Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዓድዋ አከባበር አዳዲስ ገጽታዎች

የዓድዋ አከባበር አዳዲስ ገጽታዎች

ቀን:

ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ዙሪያ የዓድዋ ድል 121ኛውን ዓመት ለማክበር የካቲት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. የተሰባሰቡት አርበኞችና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በቦታው የተገኙት ማልደው ነበር፡፡ አርበኞች በሐውልቱ ዙሪያ በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡ ከመሀከላቸው አልፎ አልፎ ወደ አደባባዩ እየገቡ የሚፎክሩም ነበሩ፡፡ የአገሪቱን ዳር ድንበር እንደማያስደፍሩ የሚገልጹና ወራሪ ኃይልን የሚኮንኑ ግጥሞች ተጠምደዋል፡፡ አብዛኞቹ አርበኞች በዕድሜ እንደመግፋታቸው በቤተሰቦቻቸው ድጋፍ በቦታው የተገኙ ነበሩ፡፡ ሆኖም የዕድሜና የጤና ጉዳይ ወኔያቸውን ፈጽሞ እንዳልተፈታተነው ይታያል፡፡

ንጋት ላይ የዓድዋ ድልን የሚያወድሱ ጽሑፎች የታተሙባቸው ተመሳሳይ ካናቴራዎች የለበሱ ወጣቶች የአርበኞቹን ክበብ ይቀላቀሉ ጀመር፡፡ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ‹‹ዓድዋ›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ተመሳሳይ ካናቴራ ያደረጉትን ወጣቶች የባህል ልብስ የለበሱ ወጣቶች በሞተር ሳይክል ተቀላቅለዋቸው አደባባዩን ሞተር ላይ ሆነው እየዞሩ ዓድዋ የሚል ሠንደቅ ዓላማ ያውለበልቡም ነበር፡፡፡ ከንኬል የተሠራ ጎራዴ የያዙ ታዳጊ ወንዶችና ሴቶች እየፎከሩ ወደ አደባባዩ ገቡና ክብ ሠርተው ለረዥም ደቂቃ ሽለላና ቀረርቶ ያሰሙ ጀመር፡፡ ወደ ጦርነት እንደሚሄድ ሰው አገልግል የተሸከሙ ሴቶችም ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ዘማቾች ለማስታወስ ፊታቸውንና ልብሳቸውን ቀይ ቀለም ተቀብተው ባዶ ይፎክሩ የነበሩት የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል፡፡ በተዋናይ ሚካኤል ሚሊዮን የሚመራው ቡድን ደግሞ ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ እንዲሁም ቀሳውስትና ዘማቾችን የሚወክሉ ተዋንያንን ወደ ስብስቡ አክሏል፡፡

በታሪክ ድርሳናት ካነበቡትና ከታላላቆቻቸው ከሰሙት የጀግንነት ታሪክ በመነሳት የዓድዋ ጦርነት ምን ይመስል እንደነበረ ምናባዊ ምስል ለመፍጠር እየሞከሩ የነበሩት ወጣቶች ትርዒት በአንድ ጽንፍ በሌላ በኩል አርበኞች ይታያሉ፡፡ የዓድዋ ድል በየዓመቱ ሲከበር በወጣቱ ዘንድ ተገቢው ትኩረት እንደተነፈገው በመግለጽ ወጣቶችን የሚተቹ በርካቶች ቢሆኑም፣ በቦታው የተገኙት ወጣቶች የሚያሳዩትና የሚታዩባቸው ነገር የሚያሳየው ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በእርግጥ በራሳቸው ተነሳሽነት በዓሉን ለማክበር ረዘም ላለ ጊዜ ዝግጅት አድርገው በቦታው የተገኙ ወጣቶች ብዙኃኑን የዕድሜ አቻዎቻቸውን ይወክላሉ ለማለት ይከብዳል፡፡ የነሱ ጅማሮ መልካም ሆኖ ሳለ አብላጫውን ቁጥር የያዙ ወጣቶች ለአገሪቱ ታሪክ ብዙም ግድ እንደሌላቸው የሚያምኑ በርካቶች ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዓድዋ ድል የሚከበርበትን ቀንና ምክንያት እንዲሁም ድሉ ለአገሪቱና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ያበረከተውን አስተዋጽኦ ጠንቅቀው የሚያውቁ ስንቶች ናቸው? ታሪካዊ ዳራውን ከመፈተሽ በተጨማሪ እንደ በዓል የሚያከብሩትስ? ጥያቄዎቹ የሚነሱት በኅብረተሰቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ጭምር ነው፡፡ በዓሉ በቂ ትኩረት ተሰጥቶት ክብሩን በሚመጥን ድምቀት ይከበራል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ በዓሉ ሲደርስ የውይይት መድረኮችና ልዩ ልዩ ዓውደ ርዕዮች ከማዘጋጀት ባለፈ ድሉ በቋሚነት የሚታወስበት አንዳች ነገር አለመኖሩም ያጠያይቃል?

በበዓሉ ዋዜማ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ጽሑፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚናገሩት፣ የዓድዋ ድል  እንደ አገራዊ ቅርስነቱ ቋሚ ሐውልት አልተሠራለትም፡፡ በዓሉ በአንድ ዓመትና በሌላው ያለው የአከባበር ድምቀትም ይለያያል፡፡ ሞቅ ባለ ሁኔታ የሚከበርበትና ቀዝቀዝ የሚልበትም ወቅት አለ፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት የዓድዋ ድል 100ኛ ዓመት አከባበርን ነው፡፡ ከ21 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተውጣጡ አጥኚዎች የተሠሩ 60 የጥናት ጽሑፎች ታትመው ነበር፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀው የስዕል ዐውደ ርዕይ በበርካቶች የተጎበኘም ነበር፡፡ በዛ ዓመት በዓሉ ትኩረት ተሰጥቶት በድምቀት ከመከበሩ ባሻገር፣ መንግሥት በዓሉን ለመዘከር መታሰቢያዎችን ለመገንባት ቃል እንደገባም ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ዓድዋ አካባቢ ፓርክ ይሠራል ተብሎ አልተሠራም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የአድዋ ፓርክ ይቋቋማል ተብሎ ወዲያው ተረሳ፡፡ ዓድዋ አደባባይ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ወደ ዳያስፖራ አደባባይ ተለወጠ፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ፕሮፌሰር ባህሩ እንደሚገልጹት፣ ለዓድዋ ድል ቦታ የሚሰጡ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ብዙ ይቀራል፡፡ ዓድዋ አካባቢ ታሪኩን የሚያሳይ በግልጽ የሚታይ (ኦፕን ኤር ሙዚየም) እና ሐውልት የመሥራት ዕቅድ እንዳለ ብዙ ጊዜ ቢነገርም የተጀመረ ነገር የለም፡፡ በቅርቡ የፓን አፍሪካን ስተዲስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም ከተጀመረው እንቅስቃሴ ውጪ ተጨባጭ ነገሮች አይታዩም፡፡ ‹‹ምን ተሠርቷል ሲባል መልስ አይኖረንም፤›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ታሪኩን የሚያወሳ ነገር መገንባት እንደሚያሻ በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡ በዓሉ ከዓመት ዓመት ያለው አከባበር አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ የሚል ሳይሆን፣ ወጥ በሆነ መንገድ መካሄድ እንዳለበትም ያክላሉ፡፡

የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል ካለፉት ጥቂት ዓመታት በተሻለ በደመቀ ሁኔታ መከበሩን የሚገልጹ አሉ፡፡ በአዲስ አበባ፣ በዓድዋና በሌሎች አካባቢዎችም በዓሉ በልዩ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ በአዲስ አበባው አከባበር የከተማው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ተወካይ አቶ ጌታቸው ወረደ ሲገኙ፣በዓድዋው አከባበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ታቦ ምቤኪና ሌሎችም ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡

በዓሉን የሚታደሙ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ደረጃ ለበዓሉ የሚሰጠውን ቦታ በማመላከት ረገድ የሚሰጠው ዋጋ እንዳለ ሆኖ የተቀረው የማኅበረሰቡ ክፍል ለበዓሉ ምን ያህል ቦታ ይሰጠዋል? የሚለው አነጋጋሪ ነው፡፡ በተለይም ወደ ወጣቱ ትውልድ ሲመጣ ወቀሳው ይጠነክራል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ለበዓሉ ልዩ ልዩ ትርዒት አዘጋጅተው ከነበሩ ወጣቶች መሀከል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የትችቱን እውነተኛነት ይስማሙበታል፡፡ ሆኖም ቁጥራቸው ቢያንስም ለዓድዋ ድል ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡ ወጣቶች መኖራቸው ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ያምናሉ፡፡

ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የሚኖሩ የአንድ ሠፈር ልጆች ‹‹ኢትዮጵያ  አገሬ የአፍሪካ መቀነት፣ የነፃነት ዓርማ የሉዓላዊነት›› የሚል ካናቴራ አሠርተው በኅብረት በዓሉን እያከበሩ ነበር፡፡ ከሠፈሩ ልጆች አንዷ ቤተል ጥበቡ እንደምትናገረው፣ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ አገሮች በአጠቃላይ የነፃነት ብርሐን የፈነጠቀችበት እንደመሆኑ በዓሉን የሚያከብሩ ወጣቶች መበራከት አለባቸው፡፡ ጥረት የሚያደርጉ ወጣቶች ጥቂት ስለሆኑ ‹‹ከዚህም በላይ ብዙ መሆን አለብን፤›› ትላለች፡፡

የተግባረዕድ የኅብረ ቀለም የኪነ ጥበብ ቡድን አባል የሆነው የትምህርት ቤቱ ሀርድዌርና ኔትወርኪንግ ሰርቪስ ተመራቂ ተማሪ ዘካሪያስ ናስር፣ ‹‹ከ121 ዓመታት በፊት አገራችንን ጠብቀው ከቅኝ ግዛት ባይታደጉን እኛ እዚ አንገኝም ነበርና ለውለታቸው ምላሽ ክብር መስጠት አለብን፤›› ይላል፡፡ ኃላፊነቱን ወስደው እንቅስቃሴ ማድረግ ያለባቸው ወጣቶች እንደሆኑም ይገልጻል፡፡

አስጎብኚዎች ተሰብስበው የመሠረቱት ቀዳማይ አገርህን ዕወቅ ክበብ አባል ፍሬሰናይ በበኩሏ፣ ተተኪውን ትውልድ መቅረጽ የቀደምቶች ኃላፊነት ነው ትላለች፡፡ ቤተሰብ ልጆቹን ከማስተማር አንስቶ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ገልጻ፣ ‹‹ከፊት ሆኖ መንገድ እየጠረገ የሚያሳይ ያስፈልጋል፡፡ ታሪኩ በትምህርት ሥርዓቱም ሰፊ ሽፋን ሊሰጠው ይገባል፤›› ትላለች፡፡

የዓድዋ ድል በተከበረበት ዕለት በጦርነቱ ወቅት እንደነበረው ለብሰው (ጎፈር ደፍተው ካባ ደርበው) ባዶ እግራቸውን እየሄዱ ጡሩንባ የሚነፉ ሕፃናት ነበሩ፡፡ ልጆቹ ታሪኩን በየዕድሜ ደረጃቸው በጥልቀት እየተረዱት እንዲያድጉ የማድረግ ተስፋ እንዳለም ይታያል፡፡ በተቃራኒው በዓድዋ ድል ዋዜማ ፒያሳ የሚገኝ አንድ የልብስ ሱቅ ውስጥ የተፈጠረውን ማንሳት ይቻላል፡፡ እግረ መንገዱን ወደ ሱቁ ጎራ ያለ ጎልማሳ አንድ ልብስ ላይ ቀልቡ ቢያርፍም በኪሱ የያዘው ገንዘብ ስላልበቃው ሻጩን በነጋታው እንደሚመለስ ነግሮት ከሱቁ ሊወጣ ሲል እያቅማማ በነጋታው ዓድዋ በመሆኑ ሱቅ ይዘጋ እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ሻጩ በንቀት አዘል ድምጽ ‹‹አድዋ ለኔ ምኔም አይደለም›› ሲል መለሰለት፡፡

በተመሳሳይ ቦሌ የሚገኝ አትክልት ቤት ውስጥ ይመገቡ የነበሩ ሁለት ሴቶች በቀጣይ የሚገናኙበትን ቀን ለመወሰን ይነጋገራሉ፡፡ አንዷ ሐሙስ (የካቲት 23) ለበዓል ሥራ ስለማይኖር መገናኘት እንደሚችሉ ገለጸች፡፡ ሌላዋ ምን በዓል አለ? ብላ  ስትጠይቅ የመጀመሪያዋ ሴት ግራ በመጋባት ‹‹የሆነ በዓል›› ከማለት ያለፈ ነገር አላለችም፡፡ በዓሉን ማክበሩ ቀርቶ የበዓሉ ምንነት ያሳሰባቸው አይመስልም፡፡ የቀኑ ለነፃነት የተከፈለ የደም ዋጋ ከመሆኑ ይልቅ የዕረፍት ቀን አድርገው በማሰብ የሚደሰቱ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ዓድዋ አደባባይ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችና የካቲት 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ሳይቀሩ ስለሚኖሩበት ሠፈር ወይም ስለትምህርት ቤታቸው መጠሪያ መረጃ እንደሌላቸውና እንደማይጠይቁም የታዘቡ ጋዜጠኖች ሰሞነኛ አጀንዳቸው አድርገውታል፡፡

