Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየኢትዮጵያ የድንበር ግጭት አፈታት ሕግ ተርሚነስን ፍለጋ

የኢትዮጵያ የድንበር ግጭት አፈታት ሕግ ተርሚነስን ፍለጋ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ኢትዮጵያ እልባት ያላገኙ በርካታ የድንበር ጉዳዮች አሉባት፡፡ ከአዋሳኝ አገሮች ጋር ብቻ ሳይሆን በውስጥም በክልሎችና ከዚያ በታች በሚገኙ አስተዳደራዊ እርከኖች ላይ የድንበር ጉዳይ አሁንም ቢሆን እየቆየ የሚነሳ ወይም ደግሞ የሚያገረሽ ግጭትን እያስከተለ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ከሁሉም አዋሳኞቿ ጋር ያላለቀ የቤት ሥራ አለባት፡፡ በመሆኑም በውጭም በውስጥም ግጭት ያስነሱ ወይም ሊያስነሱ የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ከውጭ ከኤርትራ ጋር በድንበር ተጋጭተናል፡፡ ከሱዳን በተለይም በአማራና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ ጉዳዩ አጀንዳ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ከኬንያ በኩል የሚነሱ ጥቃቶችም እንዳልቆሙ ይታወቃል፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋርም እንዲሁ የጎሳ ግጭቶች አሉ፡፡ የሶማሌም ቢሆን አለመጠናከሯ በጀ እንጂ በድንበር አካባቢ ግጭት አይነሳም ማለት በደርግ ጊዜ የነበረውን ጦርነት መርሳት ነው፡፡ ተመሳሳይ ብሔሮች በኢትዮጵያና በአዋሳኝ አገሮች መገኘታቸው ደግሞ ነገሩን የበለጠ ያወሳስበዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኢትዮጵያ ውስጥ ክልል ከክልል ጋር ያላለቁ የድንበር ወይም ወሰን ጉዳዮች አሉ፡፡ ግጭት ያስነሱና አሁንም በግጭት ውስጥ ያሉ አሉ፡፡ ክልሎቹ እንደ አንድ የመስተዳድር መዋቅርና እንደ መንግሥት ግጭት ውስጥ ባይሆኑም እንኳን የብሔር ግጭቶች ግን አሉ፡፡ በወልቃይት የሚኖሩ አማሮች የክልል ለውጥ በማንሳታቸው ግጭት ተከስቷል፡፡ በአማራና በአፋር፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ (ከሲዳማ፣ እንዲሁም ከጌዴዮ ብሔሮች ጋር) በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ውዝግቦች ንብረት ወድሟል፤ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ሰው ሕይወት እንደጠፋ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በአንዳንድ ሚዲያዎች እንደተዘገበው ደግሞ በግጭቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ሶማሌ ልዩ ኃይል ፖሊስም ተሳትፎ ተጨምሮበታል ይላሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛም የድንበር ግጭት ሕጋዊ መፍትሔዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ይሁን እንጂ መፍትሔዎቹ ከግጭቶቹ መንስዔ፣ በግጭቱ ውስጥ ከሚሳተፉት አካላት ማንነት፣ ግጭቶቹን የመፍታት ድርሻ ያለባቸው አካላት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ እነሱም በስሱ ይዳሰሳሉ፡፡ የሕጎቹን ክፍተትና የተቋማቱን ጎደሎነት ለመጠየቅና መፍትሔዎችን ለመጠቋቆም የሚያስችል እገዛ ለማገኘት ሲባል የአንዳንድ አገሮችን ተሞከሮ መቃረማችን አይቀርም፡፡

ስለ ድንበር ግጭት ምንነትና መንስዔዎች

የድንበር ግጭት ስንል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚጋጩት አካላት ብሔሮች ናቸው፡፡ ብሔርን የደረቡ የድንበር ግጭቶችን ወይም ቢያንስ ማንነትን (የጎሳ፣ የነገድ…) መሠረት ያደረጉትን ማለታችን ነው፡፡ ጥቅል የሆነው የግጭቱ ይዘት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ ወይም የግዛት ሊሆን ይችላል፡፡ የግጭቱ መነሻ ምንም ይሁን ምን ሕይወት ይቀጠፋል፤ የሰብዓዊ መብት በተለያየ መልኩ ይገሰሳል፤ ንብረት ይወድማል፡፡ ብሔርን ወይም ማንነትን መሠረት ወዳደረገ የእርስ በርስ ጦርነትም ሊያድግ ይችላል፡፡

