Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርጥልቅ ተሃድሶው ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለውን የሰነፎች ምሽግ ያፈርሰው ይሆን?

ጥልቅ ተሃድሶው ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለውን የሰነፎች ምሽግ ያፈርሰው ይሆን?

ቀን:

በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች ለተነሱት ተቃውሞዎች የፀጥታ ችግር ተከስቶ ነበር፡፡ ይኼንንም የፀጥታ ችግር ለመፍታትና መረጋጋት ለማምጣት አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዳለች ይታወቃል፡፡ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ውስጥም ሳለች ሕዝቡ ያነሳቸውን ተገቢ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ መንግሥት ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ብሎ በሰየመው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ የካቢኔ ለውጥ በማድረግ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ መጀመሩን አሳይቷል፡፡ በዚህ ለውጥ ስም የነበራቸው ሚኒስትሮች ከሜዳ ውጪ ሲሆኑ፣ ለፖለቲካዉ ጨዋታ አዳዲስ የሆኑ ሚኒስትሮች ወደ ሜዳው ገብተዋል፡፡

መንግሥትም ይህ ለውጥ በላይ ባለው አመራር ብቻ ተግብሮ እንደማይቀርና ወደታች በደረጃው እየወረደ እንደሚሄድ ቃል ገብቷል፡፡ እኔም ይህን እንደ መንደርደሪያ ይዤ በጥቅሉ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በተለይም ተደጋግመው በሚነሱ ሁለት ችግሮች ላይ እንዲህ ለማለት ወደድኩኝ፡፡

ይህ ጥልቅ ተሃድሶ ማፍረስ ካለበት አደገኛ ምሽግ ውስጥ አንደኛውና ዋነኛው ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መሆን አለበት እላለው፡፡ ለአብነት ያህል እንደ መንገድ ባለሥልጣን፣ ገቢዎች፣ በየክፍለ ከተማው የሚገኙ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ይኼ ተሃድሶ ካልገባ ጥልቅ መሆኑ ቀርቶ ከአንገት በላይ ለይስሙላ ይሆናል፡፡ በነዚህ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ተገልጋዩ ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ፣ እነዚህ አገልግሎት ሰጪዎች እንደ ምክንያት እያነሱ በጋራ የሚደበቁበት አንድ ምሽግ አለ፡፡ “ሲስተም የለም” የሚባል የሰነፎች ምሽግ፡፡

ካስተዋላቹ በአንዳንድ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሆነውም ባልሆነውም አገልግሎት ላለመስጠትም ሆነ አገልግሎት ባለመስጠታቸው ተጠያቂ ላለመሆን፣ “ሲስተም የለም” ዋነኛ ምክንያትና መሸሸጊያቸው ሆኗቸዋል፡፡ ይኼንንም ምክንያት ላልተገባ ጥቅም ማጋበሻ (በዘሙኑ አነጋገር ለኪራይ ሰብሰቢነት) ትልቅ በር ሆኗል፡፡ “ሲስተም የለም” የሚለው ምክንያት ሕዝቡን አማሮታል፣ አሰልችቶታል፣ እጅ እጅ አስብሎታል፡፡

እዚህ ላይ አንድ አገልግሎት ፈላጊ በዚህ ምክንያት እጅግ ከመማረራቸዉ የተነሳ አሉ የተባለውን ላንሳ፡፡ ሰውዬው “የሲስተም የለም” ችግር ሰለባ ሆነው፣ ‹‹ኮምፒውተር ነጥቆ ወደ ዶሴ (መዝገብ) ማገላበጥ መመለስ ነው የሚያስፈልገው፤›› ብለዋል፡፡ ለእኔ አባባላቸውን የንዴት ንግግር ብቻ ነው ብዬ ማለፍ አልፈለኩም፡፡ ንግግራቸው ውስጥ ድሮ ያለ ኮምፒውተር መዝገብ እያገላበጡ ሲሠሩ የተሻለ አገልግሎት ነበር የሚል ቁም ነገር አለው፡፡ እየተናገርኩ ያለሁት ስላለፈ ነገር አይደለም፤ በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ሆነን እየሆነ ያለውን ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት እንደሚለው በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘመናት መካከል የተገነባን የመጥፎ አስተዳደር ምሽግ ማፈራረስና ምቹ ማድረግ ቀላል እንደማይሆን እረዳለው፡፡

