ጥቅም መገለጫን በቀላሉ ማግኘት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተገንጥላ ራሷን የቻለች አገር እንድትሆን ከማንም የተሻለ የሠራች ቢሆንም፣ ከአዲሷ አገር በኢኮኖሚ ሆነ በሌላው ዘርፍ ተጠቃሚ ሆነው የታዩት ያነሰ አስተዋጽኦ ያላቸው እንደ ኡጋንዳ ዓይነት አገሮች ናቸው፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር በበርካታ መሥፈርቶች የተለየና የተወሳሰበ በመሆኑ፣ በሚታዩና በሚዳሰሱ ጥቅሞች ሊገደብ እንደማይችል ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሁለቱ አገሮች ድንበር የሚጋሩና የተረጋጋ ፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ብዙ የሚቀራቸው በመሆኑ፣ አንዳቸው የሌላውን መንግሥት ተቃዋሚ በማስጠለል ጉዳት ለማድረስ መሞከራቸው አንዱ በግልጽ የሚታወቅ ችግር ነው፡፡ አንፃራዊ ሰላም ያላት ኢትዮጵያ ሰላም ከራቃት ዘመን ለቆጠረችው ደቡብ ሱዳን (ሱዳን) የስደተኞች መጠለያ ሆናም ታገለግላለች፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከተጠለሉበት የጋምቤላ ሕዝብ ቁጥር ጋር እኩል ሆኗል፡፡ በጋምቤላ ክልል በስደተኞቹ ተመራጭ የሆነው ደቡብ ሱዳንን ስለሚያዋስን ብቻ አይደለም፡፡ በጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚገኙት የኑዌርና አኙዋ ብሔረሰብ በደቡብ ሱዳንም ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) መሪነት የተካሄደውን የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች የእርቅ ሒደትንም፣ በተወካይዋ አምባሳደር ሥዩም መስፍን መሪነት በበላይነት ስታካሂድ ቆይታለች፡፡ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላም አስከባሪነት ተሰማርተውም ይገኛሉ፡፡

ይህንን የተወሳሰበ ግንኙነት የሁለቱን ወገኖች ፍላጎት ባሟላ መልኩ መፍታት ትልቅ የአመራር ጥበብ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጋር ኢትዮጵያ ያላት ግንኙነትም እንዲሁ ቀላል ነው ተብሎ የሚደመደም አይደለም፡፡ በናይል ፖለቲካ የተፋሰሱ አገሮች ግብፅ አለኝ የምትለውን ‘ታሪካዊ መብት’ በመጠቀም ውኃውን በበላይነት መጠቀሟን አቁማ፣ ምክንያታዊና ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም በአካባቢው እንዲሰፍን ለማድረግ የሚካሄደው ትግል የሚመራው በኢትዮጵያ ነው፡፡ በዚህ ትግል ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚቆጠረው ደግሞ ለበርካታ አሥርት ከግብፅ ጎን የነበረችው ሱዳን የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ጨምሮ በወሳኝነት የኢትዮጵያን አቋም እንድትደግፍ ማድረጓ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ከሱዳን ጋር ጥሩ ግንኙነት መሥርታ በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ሱዳን ላይ ትልቅ ሚና መጫወት መቀጠሏ አገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ላይ አውራ ለመሆኗ ማሳያ ተደርጎ ሲቀርብ የከረመ ቢሆንም፣ አንዳንድ የደኅንነት ተንታኞች ግን በተለይ በደቡብ ሱዳን የውስጥ ፖለቲካ የተዋናዮች መብዛት አንፃር ኢትዮጵያ ነፃና ገለልተኛ ሆና መቀጠል ያዳግታታል በማለት ያላትን ተሳትፎ ልታጤነው ይገባል በማለት ያሳስቡ ነበር፡፡

በድርድሩ መካከል የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ኢትዮጵያ ለዋነኛው ተቃዋሚና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ለዶ/ር ሪይክ ማቻር ታደላለች የሚል ቅሬታ አሰሙ የሚለው ዜና መነጋገሪያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ሆኖ መቀጠል አትችልም ለሚለው ሥጋት ዕውን መሆን እንደ ምሳሌም ቀርቦ ነበር፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ዶ/ር ማቻርን እንደማትቀበል በመግለጽና በቦታቸው በደቡብ ሱዳን መንግሥት የተተኩትን ጄኔራል ታባን ዴንግን እንደምትደግፍ በመግለጽ፣ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ጊዜ አልወሰደችም፡፡

በአፍሪካ የደኅነነት ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ብሩክ መስፍን በዶ/ር ሪክ ማቻር ላይ የወሰደችው የአቋም ለውጥ ዓለም አቀፍ ገጽታ እንዳለው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የኢጋድ የሰላም ሒደትን ስትመራ ነበር፡፡ ነፃና ገለልተኛ በመሆን ሁለቱንም ወገኖች በወታደራዊውም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ስትረዳ ለማስታረቅ ሞክራለች፡፡ ሆኖም መረዳት ያለብን ሁለቱ ዋነኛ የፖለቲካ ተዋናዮች መታረቅ ይፈልጋሉ ወይ የሚለውን ነው፡፡ ተደራድረውና ተፈራርመው ካበቁ በኋላ ጁባ ገብተው የሚሠሩትን ካየን እነዚህ ኃይሎች በቀና ልቦና የሰላም ስምምነቱን መፈጸም አይፈልጉም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ኡጋንዳና ሱዳንን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዶ/ር ማቻርን ከጨዋታው አስወጥቶ ከፕሬዚዳንት ኪር ጋር ብቻ ለመሥራት እንደወሰነ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ እውነታ የተለየ ፖሊሲ ማራመድ ለኢትዮጵያ በጣም አዳጋች እንደሆነም ያመለክታሉ፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ይህን ውሳኔ ሳትወስን አደጋውንም አብራ ልታስብበት እንደሚገባ አቶ ብሩክ ያሳስባሉ፡፡ ‹‹ጄኔራል ታባን ዴንግ ብዙም የማቻርን ኃይል ይዘው ወደ ጁባ አልመጡም፡፡ ማቻርን የሚደግፉ ኃይሎች አሁንም ትጥቅ አልፈቱም፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎት ጋር እየተጋጩ ነው፤›› በማለት የኢትዮጵያና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምርጫ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የማይችልበት ዕድል እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡

ይህ የአቶ ብሩክ ሥጋት መሠረት ያለው ለመሆኑ ማረጋገጫው ባለፉት ጥቂት ቀናት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየከዱ የተቃዋሚውን ጎራ ተቀላቅለዋል የሚል ዘገባ መውጣቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእነዚህ የተወሳሰቡ የፖለቲካ ተቃርኖዎች መሀል በደቡብ ሱዳን ላይ ያላት ትኩረት ባልተገታበት ወቅት ነበር ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አስደንጋጭ የተባለው ዜና በቅርቡ የተሰማው፡፡ ዜናው የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ወደ ካይሮ አድርገውት በነበረው ጉብኝት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ፣ በተለይም የህዳሴ ግድቡን ለአደጋ የሚያጋልጥ ስምምነት ከግብፅ ጋር መፈራረማቸውን የሚገልጽ ነበር፡፡ ከቀናት ዝምታ በኋላ ዜናው መሠረተ ቢስ እንደሆነ መንግሥት ቢያስተባብልም፣ ሥጋትና ጥርጣሬው ግን በኢትዮጵያውያን ዘንድ አሁንም እንዳለ ነው፡፡ በዚሁ ስምምነት የኡጋንዳ እጅ እንዳለበትና ሙሉ ድጋፏን ሰጥታዋለች መባሉም ሌላ ራስ ምታት ነበር፡፡