በአገር ውስጥ የሚከሰቱት ግጭቶች በአብዛኛው ከሀብት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ሀብቶቹ፣ የግጦሽ ሳር ወይም ውኃ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን አሁን ደግሞ ከሀብት ወደ ግዛት ይገባኛልነት እየተቀየሩ መምጣታቸውን በቅርብ ይፋ የተደረጉ ሌሎች ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት በኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል የተከሰተውን ግጭት በአስረጅነት በማቅረብ ዶ/ር አስናቀ ከፋለ ለዘመናት አብረው በአንድነት  የኖሩት ድንበር ሲካለል መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሞዎች መካከልም ቢሆን  በተለይ ጉጂ፣ ጋሪና ገብራ ጎሳዎች አብረው ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ቢሆንም፣ ድንበር ወይም መለያ ሲሠራ አልፎ አልፎ ጥል መፈጠሩ ገሃድ ሆኗል፡፡ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ቦታዎችን ማካለል ሀብትን እንደ ቀድሞው ለመጋራት በስምምነት ለመጨረስ ወይም ተስማምተው ለመኖር፤ ብሔርን መሠረት ያደረገ አስተዳደር ሲመሠረት ትብብሩም፣ ስምምነቱም ከሚመሳሰሉት ብሔሮች ወይም ቡድኖች ጋር ብቻ ስለሚሆንና ድንበርን መተላለፍ ስለሚመጣ ግጭት ያመጣል፡፡

ጉዳዩ የበለጠ የሚባባሰው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ብሔሮች ሰፋ ባለ ሁኔታ የሚገናኙበት አካባቢን (ethnic frontier) በድንበር ለመለየት በሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ለዘመናት ተቀላቅለው በመኖራቸው የፈጠሩትን የእርስ በርስ ግንኙነት የፖለቲካ ወሰን ሲሰመርባቸው የቀደመው የኑሮ ይትባሃላቸው በቀላሉ ስለማይቆም ግጭትን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ አስተዳደራዊ ወሰን ሲካለል ሕዝቦች ወደ የትኛው የአስተዳደር ቀጣና መካለል እንደሚፈልጉ ወይም እንዳለባቸው ማንነታቸውን ከተለያዩ ጥቅም ጋር አቆራኝተው ከወሰኑ (utilitarian self-identification) በኋላ በድጋሚ ማንነትን መቀየር (identity switching) ሊመጣ ስለሚችል፣ ማንነታቸውን መቀየር ሲፈልጉ ግጭት ይፈጠራል፡፡ ማንነትን ለመቀየር የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች በእነዚህ አካባቢዎች ይበዛሉ፡፡ ከተለያዩ ብሔሮች መወለድ ዋናው ነው፡፡ ለመቀየር የወዲያው ምክንያት የሚሆኑት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መለያየት፣ በመሠረተ ልማት መለያየት፣ በተሻለ የሥራ ዕድል መኖር ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ እነዚህን ሁኔታዎች ከማንነት ጋር መያያዝ ይከተላል፡፡ በመሆኑም ድንበሩ ረግቶ ላይቆይ ይችላል፡፡

ግጭቶቹ የድንበር ሆነው በክልሎች ውስጥም ሊነሱ ይችላሉ፡፡ መነሻቸው የማንነት ይታወቅልኝ፣ ራሴን የማስተዳድርበት ወረዳ፣ ዞን ይከበርልኝ ሊሆን ይችላል፡፡ አካባቢውንም የራስ አድርጎ የመቁጠር ነገርና ሌሎቹን ማግለልና መጤ ማድረግም  አለ፡፡

ዝርዝር የድንበር ግጭቶቹ እንደ ማኅበረሰቡ የአኗኗር ሁኔታም ሊለያይ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር አርብቶ አደር የሆኑ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ግጭቶቹ ይበዛሉ፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወራቸው አንዱ መነሻ ቢሆንም፣ ለወዲያው የሚያጋጫቸው ግን የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ በአኗኗር ዘይቤ በሁለቱም ወይም በአንድ በኩል ያሉት ብቻ አርብቶ አደር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አርብቶ አደር ሲባል በአንድ አካባቢ ረግተው የማይኖሩትን ለማለት ነው፡፡ ለግጦሽ የሚሆን ምግብና ውኃ የመፈለግና ውድድርም ውስጥ የመግባት ሁኔታ የብሔር ልዩነቱን እያሰፋው እንደሚመጣ ግልጽ ነው፡፡ ፍለጋውም፣ ጥቃቱም፣ መከላከሉም እንዲሁ ብሔር መሠረት አድርጎ ስለሚከናወን ማለት ነው፡፡

