Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሸገር የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ጀመረ

ሸገር የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ጀመረ

ቀን:

– የ100 አውቶቡሶች ግዢ ተፈጽሟል

ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በመጪው በጀት ዓመት የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ገብሬ እንደገለጹት፣ በ2010 በጀት ዓመት ይጀመራል ተብሎ ለሚታሰበው የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ድርድርና ምክክር እየተደረገ ነው፡፡

ግዢ ከተፈጸመባቸው 100 ለተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የትምህርት ቤት አውቶቡሶች ‹‹ስኩል ባስ›› ውስጥ 60ዎቹ ለሁለተኛ እንዲሁም 40ዎቹ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚውሉ ሲሆን፣ የአንዱ አውቶቡስ ርዝመትም አሥር ሜትር ነው፡፡

ድርጅቱ ከሌሎች የትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ጎን ለጎን የብዙኃን፣ የፈጣንና የተማሪ ትራንስፖርት አገልግሎት ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ መስጠትን ዓላማ አድርጎ በ2008 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን፣ ባለፉት ስምንት ወራት በተለይ ትኩረት ሰጥቶ የተንቀሳቀሰው በብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡

የመሠረተ ልማት አውታሮች ሲሟሉ የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፣ ከቀጣይ ዓመት ዕቅዱ ደግሞ በከተማዋ በትራንስፖርት ዘርፉ ያለውን ችግር ከመቅረፉና አማራጭና ተመራጭ ሆኖ ከመቅረብ ጋር በተያያዘ የተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት አንዱ ነው፡፡

የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳነ አብደታ እንዳስታወሱት፣ ድርጅቱ 300 የመደበኛ አውቶቡሶች ግዢ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ፈጽሟል፡፡ እስካሁን 210ሩን የተረከበ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ መስመር ላይ እየሠሩ የሚገኙት 108 ናቸው፡፡

30 አውቶቡሶች ደግሞ በግጭት ምክንያት ለሰርቪስ የቆሙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ የኢንሹራንስና አይሲቲ ተሟልቶላቸው በቅርቡ ሥራ ላይ ይገባሉ ተብሏል፡፡

ድርጅቱ እስከ የካቲት አጋማሽ 2009 ዓ.ም. ድረስ 19 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጉን፣ ይህም ከታሰበው በታች መሆኑን አቶ ተስፋዬ አውስተው፣ ለዚህም ተለዋዋጭ ታሪፍ ሥርዓት መዘርጋታቸው፣ የቁጥጥር ሥርዓት ላይ ክፍተት መኖሩና በሙሉ አቅማቸው አለመሥራታቸው እንደምክንያት ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ከተለዋዋጭ ታሪፍ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ተገልጋዩ የአጭር ርቀት ዋጋ ከፍሎ ሩቅ መጓዝ እንዲሁም አንዳንዴ ሳይከፍል መጓዙ እንደ ችግር በመስተዋሉ የቁጥጥር ሥርዓት አጠናክረው እንደሚዘረጉ ከዚህ ጎን ለጎንም ኅበረተሰቡ አለአግባብ የሚጓዙትን እንዲከላከል የሥራ ኃላፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

ባሉት አውቶቡሶች ልክ በፍጥነት ወደ ገበያ እንዳይገቡ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አውቶቡሶቹ በሚጠይቁት ደረጃ አሽከርካሪዎችን አለማግኘት አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ፣ 30 አውቶቡሶች ለጥገና የቆሙትም ከአሽከርካሪ ብቃት ማነስ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ ግጭቶች እንጂ ሌላ የቴክኒክ ችግር በአውቶቡሶቹ ላይ ተከስቶ አይደለም፡፡

ከአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍም ከአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር በመነጋገር፣ በማንኛውም የማሽከርከር ደረጃና ክህሎት ላይ የሚገኙ 3000 ሰዎችን የመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ድርጅቱ የሚፈልገውን መስፈርት የሚያሟሉትን ተጨማሪ ሥልጠና ሰጥተውና ክህሎት አላብሰው ወደ ሥራው ለማስገባት ሥራ መጀመራቸውን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአዛውንቶች፣ ለሕፃናት፣ ለነፍሰጡሮችና በአጠቃላይም ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ምቹ ተደርገው የተሠሩት ሸገር አውቶቡሶች፣ በየመንገዱ ባዶዋቸውን እየሄዱ ሰው አይጭኑም በሚል በተደጋጋሚ በተጠቃሚዎች ሲወቀሱ ይሰማል፡፡

ይህንን አስመልክቶ በድርጅቱ የዋና ሥራ አስኪያጁ አማካሪ አቶ ኑረዲን ሙስጠፋ እንዳሉት፣ እያንዳንዱ አውቶቡስ 42 መቀመጫ አለው፡፡ ከሚቀመጡት በተጨማሪ 28 ሰዎች እንዲቆሙ በማድረግ በአጠቃላይ 70 ሰዎች ብቻ እንዲጭኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ለተመልካች ዓይን አውቶቡሶቹ ባዶዋቸውን የሚጓዙ ቢመስልም ለደኅንነት፣ ለምቾትና ተሳፋሪዎችን ላለማስጨነቅ ሲባል የተደረገ ነው፡፡

በግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሥራ የጀመረው በአንድ መስመርና በአሥር አውቶቡሶች ነበር፡፡ አሁን ላይ በ108 አውቶቡሶች፣ በ11 መደበኛና በ12 ልዩ በአጠቃላይ በ23 መስመሮች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...