ይህ ስሜት ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር በአዲስ አበባ ከየካቲት 24 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የተወያዩ ሲሆን፣ በዚሁም ሁለቱ አገሮች የተለያዩ የሁትዮሽ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ ከስምምነቶቹ መሀል ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሁለቱን አገሮች በመንገድ የማገናኘት ፕሮጀክት ግንባታ ነው፡፡ ‹‹ሰላማቸውን መልሰው ሲያኙና ኢኮኖሚያቸው ሲጠናከር ይከፍሉናል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የመንገድ ግንባታ ወጪው በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በኢነርጂ፣ በንግድ፣ በጤናና በኮሙዩኒኬሽንና በሚዲያ ላይም በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በኢነርጂና በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የተደረገው ስምምነት፣ ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ እንድትገዛ የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ውይይትና ስምምነት በደኅንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ የወጡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን ኢኮኖሚያዊ ስምምነቶች ጉልህ ቦታ እንደያዙ ያመለክታሉ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የደኅንነት ተንታኝ በውይይቱና በድርድሩ የፀጥታ ጉዳዮች አለመነሳታቸው ትልቅ አደጋ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹በውይይቱ ላይ ሙሉ መረጃ የለንም ማለት የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ውይይት አለተደረገም የሚለውን አያሳየንም፡፡ ከዶ/ር ማቻር መገለል ጋር የሥልጣን መጋራትና የፌዴራል መዋቅሩ ተትቷል ወይ? የሚለው ላይ ውይይት ካልተደረገ ይገርመኛል፡፡ በደቡብ ሱዳንና በግብፅ መካከል ያለውን ጤናማ ያልሆነ ሐሳብም ሆነ ድርጊት ለመስበር ኢትዮጵያ የተሻለች አጋር እንደሆነች መተማመኛ መስጠትም የጊዜው አንገብጋቢ አጀንዳ ነው፤›› በማለትም በደኅንነት ጉዳይ ላይ ለሚዲያ ባይገለጽም ውይይት መደረጉ እንደማይቀር ገምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከተመሠረተባቸው መርሆዎች አንዱ ከአጎራባች አገሮች ጋር የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር በራሱ የደኅንነት ስትራቴጂ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የደኅንነት ተንታኙ ግን መርሁ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም ኃላፊነት የሚሰማውና ከጊዜያዊ ሥልጣን ባሻገር የሕዝቡን ፍላጎት የሚያሟላ መንግሥት ከሌለ፣ ይህ የፖሊሲ አቅጣጫ በራሱ ምላሽ ሊሆን እንደማይችል ተከራክረዋል፡፡ ‹‹በደቡብ ሱዳን የሥልጣን ሚዛኑ የለየለት ነው ማለት አይቻልም፡፡ ፕሬዚዳንት ኪር ለጊዜውም ቢሆን የተጠናከረ ሥልጣን አላቸው፡፡ ይህ ዘላቂ ካልሆነና ግጭት የሚቀጥል ከሆነ የኢኮኖሚ ትስስሩ በራሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ይበልጥ እንዲጎዳ ሊያደርግም ይችላል፡፡ ግጭቱ ከስደትና ከጦር መሣሪያ ግብይት አንፃር ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያሻክርም የሚችልበት ዕድልም አለ፤›› ያሉት ተንታኙ፣ የኢኮኖሚ ትስስሩ ከደኅንነት መፍትሔዎች ጋር ተቀናጅቶ እንዲከናወን ያሳስባሉ፡፡