አርሶ አደር የሆነው ሕዝብ ባለበት አካባቢ በርካታ ግጭት ሲከሰት አይስተዋልም፡፡ ለዘመናት መሬቱን በገበሬዎች የተያዘ ስለሆነ መገፋፋትና መንቀሳቀስ  ስለማይኖር ሊሆን ይችላል፡፡ አለበለዚያም ግጭቱ በግለሰብ ደረጃ የሚወሰን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ልካለል በሚል ምክንያት ሲከሰት ይስተዋላል፡፡ መነሻው የመልካም አስተዳደር እጦትና በማንነት መጨቆን ሊሆን ይችላል፡፡ ድንበሮች በግጭት ማግስት በጥልቀት ሳይታሰብባቸውና ጥናት ሳይደረግባቸው የተካለሉበት ሁኔታ ስላለና የነዋሪው ፈቃድ በትክክል ስላልታወቀ ወይም የክልሎችን ባሕርይ ማለትም ከቀድሞው በምን እንደሚለዩ ካለማወቅ በመነጨ ስምምነት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ውሎ ሲያድር ግን ድንበር የመለወጥ ፍላጎት ይመጣል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪም ከውስጥም ከውጭም ያለው የፖለቲካ ትኩሳትም (ለአብነት ነፃ አውጭ ድርጅቶችን ማንሳት ይቻላል) ግጭት ኮትኳች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህም ይሁን በሌላ ምክንያት ውሎ ሲያድር የብሔር ማንነትን አጥብቆ መፈለግና ወደሚመሳሰላቸው ክልል ለመካለል መሻት ሲነሳ ሊያጋጭ ይችላል፡፡

ድንበርን የሚመለከቱት ሕጎች

የፌደራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሁለት ላይ እንደተገለጸው የአገሪቱ የግዛት ወሰን (ድንበር) የክልሎቹ ወሰን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ይኼም አንቀጽ በዚህ መልኩ መደንገግ እንደሌለበት፣ ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ሁሉ፣ የራሷ የሆነ ዳር ድንበርና አዋሳኞች ሊኖሯት እንደሚገባ ክርክር እንደነበር ከተለያዩ ሰነዶች መረዳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ሳይቀር የሚወሰነው በክልሎች ሕግጋተ መንግሥት ነው እንደማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ክልሎች አዋሳኞቻቸውን ብሎም ድንበራቸውን የደነገጉ ቢሆንም የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥት ግን የክልሉ ወሰን የዞኖቹና የወረዳዎቹ ነው በማለት ደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ እንኳንስ ወረዳና ዞን ይቅርና ከልሎችም ከሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋል ስለማይችሉ ይህ ዓይነቱ በክልል፣ በዞንና በወረዳ የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን በተለይም ከሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ጋር የምትዋሰንባቸውን ድንበሮች መለየት ለአፈጻጸምም አስቸጋሪ ነው፡፡ ክልሎቹ ከሉዓላዊ አገሮችና ከሌሎች ክልሎች ጋር ይዋሰናሉ፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚዋሰኑበት ጊዜ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ሲሆን፣ ከሌላ ክልል ጋር በሚዋሰኑበት ድንበር ምክንያት የሚነሱት ጉዳዮች ደግሞ የፌደራል ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው፣ ድንበርን በተመለከተ ጥቅልል አድርጎ የክልል ማድረግ ተገቢያዊ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ፌደሬሽን ግዛቷ (territory)  የክልሎቹ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የግዛት ወሰኗ ደግሞ በጥቅሉ የክልሎቹ ሳይሆን ክልሎቹ ከሌሎች ሉዓላዊ አገሮች ጋር ያላቸው ድንበር (border or boundary) ነው፡፡ ስለሆነም ክልሎቹ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚዋሰኑበትን የድንበር አከላለልና ተያያዥ ጉዳዮች በፌደራሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር እስካልሆኑ ድረስ ሁኔታዎቹን የበለጠ ውስብስብ ያደርጋቸዋል፡፡