ነገር ግን ‹‹አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል›› እንደሚባለው፣ ከላይ በሚኒስትሮች ላይ የተደረገው ለውጥ ንዝረቱ በትንሹም እንኳን ቢሆን ታች አገልግሎት ሰጪው ጋር መሰማት ነበረበት፤ አለበትም እላለው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ማስተካከልና ምቹ ማድረግ፣ የአገልግሎት ሰጪው የቤት ሥራ እንጂ የተገልጋዩ ራስ ምታት መሆን የለበትም፡፡ የኔትወርክ መቆራረጥና ብሎም መጥፋት ተገልጋዩ የሚጨነቅበት ጉዳይ መሆን አይኖርበትም፡፡ ተገልጋዩ አገልግሎት የማግኘት መብት እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት እንጂ የተገላቢጦሽ መሆን የለበትም፡፡

እየሆነ ያለው ግን አገልግሎት ፈላጊ ለማኝ፣ አገልግሎት ሰጪ ተለማኝ፤ አገልግሎት ፈላጊ ደጅ ፀኝ፣ አገልግሎት ሰጪ ደጅ አስፀኝ፤ አገልግሎት ሰጪ ደስ ሲለው የሚሠራ ሲፈልግ ምክንያት ፈልጎ የማይሠራ፤ አገልግሎት ሰጪ ፈላጭ ቆራጭ አድራጊ ፈጣሪ የሆነበት ሀቅ ነው መሬት ያለው፡፡ የጥልቅ ተሃድሶው እንቅስቃሴ በፍጥነት ወደዚህ ምሽግ መገስገስ አለበት እላለው፡፡ ምክንያቱም እዚያ ብዙ ነፃ መውጣት ያለበት የሕዝብ ምሬት፣ ለቅሶ፣ ብስጭት ስላለ፡፡

በባህላችን አንድ ጉርሻ ያጣላል ይባላልና አንድ ሌላ በእነዚህ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገልጋዩን ከሚያማርሩ አሠራሮችና ሁኔታዎች ውስጥ ‹‹ፋይሉ ጠፋ›› የሚለውን ልጨምር፡፡ ይህ አባባልና መልስ በጣም ያስገርመኛል፤ እንዲህ ብለው መልስ የሚሰጡ ተቋማትም ያሳፍሩኛል፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ፋይል ግዑዝ ነገር መሰለኝ እግር የለው፣ ክንፍ የለው፣ እንዴት ነው ተነስቶ የሚጠፋው፡፡ በተቋሙ ውስጥ ባለ መዝረክረክና ፋይል የማስተዳደር ችግር ፋይል እየጠፋ፣ ፋይሉ ጠፋ ብሎ ደረት ገልብጦ፣ አፍ ሞልቶ መናገር ያሳፍራል፡፡ በዚህም ምክንያት ተገልጋይ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት በሰዓቱ ካለማግኘቱ በተጨማሪ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ በሰዓቱ መቀለድ ምን የሚሉት ዓይነት አገልግሎት ነው፡፡ እንዴት ‹‹ፋይሉ ጠፋ›› የሚባል ነገር ለአገልግሎት ሰጪ አገልግሎት ላለመስጠት ምክንያት ይሆናል፡፡

እንዲህ አይጠየቅም፤ እንዴ ፋይሉ ማን ጋ ነው የጠፋው? ፋይሉን በአግባቡ የመያዝ  ሥራ  የማን ነው? ፋይሉስ ሲጠፋ ተጠያቂ መሆን ያለበት ማን ነው? ፋይሉ በመጥፋቱ መደንገጥ ያለበት ማን ይሆን? ይኼማ የአገልግሎት ሰጪው ኃላፊነት ነው  እንደምትሉ አልጠራጠርም፡፡ በመርህ ደረጃ እውነት ብላችኋል፡፡ እውነታው ግን በዚህ ሁሉ ፍዳውን የሚያየው ተገልጋዩ ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንዴ ፋይሉ ሳይጠፋ በአንዳንድ ሰውን በማማረር ኪሳቸውንና ሆዳቸውን በሚሞሉ ግለሰቦች ተደብቀው፣ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትና ለመደራደሪያ እንደ መሣሪያ ጭምር ይጠቀሙበታል፡፡ ይኼን ሁሉ የምለው በጥልቅ መታደሱ ደረጃ በደረጃ ወደዚህ የሥርዓት አልበኞች መፈልፈያ ወደሆነውና እስካሁንም ወዳልተነካው ምሽግ ውስጥ መግባት አለበት ለማለት ነው፡፡ አለዚያ ግን ትርጉም ያለው ተሃድሶ አይመጣም፡፡ ጥሩ መመርያ ማውጣት ብቻ ጥሩ የአገልግሎት አሰጣጥን አያመጣም፡፡ ጥሩ አገልጋይና ጥሩ ፈጻሚም ያስፈልጋል፡፡