አቶ ብሩክም በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ትስስርን እንደ ዘላቂ መፍትሔ መውሰድ የሚቻለው በረጅም ጊዜ እንጂ፣ ለአጭርና ለመካከለኛ ጊዜ ሁሌም ሊሠራ እንደማይችል ያስጠነቅቃሉ፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ ትስስር የረጅም ጊዜ ጥቅም እንዳለው የሱዳንን ልምድ ማየት እንደችላለን፡፡ ሱዳን ለአምስትና ለስድስት አሥርት ከግብፅ ጋር ነበር የምትወግነው፡፡ አሁን ግን የህዳሴ ግድቡ ጥቅሟ ሲሆን አቋሟን ሙሉ በሙሉ ቀየረች፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን ይህ አቀራረብ ሁሉም አገሮች ላይ ሊሠራ እንደማይችል ይሞግታሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከብዙ አገሮች ጋር ትጎራበታለች፡፡ አካባቢው ደግሞ በችግር የተሞላ ነው፡፡ ብዙ የተለያዩ ተዋንያንም ይታያሉ፡፡ ለሁሉም ችግሮች ወጥ የሆነና አንድ ዓይነት መፍትሔ ሊኖረን አይችልም፡፡ ከአገሮች ጋር የኢኮኖሚ ጥቅም መፍጠር ለረጅም ጊዜ ውስጥ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ የተለያዩ መፍትሔዎችን መስጠት ይገባል፡፡ ለአብነትም ወታደራዊ ኃይልንና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይገባል፡፡ የተለያዩ አጋርነቶችንም መፍጠር አለብን፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ምናልባትም ከዚህ ሁሉን አቀፍ አቀራረብ አንፃር ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሁለት ቀን ይፋዊ ጉብኝት በአዲስ አበባ እንደተጠናቀቀ፣ ለሦስት ቀናት ጉብኝት ወደ ኡጋንዳ ዓርብ የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. አምርተዋል፡፡ በጉብኝቱ የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ እንደሚሆን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በናይል ስምምነት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የናይል ስምምነቱን ኡጋንዳ ያልፈረመችው በጉዳዩ ላይ በቂ ስምምነትና ውይይት ስላልተፈጠረ እሱን ለማሳካት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳንና ከኡጋንዳ ጋር ሁኔታዎችን በማርገብ ለመንቀሳቀስ በምትጣጣርበት ተመሳሳይ ወቅት ግብፅ ለደቡብ ሱዳን ችግረኞች ምግብና መድኃኒት ለማጓጓዝ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን መጠቀሟም ተዘግቧል፡፡ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ግብፅ ለሳልቫ ኪር ኃይሎች የጦር መሣሪያ ዕርዳታ ታደርጋለች በማለት በቅርቡ መወንጀላቸው ይታወሳል፡፡

የደኅንነት ተንታኙ ግብፅ በደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ቤዝ በማግኘት ከህዳሴ ግድቡ በቅርብ ርቀት (40 ኪሎ ሜትር) ላይ በመሆን ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠርና መረጃዎችን ለመሰብሰብ ፍላጎት ማሳየቱ የሚገርም እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ለዚህ የኃይል ሚዛን ቀያሪ ፍላጎት አለመሳካት የምትሰጠው ምላሽ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ኡጋንዳ በነፃነት እንደፈለገችው ለመንቀሳቀስ ኢትዮጵያ አላስቻለኝም ብላ የምታምን ከሆነ፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ የማይቀለበስ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የተለያዩ መፍትሔዎችን መሞከሩ የሚበረታታ እንደሆነም አክለዋል፡፡

‹‹ግብፅ ጣልቃ ባትገባ ነው መገረም ያለብን፤›› ያሉት አቶ ብሩክ፣ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ግን ኡጋንዳና ሱዳን መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱ አገሮች ስምምነት የሌላቸው መሆኑም ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት መፍጠሯ ግብፅን ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሳበ አስምረውበታል፡፡

ሱዳን፣ ኡጋንዳና ሌሎች አገሮች ከደቡብ ሱዳን ምን እንደሚፈልጉ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፍላጎት በግልጽ እንደማይታወቅም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የወጣው እ.ኤ.አ. በ2002 ነው፡፡ በተወሰነ መልኩ እ.ኤ.አ. በ2009 ተሻሽሏል፡፡ ደቡብ ሱዳን ደግሞ ነፃ አገር የሆነችው እ.ኤ.አ. በ2011 ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚያ በኋላ የተፈጠሩ ለውጦችን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ጠቅለል ያለ ፖሊሲ በደቡብ ሱዳን ላይ ልታወጣ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -