የትራንስፖርት አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ የሚገኘው አዲሱ የአዲስ አበባ ጂቡቲ ምድር ባቡር መስመር 106 ኮንቴይነሮችን በአንድ ጊዜ ከጂቡቲ ወደብ በመጫን የሙከራ የትራንስፖርት አገልግሎት ጀመረ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አመራሮች ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ከሰኞ ኅዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የአገልግሎቱ ሙከራ ከጂቡቲ ወደብ እስከ ሞጆ ደረቅ ወደብ የደርሶ መልስ ጉዞ መከናወኑን የኮርፖሬሽኑ አንድ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሙከራ አገልግሎቱ በሚዲያ ይፋ ያልተደረገው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ በተለያዩ ጊዜያት ሊጀምር እንደሆነ ተገልጾ ባለመጀመሩ፣ ይህንንም ሙከራ ይፋ ማድረግ አገልግሎቱ የሚጀምርበት ወቅት በቁርጥ ባለመታወቁ፣ አገልግሎቱን በሚጠብቁ ላይ ተስፋ ፈንጥቆ ማደብዘዝ ባለመፈለጉ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በተደረገው የጭነት ትራንስፖርት ሙከራ ባቡሩ 106 ኮንቴይነሮችን ከጂቡቲ ወደብ በአንድ ጊዜ በማንሳት ከአንድ ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሞጆ ደረቅ ወደብ መድረሱን፣ ተመሳሳይ መጠን ባዶ ኮንቴይነሮችንም ወደ ጂቡቲ ወደብ መመለሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህ የሙከራ የትራንስፖርት አገልግሎትም የባቡሩ ሥራ መጀመር በሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ መቅረፍ ያልተቻለውን ሰፊ ችግር በማቅለል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው መረጋገጡን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ በሙከራ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በአንድ ጉዞ የተጓጓዘውን የኮንቴይነሮች መጠን በከባድ ተሽከርካሪዎች ለማጓጓዝ፣ 53 ተሽከርካሪዎችን ማቅረብ ያስፈልግ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የሙከራ ትራንስፖርት አገልግሎቱ ስኬታማ ቢሆንም፣ ባቡሩን ሥራ ለማስጀመር የዶክመንቴሽንና የክፍያ ሥርዓቱን ማሻሻል የተመለከቱ ሥራዎች እንደሚቀሩ ከምንጮች መረዳት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በጂቡቲ በኩል የተነሱና በኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ማግኘት የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ቢገልጹም፣ የተነሱትን ጉዳዮች ግን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪም የባቡሩን ዋና መስመሮች ከጂቡቲ ወደቦችና በኢትዮጵያም ከሞጆና ከሌሎች ደረቅ ወደቦች የማገናኘት ሥራ እንደሚቀር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወደቦቹን ከባቡሩ ዋና መስመር የማገናኘት ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም፣ ከስድስት ወራት በፊት ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ይህም ማለት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ወደ ሥራ ለማስገባት በትንሹ ስድስት ወራት መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለመጀመርም በጂቡቲ በኩል የተነሱ ጥያቄዎችን በሁለቱ መንግሥታት ምክክር መፍታት እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡
ባቡሩን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወጪን በተመለከተ፣ በጂቡቲ ውስጥ ለሚደረገው 90 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍን ጉዞ የጂቡቲ መንግሥት የኃይል ፍጆታ ወጪውን ለመሸፈን ፈቃደኛ አለመሆኑ አንዱ መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል የሪፖርተር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ድንበር ድረስ የተዘረጋውን የባቡር መሠረተ ልማት ገንብቶ ለማጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግሥት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያደረገ ሲሆን፣ ከጂቡቲ ድንበር እስከ ወደብ የሚደርሰውን 90 ኪሎ ሜትር የግንባታ ወጩ የጂቡቲ መንግሥት ሸፍኗል፡፡
የባቡር ትራንስፖርቱ በአመዛኙ የሚጠቅመው ኢትዮጵያን ቢሆንም፣ የጂቡቲን የወደብ አገልግሎት በማሳለጥ ረገድም ጂቡቲ ከፍተኛ ጥቅም እንደምታገኝ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በኩል ሁለቱንም መንግሥታት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያደረጓቸው ስምምነቶች ያስረዳሉ፡፡
በመሆኑም የመሠረተ ልማቱ ባለቤቶች ሁለቱ አገሮች እንደሆኑና ድርሻቸውም የኢትዮጵያ 75 በመቶ የጂቡቲ ደግሞ 25 በመቶ እንዲሆን በቅርቡ ከስምምነት መደረሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በኢትዮጵያና በጂቡቲ ባለሙያዎች ለመምራት የሚያስችል አቅም እስኪፈጠር ድረስ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታውን ያከናወኑት ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ውል መፈጸማቸው አይዘነጋም፡፡