Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሐይኒከን በሦስቱም ቢራ ፋብሪካዎቹ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ተከለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የቂሊንጦ አካባቢ ነዋሪዎች የሚለቀቀው ፍሳሽ ጉዳት እያደረሰብን ነው አሉ

የኢትዮጵያ የቢራ ኢንዱስትሪን የተቀላቀለው ሐይኒከን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ኩባንያ፣ በሦስቱም ቢራ ፋብሪካዎቹ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ማቋቋሙን አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 (ቂሊንጦ) በገነባው ፋብሪካ በ176 ሚሊዮን ብር ግዙፍ የፍሳሽ ማጣሪያ ገንብቶ ሥራ ላይ ቢያውልም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚወጣው ፍሳሽ ሽታ ያለው በመሆኑ መቸገራቸውን በመግለጻቸው፣ ተጨማሪ ወጪ በማውጣት ፍሳሹ ከነዋሪዎቹ ክልል እስኪርቅ ድረስ በቱቦ ለማሳለፍ አዲስ ፕሮጀክት መቅረጹንም ሐይኒከን አስታውቋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በሁለት ዙር በቂሊንጦ የገነባው የቢራ ፋብሪካ በዋልያና በሐይኒከን የንግድ ስያሜ ሦስት ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም አለው፡፡ ሐይኒከን ለግንባታው አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ሐይኒከን ከመንግሥት የገዛቸው የሐረርና የበደሌ ቢራ ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው 500 ሺሕ በድምሩ አንድ ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ቢራ የሚያመርቱ በመሆናቸው፣ በአራት ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የቢራ ፋብሪካ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ሐይኒከን ቢራ ፋብሪካ በኢትዮጵያ የቢራ ገበያ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ የገባ ሲሆን፣ በንግድ ድርሻውም ከቢጂአይ ኢትዮጵያ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ) ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ግዙፍ የቢራ ፋብሪካ በሦስቱም ቢራ ፋብሪካዎቹ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ቢገነባም፣ አዲስ አበባ በሚገኘው ፋብሪካ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታ አሰምተዋል፡፡

አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ካሉት 11 ወረዳዎች ውስጥ ሐይኒከን ቢራ የሚገኝበት ወረዳ ዘጠኝ ወይም ቂሊንጦ አካባቢ ሰፊና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያሉበት ነው፡፡

ለአብነት ያህል የአዲስ አበባ ከተማ የሚያካሂዳቸው ግዙፎቹ ኮዬ ፈጬና ቱሉዲምቱ የኮንዶሚንየም ሳይቶች በአካባቢው ይገኛሉ፡፡ የአይሲቲ ፓርክ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትም እዚሁ አካባቢ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ አካባቢው ወደ ከተማነት እየተቀየረ ቢሆንም በርካታ አርሶ አደሮችም አሉ፡፡

የሐይኒከን ቢራ ፋብሪካ ተረፈ ምርት በዘመናዊ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ተጣርቶ የሚወጣ ቢሆንም፣ ወደ አቃቂ ወንዝ እስኪገባ ድረስ በክፍት ቱቦ የሚጓጓዝ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችና በአካባቢው የሚገኘው ትምህርት ቤት ሽታው ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጋቸው መሆኑን በመግለጽ መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቀዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሉ ጌቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በታችኛው ቂሊንጦ የሚገኙ ነዋሪዎች ሽታው እያስቸገራቸው መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ አቶ ኃይሉም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

ይህንን ጉዳይ ለመቅረፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ችግሩን እንዲያጠኑት መደረጉን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ ችግሩንም ለመፍታት ከሐይኒከን ቢራ ፋብሪካ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

የሐይኒከን ቢራ የቂሊንጦ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ምትኩ እንዳብራሩት፣ ፋብሪካው ተረፈ ምርቱን በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ ባለ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ በማጣራት ምንም ጉዳት የማያመጣ ንፁህ ውኃ ይለቃል፡፡ አንድ ሊትር ቢራ ለማምረት እስከ አምስት ሊትር ድረስ ውኃ ጥቅም ላይ እንደሚውል አቶ አንተነህ ገልጸው፣ የሚለቀቀው ፍሳሽ በጤና ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያመጣ አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ነዋሪዎች ጉዳዩን እንደ ችግር በማንሳታቸው ተጣርቶ የሚለቀቀው ፍሳሽ ከነዋሪዎች መንደር እስኪርቅ ድረስ በዝግ ቱቦ ለማስተላለፍ፣ ፕሮጀክት መንደፉን አቶ አንተነህ አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ግንዛቤና ብክለት ቁጥጥር ቡድን አስተባባሪ አቶ ለሜሳ ጉደታ እንደተናገሩት፣ የሐይኒከን ቢራ ፋብሪካ ተረፈ ምርቱን ከመጀመሪያው ጀምሮ እየለየ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ያስወግዳል፡፡ ‹‹ፍሳሽ ቆሻሻውንም እንዲሁ ከሌሎች ፋብሪካዎች በተለየ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ጉትጎታ ሳይጠብቅ በራሱ መንገድ የኅብረተሰብን ጤንነት፣ የአካባቢን ደኅንነት በጠበቀ ሁኔታ እያስወገዱ ነው፤›› ሲሉ አቶ ለሜሳ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች