ገዢው ፓርቲን ጨምሮ ከጥቂት ሳምንት በፊት የቅድመ ድርድር ውይይት የጀመሩት 22 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዓርብ የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ውይይት አደረጉ፡፡ በውይይቱ ወቅት አሁንም ያልተፈቱ ልዩነቶች ተንፀባርቀዋል፡፡
ውይይቱን የመምራት ኃላፊነት ለገዢው ፓርቲ ተሰጥቶ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በመሩት የዓርቡ መድረክ፣ ባለፈው ሳምንት የክርክርና የውይይት ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ በቀረበበት ወቅት የየራሳቸውን ሐሳቦች ይዘው በመምጣት ዳግም ለመወያየት በተስማሙት መሠረት ነበር ተገናኝተው የተወያዩት፡፡
በተለይም ፓርቲዎች ውይይታቸውን ለወደፊት ማስቀጠል የሚያስችለውን የሕግ ማዕቀፍ ለመቅረፅ፣ ለረቂቅ ሕጉ መጠሪያ ስያሜና በሕጉ ዓላማ ዙሪያ በቡድንና በተናጠል እንዲያዘጋጁ የቤት ሥራው ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
በሁለቱም አጀንዳዎች ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ተካሂዶ ፓርቲዎች በሕጉ ዓላማ ዙሪያ በቀረቡ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ በአንፃሩ ለበርካታ ሰዓታት አጨቃጫቂ በነበረው የሕጉ ስያሜ ላይ ባለመስማማታቸው በይደር አልፈውታል፡፡
በተለይም የመድረክ ተወካይ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የኤዴፓ ዶ/ር ጫኔ ከበደና ሌሎች የፓርቲ አመራሮች የሕጉ ስያሜ ድርድርን ብቻ የሚገልጽ መሆን አለበት በማለት ሲከራከሩ፣ ገዢው ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ ሕጉ ከድርድር በተጨማሪ ክርክርና ውይይትን የያዘ መሆን አለበት በማለት ተከራክረዋል፡፡
በስያሜው ላይ አብዛኛዎቹ ተሳታፊ የፓርቲዎች ወኪሎች የየራሳቸውን ሐሳብ፣ ሥጋትና ምክንያቶችን ለበርካታ ዙሮች ያቀረቡ ቢሆንም በሁለቱም ወገኖች ጠንካራ ክርክሮችና መልሶች ተሰምተዋል፡፡
በዚህም ጉዳይ ላይ ክርክሩ እየከረረ በመምጣቱና ረዘም ያለ ሰዓት በመውሰዱ፣ በሰብሳቢው በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ አማካይነት በቀረበው የይደር ሐሳብ መሠረት በሚቀጥለው ውይይት አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ፓርቲዎች ተስማምተዋል፡፡
በተጨማሪም ፓርቲዎች በጋራና በተናጠል ባቀረቧቸው የሕጉ ዓላማ የመነሻ ሐሳቦች ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክሮች የተካሄዱ ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ ስምምነት ላይ ተደርሶባቸዋል፡፡
በኢሕአዴግ በኩል ከአቶ ሽፈራው በተጨማሪ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴና አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ተሳታፊ ነበሩ፡፡
የሚቀጥለውን ዙር ውይይት ሐሙስ የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማካሄድ ቀጠሮ በመያዝ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