(እስጢፋኖስ ስሜ፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

አንበሳ አውቶብስ ነፃ ቲኬት ቢሰጠን ምን ይገጎዳል?

በጡረታ ላይ ባሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት ድርጅት (በአሁኑ ስሙ አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት) ሠራተኞች መረዳጃ እድር መንግሥት በፈቀደው የመደራጀት መብት መሠረት በኅዳር ወር 1995 ዓ.ም. ተመሥርቶ እነሆ ዛሬ 14ኛ ዓመት ላይ ደርሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመረዳጃ እድሩ ካፒታል 175,000 ብር በመድረሱ፣ እንደ ማንኛውም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጡረተኞች መዝናኛ ክበብ ለማቋቋምና አቅመ ደካማ የሆኑትን አባላት ለመርዳት አቅዷል፡፡ ከዚያም አልፎ አባላቱ ለቤተሰቦቻቸው የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ራሳቸውን እንዲረዱ ለማስቻል አቅደን፣ አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት እገዛ እንዲደረግልን ጥያቄ አቅርበን አንድ ዓመት ከሰባት ወር ካመላለሱን በኋላ ምንም ዓይነት ድጋፍና እገዛ እንደማያደርጉልን ገልጸውልናል፡፡ ስለሆነም ክቡር ከንቲባው በአርቆ አስተዋይነትዎ ከዚህ በታች የምናቀርበውን ጥያቄዎች ግምት ውስጥ በማስገባት፣ መልካም ፈቃድዎ ሆኖ አዎንታዊ መልስዎን እንደማይነፍጉን በመተማመን ነው፡፡

  1. መዝናኛ ክበቡን በሚመለከት

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲዎች አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ይጠቀምባቸው የነበሩት ቢሮዎች፣ ሙት ሰነዶች /Dead File/ ማከማቻ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ቢሮዎች መካከል አንደኛውን ቤት በመረዳጃ እድሩ ስም እንዲዞርልንና መረዳጃ እድሩ ኪራይ እየከፈለ ክበቡን እንድናቋቁምበት ጥያቄ ብናቀርብ እንደማይቻል ተገልጾልናል፡፡ ስለሆነም ክቡር ከንቲባው በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የቤት ችግር እየታየ ባለበት ወቅት፣ ከአሥር የማያንሱ ቢሮዎች የሙት ሰነድ ማከማቻ ሆነው መቀመጣቸው ያሳዝናል፡፡ ከዚህም በላይ ድርጅቱ አላግባብ የቤት ኪራይ መክፈል አይገባውም ነበር፡፡

ለዚህ መፍትሔ የሚሆነው በሦስቱ ዲፓዎች በአንዱ ትልቅ መጋዘን አሠርቶ ሙት ሰነዶቹን በአግባቡ ማስቀመጥ ይቻል ነበር፡፡ የቀድሞ የሕዝብ ማመላለሻ ኮርፖሬሽን ሰነድን አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በኃላፊነት ስለተረከበና ከእኛ ይልቅ ሙት ሰነዱ ስለበለጠበት ጥያቄያችን ለመመለስ አልቻለም፡፡ ይህ ቀና አመለካከት ባለመኖሩና ድርጅቱ በመልካም አስተደደር ችግር የተተበተበ በመሆኑ እንደሆነ እናውቃለን፡፡

