– የህዳሴውን ግድብ ለማጥቃት የተንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ከኤርትራ መነሳቱ ተጠቆመ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በጄኔቫ (ስዊዘርላንድ) ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠቱ ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሒሩት ዘመኔ ባለፈው ሳምንት በጄኔቫ በተካሄደው የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ተገኝተው፣ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን፣ የውጭ ዳዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
አቶ ተወልደ ዓርብ የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስረዱት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የእያንዳንዱ አገር የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በሚዳሰሱበት ጉባዔ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፣ ሚኒስትር ዴኤታዋ በተለይ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከት ስለተወሰዱ ዕርምጃዎችና የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ተጠናቅሮ ለፓርላማ ስለቀረበው ሪፖርት፣ እንዲሁም በቀጥታ ለምክር ቤቱ የሚቀርበውን ሪፖርት አስመልክተው ንግግር አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ጀምሮ፣ የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሰዎችን ሰብዓዊ መብት እንዳይጣሱ፣ በገለልተኝነት የሚከታተል ኮሚቴ ተዋቅሮ ሪፖርት ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ዝርዝሩን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ኦፊሴላዊ ጉብኝት ያደረጉት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤላን ጆንሰን ሲርሊፍ ጉብኝትን በተመለከተ አቶ ተወልደ አስረድተዋል፡፡
ሐዋሳና ዱከም አካባቢ ያሉ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን የጎበኙት የላይቤሪያዋ ፕሬዚዳንት፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ልምድ ለመቅሰምና ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ልውውጥ ለማጠናከር ያላት ፍላጎት መሠረት ያደረገ ጉብኝት እንደነበር አቶ ተወልደ አክለዋል፡፡
በቅርቡ የቤንሻንጉል ታጣቂ ቡድን አባላት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸውም ተናግረዋል፡፡ አቶ ተወልደ እንደሚሉት፣ ታጣቂዎቹ ሥልጠና የወሰዱትና የጥፋት ተልዕኮ የተሰጣቸው ከኤርትራ መንግሥት ቢሆንም፣ ግድቡ ያለበት ቦታ ላይ ሳይደርሱና ምንም ጉዳት ሳያደርሱ በተወሰደባቸው ዕርምጃ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት መግለጫ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ ከኤርትራ የተነሱ 20 የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ አባላት መንገድ ላይ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡ በዕርምጃው 13 ታጣቂዎች ሲደመሰሱ፣ ሰባቱ ወደ ሱዳን ቢሸሹም የሱዳን መንግሥት ለኢትዮጵያ አሳልፎ መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡ የታጣቂዎቹ ዓላማ ግድቡ ላይ ጉዳት ለማድረስ ቢሆንም፣ በፀጥታ ኃይሎች ከሽፏል ሲሉ አክለዋል፡፡ በዚህ ሙከራም የሻዕቢያ እጅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግን አስተባብሏል፡፡ እንዲህ የሚባል ታጣቂ አላውቅም ብሏል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ታጣቂ ቡድኑ ኤርትራ ውስጥ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በጥቃት ሙከራው የሻዕቢያ እጅ እንዳለበት ያረጋግጣል በማለት አስታውቋል፡፡