አንዳንድ ጊዜ ያሳለፍናቸው ጊዜያት ትዝ ይሉናል፡፡ ሰሞኑን እጅግ በጣም ከምናፍቃቸው የልጅነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አፍላ ጉርምስናዬ ያሉ ወቅቶች ፊቴ ድቅን ይሉብኛል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ሆነን የዋኘንበት የቀበና ወንዝ፣ አጋምና ቀጋ የለቀምንበት የዳንሴ ተራራ፣ አፈር እስክንመስል ኳስ የተራገጥንበት ጃንሜዳ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ ከእኩዮቼ ጋር የወጣንባቸውና የወረድንባቸው ጊዜያት ትዝታ አላስቀምጥ ብሎኛል፡፡ በቀደም ምሽት ላይ በቃና ቴሌቪዥን ቻናል በአማርኛ የተተረጎሙ ፊልሞችን ስመለከት የጥንቶቹ ሲኒማ አምፔር፣ ሲኒማ ዓደዋ፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ ራስ፣ ወዘተ በሐሳብ ወደ ኋላ መለሱኝ፡፡ እነ ማዘር ኢንዲያ፣ ወክትና የመሳሰሉት የህንድ ፊልሞች ሳይቀሩ ትዝ አሉኝ፡፡ እንደ ልጅነት ምን የሚናፍቅ ነገር አለ?
የትዝታ ነገር ሲነሳ ከንጋት ኮከብ ትምህርት ቤት እስከ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የነበሩት ትዝታዎች፣ አብዮቱ ፈንድቶ ዕድገት በኅብረት የተዘመተበትና እነዚያ የዘመቻ ኅብረ ዜማዎች፣ የኢሕአፓ የጥናት ክበብ ውይይቶች፣ ወረቀት ብተና፣ ውጥረቱ፣ በየቦታው ይሰማ የነበረው ተኩስ፣ ነፃ ዕርምጃ፣ ቀይ ሽብር፣ ዕልቂት፣ እስር፣ መከራና ሰቆቃ ሳይቀሩ ታወሱኝ፡፡ በቀይ ሽብር የተገደሉ ወጣቶች አስከሬን ላይ አብዮት ጠባቂና ካድሬ ሲፎክሩ፣ እናትና አባት ማልቀስ ተከልክለው እንባቸው እንደ ገደል ጅረት በጉንጫቸው ላይ እየወረደ በሐዘን የተጠበሱበት፣ ለለውጥ የተነሳው ወጣት በመጣበት መከራ ምክንያት ሞቶ፣ እስር ቤት ተወርውሮና ሞራሉ ደቆ እንዳይሆኑ የሆነበት ዘመን ትዝ አለኝ፡፡ ለካ ሰቆቃም ትዝ ይላል? እንዴት አይል?
ከዚያ ሁሉ እሳት ውስጥ ተርፈን ለእስር ተዳርገን በአሰቃዮቻችን እጅ ወፈፌ ላላ ተገልብጠን ለመናገር የሚያዳግቱ ሥቃይ የተቀበልን፣ ፍርድ ቤት ሳንቀርብ በቃል ትዕዛዝ ተፈርዶብን ከርቸሌ ወርደን ዓመታትን ያስቆጠርን፣ ከአገር ሸሽተን ወጥተን በሰው አገር በስደት የተንከራተትን፣ መሸሻ አጥተን በዘመኑ አገዛዝ ተረግጠን የተገዛን፣ የመጣው ይምጣ በማለት ሥርዓቱን በድፍረት የተዋጋን፣ ‹‹እናቴን ያገባ አባቴ ነው›› ብለን ለሥርዓቱ ያደርን፣ ወዘተ በትዝታዬ መስታወት እያፈጠጡብኝ እንቅልፍ አጥቼ ከረምኩ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ወደ ኋላ የቀሩ ነገሮች እኔንም ወደኋላ እየመለሱኝ ብዙ ትውስታዎችን ድቅን ያደርጉብኛል፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ግን ልርሳህ ብለው አልረሳህ ያለኝ አንድ ነገር አለ፡፡
ለሰባት ዓመታት በእስር ከቆየሁበት ከርቸሌ ወጥቼ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ለመከታተል ስድስት ኪሎ ዋናው ግቢ እሄዳለሁ፡፡ ከሬጂስትራር ቢሮ ጉዳዬን ጨራርሼ ስወጣ ከአንድ ዘመዴ ጋር እገናኛለሁ፡፡ ይኼ ዘመዴ ‹ጎመን በጤና› ብሎ ትምህርቱ ላይ ብቻ በማተኮሩ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ወጥቶ እዚያው በመምህርነት ማገልገል ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ወትሮም ብዙ ቅርበት ባይኖረንም የሥጋ ዝምድና ስላለን ብቻ ሰላምታ ተለዋውጠን ሻይ እየጠጣን ለማውራት ወደ አንዱ ካፍቴሪያ ይዞኝ ሄደ፡፡ ይህ ዘመዴ የዘመኑ ሰው ሆኖ በካድሬ ቋንቋ ሲያነጋግረኝ ነደደኝ፡፡ እኔን ሰባት ዓመት ሙሉ አስሮ ካሰቃየ፣ ብዙኃኑን ወጣት ከፈጀና ለስደት ከዳረገ ሥርዓት ጋር ተዛምዶ እንጀራውን እንደሚያበስል ስረዳ ጠላሁት፡፡ ብዙ ዝርዝር ነገር ውስጥ ገብቶ መነታረክ በትምህርቴ ላይ ችግር እንደሚፈጥር በመገንዘብ ከአንገት በላይ አዋርቼው በጊዜ ተገላገልኩት፡፡
ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ብዙም ሳልቀርበውና ሳልርቀው እንደ ተከፋሁበት ጊዜውን ገፋሁት፡፡ አንዳንዴ እንዳላየሁ በማለፍ፣ አንዳንዴ ደግሞ ጥርሴን ብልጭ እያደረኩ የሆዴን በሆዴ ይዤ እንደማልወጣው የለም ትምህርቱ አልቆ ግቢውን ተሰናበትኩ፡፡ ነገር ግን በእነዚያ የቆይታ ዓመታት ግቢውን ከሚያምሱ መሪ ካድሬዎች መካከል አንዱ እሱ ነበር፡፡ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ የደርግ ዋና አፈ ቀላጤና አስደንባሪ ሆኖ የዘለቀው ይኼ ዘመዴ ብቻ አይደለም፡፡ በአሁኑ ዘመን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ቀንደኛ የደርግ አጋፋሪዎች ነበሩ፡፡ እሱ ግን ዘመዴ ስለሆነ ያናድደኝ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲውን የአካዳሚ ነፃነት አስገፍፈው የፖለቲካ ተቀጥላ ያደረጉትን ዘመዴንና ግብረ አበሮቹን ሳስብ ዛሬም ድረስ እቃጠላለሁ፡፡ ያ የሰቆቃ ዘመን አልፎ አዲስ ሥርዓት ሲመጣ ደግሞ እንደኔ ይመረሩ የነበሩ ሌሎች ጓደኞቼ ያንኑ ድርጊት ሲደግሙት፣ በአገሬ ምሁራን ላይ ያለኝ እምነት የበለጠ ጠፋ፡፡ ከአድርባይነትና ከአስመሳይነት በላይ ብዙዎቹ ውስጣቸው በክፋት የተሞላ ነበር፡፡
ያም ሆኖ ግን ከበርካታ ዓመታት በኋላ ብዙዎቹ ጥጋቸውን ቢይዙም፣ ዩኒቨርሲቲው በአምባገነኖች የተሞላ እንደ ነበር ፈጽሞ አልዘነጋውም፡፡ ተማሪዎችን በውጤት ከመበደል ጀምሮ ሥነ ምግባር የጎደላቸው መምህራን ነበሩን፡፡ ከግል ሥጋዊ ፍላጎት ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ውግና ድረስ የነበረው በሽታ አሁን ድረስ መዝለቁን ሳስበው ያናድደኛል፡፡ በቅርቡ አንድ በጣም የምወደው የልጅነት ጓደኛዬ ከአሜሪካ መጥቷል፡፡ የጥንቱን ትውስታዎች እያነሳሁለት ስናወራ፣ ‹‹ያ ዩኒቨርሲቲ የነበረው ዘመድህ እኮ የሰብዓዊ መብት መሪ አክቲቪስት ሆኖልሃል፡፡ እነዚያ የደርግ አጋፋሪ ጓደኞቹና እሱ ያሉበት ቦታ ብትገኝ የዘመኑ ለውጥ ይደንቅሃል፤›› አለኝ፡፡
ሰው በመለወጡና ከጊዜ ጋር በመራመዱ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን በእነሱ ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው እየተባረሩ አዕምሮአቸው ተነክቶ እንዳይሆኑ ሆነው የቀሩትን ይቅርታ ሳይጠይቁ ወይም ንሰሐ ሳይገቡ ተለወጥን ማለት አይገባኝም፡፡ ስማቸውን ማንሳት ደግ አይደለም እንጂ አሜሪካና ካናዳ የመሸጉት እነ ዶ/ር ምንትሴዎች ስንት ያላወራረዱት ሒሳብ እያለ ስለሰብዓዊ መብት ሲከራከሩ ይደብራል፡፡ ከእነሱ ጀምሮ እስካሁን የዘለቀውን የምሁር ካድሬነት ሳስብ ኃጢያታቸውን አለመናዘዛቸው ያበግነኛል፡፡ እነዚህን ወደኋላ ተጉዤ ሳስታውሳቸው ያመኛል፡፡ ብዙዎችም እንደኔ እንደሚያማቸው አውቃለሁ፡፡ እነሱን ባሰብኩ ቁጥር በንፅህና ያለፈው የልጅነት ጊዜ በጣም ይናፍቀኛል፡፡ ያለንበት ዘመን ሲያስከፋም የድሮውን መናፈቅ የግድ ማለቱ ያለና የነበረ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘመንም እነዚያን መሰል እስስቶች ሞልተዋልና፡፡
(ኤልያስ ዘ. ከአዲሱ ገበያ)