  1. ነፃ የአውቶብስ መጓጓዣ ትኬትን በሚመለከት

በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የምንገኝ የቀድሞ የኢትዮጵያ ተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞች ከአባት አርበኞችና ከኮሪያ ዘማቾች ያነሰ ዕድሜ የለንም፡፡ ለእነሱ ነፃ የአውቶብስ መጓጓዣ ትኬት ሲሰጥና እኛ አገልግሎታችንን በሚገባ አበርክተን በጡረታ ስንገለገል ነፃ ትኬት ተከልክለናል፡፡ ይኼንን ጥያቄ ለድርጅቱ አቅርበን ነፃ ትኬት እንደሚሰጠን ኃላፊዎቹ ቃል ገብተውልን፣ ይህን አገልግሎት የሚሰጣቸውን የእድሩ አባላት ስም ዝርዝር እንዲተላለፍልን ብለው ጠይቀውን ነበር፡፡ የድርጅቱ ኃላፊዎች በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በስብሰባችን ላይ በመገኘት ለአባላቱ ተስፋ ሰጥተው፣ አባላቱን በእልልታ ካስጨበጨቡ ከአንድ ዓመት ከሰባት ወር በኋላ የተሰጠን መልስ አሳዝኖናል፡፡ ያም ሆነ ይህ አይደለም አባት አርበኞችና የኮሪያ ዘማቾች ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው በውርስ ነፃ ትኬት እንደሚሳጣቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ መምህራን በሙሉ ነፃ የአውቶብስ መጓጓዣ ተሰጥቷቸው የትራንስፖርት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ ታዲያ እኛ አዋጅ ለማስፈም ቅጥራችን በቀድሞ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት ድርጅት የሠራን አቅመ ደካማ አረጋዊያን ነፃ ትኬት ቢሰጠን፣ ከመኖሪያ ቤታችን ወደ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ ፈጣሪችንን ለመለመን የምንሄድበት እንጂ ቀኑን ሙሉ በአውቶብስ የምንመላለስበት አይደለም፡፡ ያውም ከእንግዲህ ስንት ዓመት ስንኖር ነው? ድርጅቱንስ ምን የሚጎዳው ነገር አለ? ይህንን ድርጅት እዚህ አድርሰው ለአዲሱ ትውልድ ያስረከቡ የአሁኖቹ አቅመ ደካሞች፣ ባለውለታ ስለሆኑ መረሳትና መጣል የለባቸውም፡፡

ስለዚህ ክቡር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እኛ አቅመ ደካማ አረጋዊያን ያቀረብነው ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አስፈላውን ሁሉ እንደሚያደርጉልን በእግዚአብሔር ስም ምስጋና ከማቅረብ ውጪ የምንለው ነገር የለም፡፡

ከዚህ ቀደም ሲል ይህን አቤቱታ በተወካዮቻችን በኩል ልከን ጸሐፊዎች ደብዳቤውን አንቀበልም ማለታቸውን በዚሁ ማሳወቅ እንወዳለን፡፡

(የቀድሞ የኢትዮጵያ ተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞች መረዳጃ እድር አባላት)

* * *

ለማን አቤት እንበል?

 አዲስ አበባ አስተዳደር ነባሩን የቤት ካርታ በመቀየር ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቤቴል አካባቢ ደረጃ ስድስትና ሰባት ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ያለው የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በመቀየር ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ካርታ ለመቀየር ከአራት እስከ ስድስት ወር ይፈጃል፡፡ ዕድለኛ ካልሆንክ ደግሞ ካርታው ጠፋ ትባላለህ፣ እንደገና ሌላ መመላለስ ሌላ መንከራተት ይገጥማል፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ መንግሥት (ኢሕአዴግ) ታድሻለሁ፣ መልካም አስተዳደር አሰፍናለሁ በሚልበት ጊዜ ብሶበታል፡፡ እንኳን መልካም አስተዳደር ልናይ፣ ስሙም የለም፡፡ ምናልባት ወረዳና ክፍለ ከተማ ያሉ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ተሃድሶው የሚመለከታቸው አይመስለኝም፡፡

አለመታደል ነው መሰለኝ ወይ መንግሥት ታድሶ መልካም አስተዳደር አያመጣ፣ ወይ ጥሩ ተቃዋሚ ኖሮን ለችግራችን መፍትሔ አያወራ፣ በአጠቃላይ ብዥ ያለ ነገር ነው፡፡

(አሰፋ ብርሃኔ፣ ከአዲስ አበባ)   

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...