የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ባለፈው ሳምንት፣ ‹‹የግብፅን የዓባይ የውኃ ድርሻ ማንም እንደማይነካው ለግብፃውያን ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ›› የሚል መልዕክት በማስተላለፋቸው፣ በመግለጫቸው ማግሥትም የግብፅ የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እያወጡዋቸው ያሉ ዘገባዎችንና ግብፅ በዚህ ላይ እያራመደች ያለችውን አቋም ኢትዮጵያ እንደማትቀበል አስታወቀች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዓርብ ኅዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደናገሩት፣ ከናይል ውኃ 85 በመቶ አስተዋጽኦ ያላትን አገር ጠብታ ውኃ አትንኩብን ማለት ከሞራልም ሆነ ከሕግ አንፃር ተቀባይነት የለውም፡፡ ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ የሚያደርሰውን አካባቢያዊ ተፅዕኖና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከተ ሦስቱ አገሮች ‹‹ቢአርኤል›› የተሰኘውን የፈረንሣይ ኩባንያ ቀጥረው እየሠራ መሆኑ ይታወሳል፡፡
አጥኚ ቡድኑ የሚሠራባቸውን ጉዳዮች ለመለየት ሦስቱ አገሮች የሦስትዮሽ ድርድር እያደረጉ ነው፡፡ በዚሁ ድርድር ላይ ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር ያደረገችው የውኃ ስምምነት የተፅዕኖ ግምገማውና የሙሌትና የአለቃቀቅ ጥናቱ መነሻ እንዲሆን እንደጠየቀች፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ይህን ውድቅ እንዳደረጉ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
አቶ መለስም እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 የውኃ ስምምነቶች ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ እንዳይኖራት ያደረገ በመሆኑ ለድርድር ይዞ መቅረብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ በግብፅ የመገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አስተያየቶች ጠቃሚ እንዳልሆኑ ጠቅሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ግብፅ ለመሄድ ባቀዱበት ዋዜማ ይህ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
‹‹የተፈጥሮ ሀብታችንን ተጠቅመን ከድኅነት መውጣት የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህንን ለማድረግ ደግሞ የማንንም ቡራኬ አንጠበቅም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹የውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ያላትን ሀብትና ሰብዓዊ አቅም አስተባብራ ትጠቀማለች፡፡ ከእነዚህ ሀብቶቻችን አንዱ ደግሞ የዓባይ ውኃ ነው፡፡ ይህንን አትጠቀሙ ማለት ከድህነት ጋር ተቆራኝታችሁ ኑሩ ማለት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች ላይ ጉዳት ታደርሳለች ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፣ ከዚህ በፊት ታደርገው እንደነበረው ወደፊትም ከአገሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡
የዜሮ ድምር ዲፕሎማሲ ጠቃሚ እንዳልሆነ የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ የተፋሰስ አገሮች ተጎጂ ከሆኑ ዘላቂ መፍትሔ እንደማይመጣ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት በሁሉም አገሮች እንዲከበር ታሳስባለች ብለዋል፡፡ የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ላይ አካሂደውት በነበረው 16ኛው ጉባዔ ላይ አጥኚ ድርጅቱ የሚሠራባቸውን መሥፈርቶች ለማርቀቅ ያደረጉት ስብሰባ እልባት እንዳላገኘ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ሦስቱ አገሮች በጉባዔው ላይ ቀሪ የድርድር ነጥቦችን ካይሮ ለማጠናቀቅ ቀጠሮ ይዘው ተለያይተው ነበር፡፡
ከሳምንት በፊት የሦስቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በካይሮ አካሂደውት በነበረው 17ኛው ስብሰባ ከስምምነት አልደረሱም ነበር፡፡ ከስብሰባው ማግሥት ጀምሮ የግብፅ መንግሥት የህዳሴ ግድቡን የሚቃወም መግለጫ እያወጣ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ አሁንም ጉዳዩ በድርድር እንዲፈታ እየጠየቀች ነው፡፡
ግብፅ አሁንም ድረስ የዓባይ ወንዝ ‹‹የሕይወት ወይም የሞት ጉዳይ ነው›› እያለች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ከድህነት ጋር አብሮ የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ነው እያለች ነው፡፡ የህዳሴ ግድቡ የግንባታ ሒደት ሳይጠናቀቅ እንደማይቆምም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