Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ዕገዳና የብሔራዊ የእግር ኳስ ዳኞች ኮሚቴ ቀጣይ ዕርምጃ

የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ዕገዳና የብሔራዊ የእግር ኳስ ዳኞች ኮሚቴ ቀጣይ ዕርምጃ

ቀን:

ለእግር ኳስ ዕድገት አንዱና መሠረታዊ ተብለው ከሚጠቀሱ ግብዓቶች የእግር ኳስ ዳኝነት ተጠቃሽ መሆኑ አያከራክርም፡፡ የእግር ኳስ ዳኝነት ቅፅበታዊ ውሳኔ የሚያስፈልገው እንደመሆኑ መጠን ምንም እንኳ በስህተት የተሞላ ቢሆንም አሁንም ግን የአስፈላጊነቱ ጉዳይ ለድርድር ሳይቀርብ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ዘርፉ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካ ፋይዳው እየጎላ መምጣቱ ተከትሎ አሁን አሁን ሰዋዊ በሆነው የእግር ኳስ ዳኝነት ላይ ስህተቶች ሲፈጠሩ የሚያስከትለው ጥፋትም በዚያው መጠን እየጨመረ መጥቷል፡፡

ይህ በተለይም ኢትዮጵያን ለመሰሉ እግር ኳሳቸው ባላደገባቸው አገሮች የሚያስከትለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዲህ በቀላሉ ሊገመት እንደማይችል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመደበኛነት ከሚያስተዳድራቸው ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሊግ ውድድሮችን መመልከቱ በቂ ይሆናል፡፡ ቡድኖች በየትኛውም መመዘኛ ከእግር ኳስ ዳኝነት ጋር ተያይዘው ለሚፈጠሩ እሰጣ አገባዎች የተመቻቹ ናቸው፡፡ ቡድኖች ህልውናቸው በእግር ኳስ ዳኞች እጅ ላይ መሆኑን ካመኑ ውለው አድረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዘንድሮን ፕሪሚየር ሊግ ግማሽ የውድድር ዓመት የዕቅድ ክንውን ግምገማ የካቲት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በወላይታ ድቻ ከተማ አድርጎ ነበር፡፡ በግምገማው የተሳተፉ ሁሉም ክለቦችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ይህ ቀረሽ የማይባል የአደረጃጀትና የአሠራር ክፍተት ያለባቸው ክለቦች ሳይቀር ጣታቸው በእግር ኳስ ዳኝነት ላይ ሲያነጣጥሩ ታይተዋል፡፡

የእግር ኳስ ዳኝነት ስህተትን መቀነስ ካልሆነ ክለቦችና የክለብ አመራሮች እንደሚናገሩት ከስህተት ፍፁም የፀዳ የዳኝነት ሥርዓት አሁን አይደለም ወደፊትም እንደማይኖር የእግር ኳስ ዳኞችና ከሙያው ጋር ተያያዥነት ያላቸው ባለሙያተኞች ይከራከራሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ የእግር ኳስ ዳኞች ኮሚቴ ችግሩን የጋራ አድርጎ መውሰድ እንደሚገባ ያምናል፡፡ ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴው እግር ኳሱ ባደገባቸው የአውሮፓ አገሮች ሰዋዊ በሆነው የዳኝነት ሥርዓት የፈጠረውን ስህተት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የቴክኖጂ ውጤቶችን ተጠቅመው እንኳን ስህተቶች አሁንም በጉልህ እየታዩ መሆኑን ጭምር በማሳያነት ያስቀምጣል፡፡ በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ በጋሻውን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት የእግር ኳስ ዳኞች የብቃት ደረጃ ወሳኝነት እንዳለው ይታመናል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሊግ ደረጃ ከእግር ኳስ ዳኝነት ጋር ተያይዞ ብሶትና እሮሮ ይደመጣል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ልዑልሰገድ፡- እንደሚታወቀው በአገሪቱ ያለው የሊግ አደረጃጀት እየሰፋና እየጨመረ መጥቷል፡፡ ፌዴሬሽኑም ይህንኑ ማስተናገድ የሚችሉ የእግር ኳስ ዳኞችን ዓይነት፣ ብቃትና መጠንም እያሳደገ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ350 በላይ የእግር ኳስ ዳኞችና ከ150 በላይ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች እንዲፈሩ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ የእግር ኳስ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች መካከልም ጨዋታ የመዳኘትና የመምራት ብቃታቸው እየታየ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ለአህጉርና ለኢንተርናሽናል ጨዋታ ዳኝነት የሚያበቃቸውን የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት (የዳኝነት ባጅ) እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ እንደነ ባምላክ ተሰማና ሊዲያ ታፈሰን የመሳሰሉት በአህጉራዊም ሆነ ኢንተርናሽናል መድረኮች በጥሩ ብቃት ጨዋታዎችን መምራት መቻላቸው ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ እስካሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረት ሰባት ዋናና ሰባት ረዳት ዳኞች ማስመረጥ ችለናል፡፡ በተመሳሳይ ሴቶችም አራት ዋናና አራት ረዳት ዳኞች የፊፋን ደረጃ እንዲያሟሉ ተደርጓል፡፡ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ ናቸው፡፡ የእግር ኳስ ዳኞቻችን በብዛትም በጥራትም ለአህጉራዊው ውድድር እየበቁ ነው፡፡ በቂ ነው ብለን ግን አናምንም፡፡ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በአገር ውስጥ ለሚደመጠው የዳኝነት ጉዳይ ስንመጣ፣ የእግር ኳስ ዳኝነት ቅፅበታዊ ውሳኔ የሚሻ እንደመሆኑ ፍፁም ከስህተት ይፀዳል ማለት አይቻልም፡፡ ስህተቶችን መቀነስ ግን የግድ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ክለቦቻችን በዳኝነት ስህተት ብቻ ብለው ምክንያት ከሚደረድሩ ወደ ራሳቸው መመልከትም ይኖርባቸዋል፡፡ በሊግ ደረጃ 56 ብሔራዊ ሊግ፣ 32 ከፍተኛ  (ሱፐር ሊግ) እና 16 የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች አሉ፡፡ ሁሉንም በተቻለ መጠን ትክክለኛ የዳኝነት ሥርዓት እንዲያገኙ እየተሞከረ ነው፡፡ በቂ ነው ብለን እንደማንወስድ ግን ሊታመን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ጨዋታ የሚደረጉባቸው ሜዳዎች ጉዳይ እንዴት ይታያል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- አበው ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ እንዲሉ በተቻለ መጠን የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ በመመልከት በጨዋታ ሜዳዎች ምክንያት ጨዋታዎችን ያቋረጥንባቸው ጊዜያቶች አልገጠሙንም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ችግሮች ሳይገጥሙን እንዳልሆነም ሊወሰድ ይገባል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከሁሉም በፊት ማስተማርን ነው ቅድሚያ አድርጎ የሚወስደው፡፡ ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችን መገንባት የጀመርነው ገና አሁን ነው፡፡ ስለዚህ ከችግሮቻችን መውጣት የምንችለው ደረጃ በደረጃ ሊሆን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደሚሉት የእግር ኳስ የዳኝነት ጉዳይ በጥሩ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ በብዙዎች ዘንድ አሁንም የጥራትና የብቃት ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ነው የሚነገረው፡፡ ይህን ይቀበሉታል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ምንም ሆነ ምን የጥራት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ የምቀበለው ነው፡፡ ስፖርቱ በየጊዜው አይደለም በየሰከንዱ እየተለወጠ ነው፡፡ የግድ ይህንን ዕድገት ጠብቆ መሄድ የሚችል ተክለ ሰውነት ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ረገድ ወደ እኛ ስንመጣ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት የእግር ኳስ ዳኞቻችንንም ሆነ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችን ደረጃ እያወጣንላቸው ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን የሚቀበሉትም የማይቀበሉትም አሉ፡፡ የሚገርመው የደረጃ ምድባውን በመቃወም እስከ ክስ የደረሱ ገጥመውናል፡፡ ተቀባይነት ግን አላገኙም፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በእግር ኳስ ዳኝነት አራት ደረጃ እንዲኖር ጭምር ሆኖ አደረጃጀቱ እንዲቀየር አድርገናል፡፡ የሴቶችም በተመሳሳይ ተደርጓል፡፡ ምድባ የሚደረገውም እንደ ጨዋታው ክብደትና ቅለት ደረጃውን መሠረት እያደረግን ነው፡፡ አሠራሩም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ተግባራዊ መሆን የጀመረው፡፡

ሪፖርተር፡- የደረጃ  ምደባው  በአቅምና በዕውቀት እስከሆነ ድረስ የተቃውሞው መንስዔ ምን ነበር?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ቀደም ሲል እንደነበረው ሁሉም ደረጃ ሳይወጣ መዳቢው አካል የፈለገውን እንዲመድብ ዕድሉ ሊሰጠው ይገባል የሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ የደረጃውን ዕውን መሆን የተቃወሙት በጣት የሚቆጠሩና የካፍና ፊፋን መመዘዘኛን ማሟላት አንችልም ብለው ሥጋት ያለባቸው ብቻ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የካፍና የፊፋ መሥፈርቶች በዋናነት እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ ልዑልሰገድ፡- መሠረታዊ ተብለው የአካል ብቃትና ጤንነት ናቸው፡፡ በእነዚህ ነገሮች ካፍም ሆነ ፊፋ በፍፁም የዳኝነት ሥርዓቱን ለድርድር አያቀርብም፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊው የዳኞች ኮሚቴ በውድድር ዓመቱ በእግር ኳስ ዳኞችና በጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ላይ የዕገዳ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ሦስት የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ላይ የሁለት ዓመት ዕገዳ ጥሏል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ልዑልሰገድ፡- እንደሚታወቀው በቅርቡ የውድድሩ ዓመቱ ግማሽ ዓመት የጨዋታ የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ግምገማ አድርገናል፡፡ በግምገማው መሠረት በተወሰኑ የእግር ኳስ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ላይ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ኮሚቴው አንድ የእግር ኳስ ዳኛ ላይ የስድስት ወር ዕገዳ አስተላልፏል፡፡ ሌሎችን በማስጠንቀቂያ ያለፋቸው አሉ፡፡ በሦስቱ ኮሚሽነሮች ላይ የተላለፈው ውሳኔ በጨዋታው ላይ በተፈጸመው ስህተት ሳይሆን የብቃት ማረጋገጫ ደረጃው ሲወጣ ለምን ይወጣል? በሚል ተቃውሞና ክስ ባቀረቡ አባላት ላይ የተላለፈ የዕገዳ ውሳኔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሠራሩ ትክክል ካልመሰላቸው መቃወማቸው ስህተት ነው?

አቶ ልዑልሰገድ፡- የተሳሳተ አሠራር ከሆነ ያንን መቃወም ትክክልም ተገቢም ነው፡፡ የሦስቱ ሰዎች ተቃውሞና ክስ ግን ሰዎች በችሎታና በብቃታቸው ለምን ይለያሉ? ከዚህም በላይ በሙያው ረዥም ዓመታትን ያስቆጠሩ ሙያተኞች የአገልግሎት ጊዜያቸውስ ለምን ግምት ውስጥ አይገባም? የሙያ ደረጃ ማውጣት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ኮሚቴው ሆን ብሎ የሚፈልገውንና የማይፈልገውን ሰው ለመጥቀምና ለመጉዳት እንዲያመቸው ነው የሚል ውኃ የማያቋርጥ ክስና ትችት በማቅረባቸው ምክንያት ነው፡፡ በአጠቃላይ የዓለም እግር ኳስ በማይታመን ፍጥነት እየተለወጠ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ባለው ፍጥነት መራመድ ባንችልም ሕግና ሥርዓቱን ጠብቀን በተቻለ ፍጥነት የሠለጠነውን አካሄድ መከተል ይኖርብናል፡፡ ይኼ የእግር ኳስ ዳኞችንና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ክለቦቻችንና የክለብ መሪዎቻችንን ጭምር እግር ኳሳዊ የሆነውን መንገድ መከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን የምንፈልገው ዕድገት ሊመጣ አይችልም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...