Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበአዲስ አበባ ለሰባት ቀናት የሚቆይ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

  በአዲስ አበባ ለሰባት ቀናት የሚቆይ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

  ቀን:

  – ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ለመድረስ ታቅዷል

  የሕፃናትን ሕይወት በአጭሩ ከሚቀጥፉ በሽታዎች አንዱ የሆነውን ኩፍኝ ለመከላከል ለሰባት ቀናት የሚቆይ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ በአዲስ አበባ ተጀመረ፡፡

  የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጀመረውና የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚያበቃው የክትባት ዘመቻ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ 15 ዓመት ያሉ ሕፃናትና ታዳጊዎች የሚከተቡ ይሆናል፡፡

  የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ እንደገለጹት፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በ639 ጊዜያዊ የክትባት ጣቢያዎች ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ለመድረስ ታቅዷል፡፡

  የኩፍኝ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ መጀመሩን አቶ ሙሉጌታ ተናግረው፣ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለው የክትባት ዘመቻም፣ ከአሁን በፊት በመደበኛ የክትባት ፕሮግራም ያልተደረሰባቸው ካሉ ለመድረስና በሽታው ካልተከተቡት ወደሌሎች እንዳይተላለፍ ለማስቻል ነው፡፡

  የሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ከሚሰጡ የክትባት ዓይነቶች አንዱ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ነው፡፡ ልጆች አንድ ዓመት ሳይሞላቸው የኩፍኝ ክትባት መከተብ ያለባቸው ሲሆን፣ ያልተከተቡ ልጆች ለበሽታው እንደሚጋለጡ የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል፡፡ ያልተከተቡ ነፍሰ ጡር እናቶችና ተከትበው በሽታውን የመቋቋም አቅም ያላዳበሩም ለኩፍኝ በሽታ የተጋለጡ ናቸው፡፡

  ኩፍኝ ባላደጉ አገሮች በተለይም በአፍሪካ፣ እስያና አነስተኛ ዓመታዊ ገቢና ደካማ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ባላቸው አገሮች ከፍተኛውን ሞት ያደርሳል፡፡

  በሽታውን በክትባት አስቀድሞ ከመከላከል ባለፈ በኩፍኝ ለተያዘ ሕፃን የሚሰጥ መድኃኒት አለመኖሩን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአብዛኛው በድህነት ውስጥ የሚኖሩና በቂና የተመጣጠነ ምግብ ያላገኙ ሕፃናትን የዓይን ብርሃን መንሳትን ጨምሮ ለከባድ ትኩሳት፣ ለጉንፋን መሰል ህመም፣ ለከባድ ተቅማጥ፣ ለጆሮ ውስጥ ቁስለትና ለሳንባ ምች ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡

  በማስነጠስ፣ በሳል እንዲሁም በንክኪ እንደሚተላለፍ የሚነገርለት ኩፍኝ፣ በተለይ መከላከያ ክትባት ያልተከተቡ ሕፃናትን ለመያዝ ፈጣን ነው፡፡

  መድኃኒት የሌለውና በፍጥነት ከሰው ወደሰው የሚተላለፈውን ኩፍኝ በሽታ የመከላከያው ብቸኛ መንገድ ልጆችን በተገቢው ዕድሜ ማለትም ዘጠኝ ወር ሲሞላቸው ማስከተብ ነው፡፡

  ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የኩፍኝ ክትባት፣ አምስት ዓመት ያልሞላቸውን ልጆች ሕይወት ከመቀጠፍና ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ከመጋለጥ የሚያስጥልና በዓለም ውጤት ያሳየ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img