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ኢትዮጵያና ሌሎች አገሮችን በሚመለከት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና አሠራሮች፣ የአገሮችን መብትና ግዴታን አስመልክቶ በ1933 የተደረገው የሞንቲቪዶ ስምምነት፣ አገሮች እርስ በርሳቸው ያደረጓቸው ውሎችና ሌሎች መርሖችን በመከተል እልባት መፍትሔ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

በክልልና በክልል መካከል የሚነሱ የድንበር ውዝግቦች ለመፍታት የሚረዱ የተለያዩ ሕጋግትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቀዳሚነት ሊነሳ የሚችለው የፌደራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48 ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት የድንበር አለመግባባት በሁለት ክልሎች መካከል ሲፈጠር በቀዳሚነት ክልሎቹ በስምምነት እንዲጨርሱ ነው የተደነገገው፡፡ በራሳቸው መስማመት ካልቻሉ በፌደሬሽን ምክር ቤት አማካይነት ውሳኔ ይሰጣል፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተገለጸው ምክር ቤቱ በብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች መከካከል አንድነትና መፈቃቀድ እንዲያድግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በክልሎች መካከል አለመግበባት ሲፈጠር ውሳኔ የመስጠት ሥልጣኑም የእሱ ነው፡፡ በሁለት ክልሎች መካከል ውዝግብ አለኝ የሚል ክልል ለሌላው ክልል በጽሑፍ እንዲያውቀው ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መጥሪያው የደረሰው ክልልም በአርባ አምስት ቀናት ውስጥ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ድርድሩንም ወይም ውይይቱን የፌደሬሽን ምክር ቤት ይከታተለዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ መፍተሔ ካልተገኘ አሊያም አንዱ ክልል ለውይይት ዝግጁ ካልሆነ ለምክር ቤቱ አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ምክር ቤቱም ለጊዜው ተገቢ የመሰለውን ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በተለይ ግጭቶች ካልቆሙ ለማስቆም የሚያስችል ተገቢ የሆነ ጊዜያዊ ውሳኔ/ዕርምጃ የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ግን ማስረጃዎችን መመርመርና መልስ ከሌላው መቀበል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ በድንበርም ወይም በሌላ ምክንያት ለሚነሳ አለመግባባት በጥቅሉ የተቀመጠ አሠራር ነው፡፡ 

የድንበርን አለመግባባትን በተመለከተ ተጨማሪ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ይኼውም  ከውሳኔ በፊት የሕዝቡን አሰፋፈር ማጥናትና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ግድ ነው፡፡ በሕዝቡ አሰፋፈር ብቻ መወሰን የሚቻል ከሆነ በዚያው ያልቃል፡፡ በዚህ የሚቋጭ ካልሆነ ግን ወደ ሕዝቡ ፍላጎት መሄድ ሁለተኛው ደረጃ ነው፡፡ የሕዝቡን ፍላጎት ለማረጋገጥ ደግሞ በቀበሌ ደረጃ በሚከናውን ሕዝበ ውሳኔ በምርጫ ቦርድ አማካይነት ይፈጸማል፡፡ ድምፅ ለመስጠት የሚችለው በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ሲሆን በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀለ ሰው ግን ድምፅ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በውጤቱም መሠረትም አካባቢው የማን እንደሆነ ይለያል፡፡

ከፌደሬሽን ምክር ቤት በተጨማሪ፣ የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ሥልጣንና ኃላፊነት በክሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚፈቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዲጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥራት፣ በክልሎች ጠያቂነት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት እንዲፈቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ የመቀየስና የመተግበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በመሆኑም ከፌደሬሽን ምክር ቤት በመለስ ማለትም ዳኝነት ከሚመስሉት በስተቀር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንም ይመለከተዋል፡፡

ስለ ድንበር ለውጥ ሲነሳ

የድንበር ውዝግብ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዋናነት ግን የወጥነት መርሕ ማለትም ቀድሞ ድንበር ከተደካት ጋር የሚጣጣምና የማይቃረን መሆኑ ነው፡፡ ብሔርን መሠረት አደርጎ ከነበር በለውጥም ጊዜ እንዲሁ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ሲከለል ማንነትና አሰፋፈር ከነበሩም ኋላም በለውጥ ጊዜ እንዲሁ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለክልልነት መሥፈርቶቹ ማንነት፣ ቋንቋ፣ የሕዝብ አሰፋፈርና ፈቃድ ናቸው፡፡ የድንበር ውዝግብን ለመፍታት ግን አሰፋፈርና ፍላጎት ብቻ ናቸው፡፡ አሰፋፈር የሚለው ቋንቋንና ማንነትን ያካትታል እንዳይባል ደግሞ ቀድሞ ክልል ለመመሥረት የብቻቸው ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ በመሆኑም የሕዝቡ አሰፋፈር ማለት ምን እንደሆነ ዝርዘር ነገር ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ ወጥነቱን ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ አሰፋፈር የሚለውን መለኪያ አላግባብ ሥራ ላይ በማዋል ግጭትን ሊያባብስ ስለሚችልም ጭምር፡፡ በተለይ ደግሞ ግጭቶች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩት ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀሱ ሕዝቦች መካከል በመሆኑ ይህንን መስፈርት በተገቢው መንገድ መተርጎም ያስፈልጋል፡፡ በበርካታ አገሮች እንዲህ ዓይነት ችግር ሲከሰት ተጨማሪ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ይገባል፡፡

በአንድ በኩል የፌደራል ሥርዓቱ የተዋቀረበት ወይም ክልሎች የተከለሉበት ሁኔታም መስፈርትም ውሎ ሲያድር ሊያጋጭ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ብሔሮች የራሳቸውን አስተዳደር ለመመሥረት ወይም ለማስፋት በመፈለግ ሊከሰት ይችላል፡፡ ታሪካዊ ይዞታን መጠየቅም ሊከተልና ግጭት ሊወልድ ይችላል፡፡ የፌደሬሽኑ አባላት (ክልሎች) እኩል መብት እንዳለቸው የማይጨበጥ መብት (legal fiction) ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ልዩነት ይፈጥራል፡፡ የልዩነቱ መነሻም የሕዝብ ብዛት ከፍና ዝቅ ማለት፣ የሀብት መበላለጥ፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ፊትና ኋላ መሆን፣ የክልሎች መልክአ ምድራዊ ግዛት ስፋትና ጥበት የተወሰኑት ናቸው፡፡ እነዚህን ልዩነቶች ለማጥበብ ሽሚያ ይፈጠራል፡፡ ሽሚያው ጠብም ይጭራል፡፡ በእነዚህና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሕዝቡ አሰፋፈር በሚል ጥቅል መለኪያና የሕዝብ ፍላጎት ብቻ መወሰን ግጭቱ እንዳይቀጥል ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንን ደግሞ በተለያየ ጊዜ ውሳኔ የተሰጠባቸው አካባቢዎች ላይ በድጋሚ ያገረሹትን አለመግባባቶች ማንሳቱ በቂ ነው፡፡

ገለልተኛ የድንበር ኮሚሽን መቋቋም እንደ አማራጭ

በመሆኑም እስካሁን ያሉትን አሠራሮችም ይሁን ተቋማት ዳግም የመፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡ የድንበር ጉዳይን በተመለከተ በዓለም አቀፍም ይሁን በፌደራል ሥርዓት አሠራሩም ይሁን ጽንሰ ሐሳቦቹ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ዋናው ልዩነቱ የሚመነጨው ግጭት ሲፈጠር ተፈጻሚ የሚሆኑት ሕጋገት ላይ ነው፡፡ ግጭቶቹን ለመፍታት ግን ኮሚሽን ማቋቋም የተለመደ ነው፡፡

አንድ አገር በተለይ ከአሃዳዊነት ወደ ፌደራል ስትዋቀር ቀድሞ የሚነሳው የፌደሬሽኑ አባላት የሚሆኑት፣ ክልልም ይባሉ ሌላ፣ እንዴት እንደሚካለሉና እንደሚዋቀሩ መስፈርቶቹን የመለየት ጉዳይ ነው፡፡ መስፈርቶቹን ከተለዩ በኋላም የሚነሱ ሁለት ተግባራት አሉ፡፡ የክልሎቹን ድንበር በወረቀት ማለትም በካርታና በስምምነት ማስቀመጥ (delimitation) እና በወረቀት ላይ የተቀመጡትን በተግባር ወደ መሬት በማውረድ የማስመርና ማካለል ወይም ድንበር መደካት (demarcation) ሥራዎች ናቸው፡፡