ግድየለሽነቱ በየካቲት 23 ብቻ ሳይሆን የካቲት 12ና ሚያዚያ 27 ለምን እንደሚከበሩ አለማወቅን ያካትታል፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ዓድዋ በተካሔደው አከባበር እንደተናገሩት፣ ለድል በዓላቱ ተገቢው ትኩረት መሠጠት አለበት፡፡ በቀጣይ የሚከበረው ሚያዚያ 27 የድል በዓል አንዱ ዓድዋ ድል ሕዝቡ በኅብረት ሊያከብረው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ቂም ቋጥሮ ከዓድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ አገሪቱን የወረረው ፋሺስት ኢጣሊያ ድል የተነሳበት ዕለት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት እንዲቸረው የጠየቁ ሲሆን፣ የአርበኞች ተጋድሎ ቦታ እንዲሰጠውም አሳስበዋል፡፡ በተያያዥም ወጣቱ ትውልድ ስለ አገሩ ታሪክ የሚያውቅበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት አክለዋል፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ዓድዋ የእግር ጉዞ በማድረግ በዓሉን ከሚያከብሩት አንዱ የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ ሲሆን፣ ዘንድሮም ጉዞው በ46 ቀናት መጠናቀቁን ይገልጻል፡፡ የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል ደማቅ እንደሆነና ኅብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር ያሳየው ተነሳሽነት እንደሚያስደስትም ይናገራል፡፡ ሆኖም መንግሥት በዓሉን ለማክበር የተያያዘው አቅጣጫ ላይ ጥያቄ አለው፡፡ በዓሉን በማስታከክ መንግሥት ወቅታዊ የሚላቸውን አጀንዳዎች አያይዞ ማንሳቱ በዓሉን እንደሚያደበዝዘው ያምናል፡፡ ጉዳዮቹ አገራዊ ቢሆኑም መነሳት ባለባቸው መድረክ ተነስተው በዓድዋ ዕለት ድሉ የበለጠ ቢጎላ ይመረጣል ይላል፡፡ ‹‹ድሉ ጎልቶ ሲነገር የሚፈጠረው ብሔራዊ ስሜት ለታሪክና ለባህሉ ቦታ የሚሰጥ ትውልድ ያፈራል፤›› ይላል፡፡ በዓድዋ ዕለት ድሉ ስላመጣቸው አወንታዊ ነገሮች በስፋት ሲነገር የሚፈጥረው ኅብረት ሕዝቡ የሚነሱትን አጀንዳዎች ወቅታቸውን ጠብቆ እንዲያነሳ ጉልበት ይሰጠዋል ሲልም ይናገራል፡፡

በዘንድሮው የዓድዋ ክብረ በዓል ለየት ካሉት ነገሮች መሀከል ያሬድ መቐለ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ቀድሞ የጣሊያን ምሽግ የነበረው ቦታ ተከልሎ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚመረቅ ይጠቁማል፡፡ በጦርነቱ ወቅት ጣልያኖች ወደሠሩት ምሽግ የኢትዮጵያ ጦር ሲጠጋ ጣልያኖች ባጠሩት ብረትና ሹል እንጨት ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ብዙዎች ሲሆኑ፣ ቅሪተ አካላቸው በክብር አልተቀመጠም ነበር፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከመቐለ ኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ቦታው ታጥሮና በአካባቢው የነበረውን ምሽግ የሚወክል ምሽግ ተሠርቶ መስዋዕትነት ለከፈሉት ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ እንዲሆን ዕቅድ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያኑ ቅሪተ አካል ተሰብስቦ የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈፀመ ሲሆን፣ አካባቢው ታጥሮና የተጀመሩት ግንባታዎችም ተጠናቀው ዘንድሮ ይመረቃል፡፡ አካባቢው በትግራይ ክልል የቱሪዝም ካርታ እንደሚካተትም ተናግሯል፡፡

በተመሳሳይ ዓድዋ ላይ ይሠራል እየተባለ በየጊዜው ቢነገርለትም መሬት ወርዶ ያልታየው መታሠቢያ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡  የዘንድሮውን በዓል ለማክበር የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር በርካታ ነበርና በሚቀጥለው ዓመትስ ይደገም ይሆን? ሲሉ የሚጠይቁም አሉ፡፡ ዘንድሮ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ከታየው ሰው ብዛት በተጨማሪ፣ እስከ ዓድዋ አደባባይ ድረስ የተደረገው የእግር ጉዞም ይጠቀሳል፡፡ በዓሉ ላይ መሶብና ቅል  እንዲሁም ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች ይዘው ትርዒት ያቀረቡ ወጣቶችም አይዘነጉም፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...