አገሮች አስቀድመው የድንበር ኮሚሽን በማቋቋም ስንት ክልሎችና ወሰናቸው የሚያርፍበትን ቦታ ጭምር ለይተው በማቅረብ የሕገ መንግሥቱ አካል እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለዚህ ምሳሌ ናት፡፡ ከበርካታ የሙያ ዘርፍ የተውጣጡ የፖለቲካ ሹመኞች ሆነው የማያውቁ ሰዎች የተካተቱበት አንድ ኮሚሽን በማቋቋም ስንት ክልሎች እንዲሁም ምን ምን ጉዳዮችን መስፈርት በማድረግ እንደሚዋቀሩ ባቀረቡት አስተያየት መሠረት አገሪቱ ከእንደገና ተዋቀረች፡፡ በተለይም ዘርን፣ ቀለምንና ብሔር ጋር የተያያዙትን እንዲቀሩ አሳሳበ፡፡

ሕገ መንግሥታቸው ከፀደቀም በኋላ ቢሆን በሕገ መንግሥቱ ስለ ድንበር ለውጥና አከላለል እንዲሁም ስለ ድንበር ኮሚሽን ያካተቱም አሉ፡፡ ናሚቢያን ብንወስድ፣ እንደምን በማድረግ ክልል መዋቀር እንዳለበት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሚመራ ኮሚሽን አቋቁማ በተለይ ዘርን ለፖለቲካ አስወግደው ከእንደገና በተሳካ ሁኔታ አገራቸውን አካልለዋል፡፡ የክሎቹን ብዛት እንዲሁም ዋና መስፈርቱ አገራዊ የልማትና ማኅበራዊ ትስስር መሆን እንዳለበት ባስቀመጠው መሠረት ተፈጸመ፡፡

ናይጄሪያ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የድንበር ለውጦችና ክልሎችን እንዲካለሉ አድርገዋል፡፡ ከሦስት ወደ ሰላሳ ስድስት ሲያድጉ ብዛታቸውንም ድንበራቸውንም በሕገ መንግሥቱ በሌሉ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በተቋቋሙ ኮሚሽኖች አሳክተዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካና ናሚቢያ በተለየ የናይጄሪው በአንድ ክልል ውስጥም ይሁን በፌደራል ደረጃ የብሔር የበላይነትና የበታችነት እንዳይኖር ተግተው በመሥራት አቃልለውታል፡፡ በግብነት ይዘውት የነበረውም ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማፋጠን፣ አሳታፊ ዴሞክራሲ፣ የተመጣጠነ ውክልና ያለበትና የተረጋጋ የፌደራል መንግሥት፣ የብሔር የበላይነትና የበታችነትን ማስወገድ ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት በብሔሮች መካከል የነበረው ጥላቻና ጥርጣሬ ስላደገ  እሱን ለመቀነስና ለመቅረፍ ተጠቅመውበታል፡፡

ቀድሞ የተለያዩ አገሮች ኋላ ላይ በፌደሬሽን ሲዋሃዱ ብዙ ጊዜ ችግር አይከሰትም፡፡ ቢሆንም ግን፣ በክልሎች መካከል የሚነሳን የድንበር ውዝግብ ለመቅረፍ ሲባል የፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የድንበር ውዝግብ የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ስላልሆነ በስምምነት ከሚፈታው በመለስ ላለው ጉዳይ ኃላፊነቱ የፌደራል መንግሥት ስለሆነ ሕግ ማውጣትም መቆጣጠርም መከታተልም ይጠበቅበታል፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ለዚህ ጥሩ ዋቢ ነው፡፡

የድንበር ኮሚሽን ማቋቋም፣ ዝርዝር ኃላፊነትና ተግባር በሕግ መስጠት፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ ባለሙያዎችን እንዲያካተት ማድረግ፣ ለኮሚሽኑ ተገቢ ጊዜ በመስጠት ስለ ድንበር ሁኔታ እንዲያጠና ማድረግ ይገባል፡፡ ልማትና ዕድገትን፣ መሠረተ ልማትን፣ ብሔርን፣ የተፈጥሮ ሀብትን፣ የቦታ አቀማመጥን አስተዳደራዊ ምቹነትንና ትራንስፖርትን ማሰብ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት በዋናነት ኃላፊነት አለበት፡፡ የምርጫ ወረዳን ለማካለልም እንዲሁ ይኼው ተቋም ጠቀሜታ አለው፡፡ እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እንደ ድሬዳዋ ዓይነት መስተዳዳሮችን መዋቀርንም ማሰብ ይገባል፡፡ በተለይ ሁሉትና ከዚያ በላይ የሆኑ ብሔሮች ተዋህደው በሚኖሩባቸውና ግጭት በሚፈጠርባቸው ቦታዎች ሆነው  በግልጽ ወደ አንዱ ክልል ማጠቃለል የማይቻል ሲሆን፡፡

ለማጠቃለል

በአሜሪካ ድንበር የሚካለለው በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥርና ክትትል መሆን እንዳለበት ሕገ መንግሥታቸው በአንቀጽ 4(3) ላይ ተደንግጓል፡፡ በሌላ ሕጋቸውም ድንበር ሲባል መሬት ላይ በቀያሾች አማካይነት የሚቀመጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ብሔሮች ተሰራጭተው ሲኖሩ ማንነታቸውን መሠረት በማድረግ መከለል ያስቸግራል፡፡ እንዲህ ሲሆን የተለያዩ መስፈርቶችን በአንድነት መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ቅማንት እንደሚገኝበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ድሬዳዋ እንደ ከተማ መስተዳደር የተዋቀረችበትንም አጋጣሚ ማንሳት ይቻላል፡፡ ወደ አንድ ክልል ማካተት ሲከብድ እንዲህ ዓይነት ዘዴ መፈለግም ያስፈልጋል፡፡

የአርብቶ አደሮች (ተዘዋውሮ አደሮች) ስለ ድንበር ጉዳይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደርጉ የማድረግ አስቸጋሪነትና ኑሯቸው ከአየር ሁኔታ መለዋወጥ ጋር የሚለዋወጥ መሆኑ መፍትሔውን ዘላቂ እንዳይሆን ስለሚያደርገው በዚህ መንገድ የሚሰጠው ውሳኔም ሊጤን ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም ድንበር ሲካለል በወረቀት ማለትም በካርታና በውል መቀመጥም ይገባዋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በቋሚ ምልክት ድንበሩን መለየት ይገባል፡፡ እዚህ ላይ አሁንም የሚያስቸግረው በአርብቶ አደሮች ዘንድ ቋሚ መስመር ማስቀመጥ በራሱ ፈታኝ ነው፡፡ ለማኅበራዊ መሠረታቸው የሚስማማ ማለትም የጎሳ መሪዎችን ፈቃድ በተለያዩ መንገድ ማግኘት ለወዲያው መስማማት የመጣ ቢመስልም፣ ውሎ አድሮ ግን መልሶ ማፍረስ የተለመደ መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡

ተርሚነስ፣ በጥንት ዘመን የሮማውያኖች የድንበር አምላክ ነበር፡፡ ገዥም ይሁን ተራ ግለሰብ በሚኖረው ግዛት ወይም መሬት እንዲሰፋለት ስለሚፈልግ ድንበር ማስፋት የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ድንበር በማገፋት ምክንያት በርካታ ሕይወት መጥፋትም እንዲሁ፡፡ ይህን በድንበር አማካይነት በሚመጣ ግጭት ሕይወት እንዳያልፍ፣ ንብረት እንዳይወድም ብሎም ድንበራቸውን እንዲጠብቅላቸው የሚገብሩለት አምላክ ነበራቸው፡፡ በዘመናችን ደግሞ እንደ ተርሚነስ አገሮች ሕግጋትና አሰፈጻሚ ተቋማት አሏቸው፡፡ ሕይወት እንዳይቀጠፍና ንብረት እንዳይወድም የሚጠቀሙባቸው፡፡ ኢትዮጵያም እንዲሁ ቢኖራትም ቅሉ ውጤታማነታቸው ጥያቄ ውስጥ ስለሆነ አለመግባባትን የሚፈታ ተርሚነስ ያስፈልገናል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በአዲስ አበባ ከ700 ሺሕ በላይ የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ 716,624 የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ የአዲስ አበባ...

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ተስፋ የተጣለባቸው የንግድ ማዕከላት

ፆም ሲገባ ዋጋቸው ከሚጨምሩ የምግብ ፍጆታዎች ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ...

የወጣቶችን ፈጠራ የሚያስቃኘው የስታርት አፕ ዓውደ ርዕይ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ...

በግጭት ለተጎዱ ልጆች 80 ሺሕ መጻሕፍት ማሠራጨት መጀመሩን ኢትዮጵያ ሪድስ አስታወቀ

በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ከትምህርት ቤት ለተስተጓጐሉ፣ በሥነ ልቦናና በሌሎች...