Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በደረቅ ወደቦች ዕቃ ጭነው ለተከማቹ ኮንቴይነሮች ኪራይ መንግሥት በየዓመቱ እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ደረቅ ወደቦች ንብረት እንዲጭኑ ለተከማቹ ኮንቴይነሮች የመያዣ ኪራይ (ዲመሬጅ) እና የመጋዘን ኪራይ፣ መንግሥት በየዓመቱ እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል መገደዱን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ገለጸ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ደርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን የ2010 ዓ.ም. ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም፣ ረቡዕ ኅዳር 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በገመገመገበት ወቅት ነው አገሪቱ ያላግባብ ለኮንቴይነሮች መያዣና የመጋዘን ኪራይ በውጭ ምንዛሪ እየከፈለች መሆኑ የተገለጸው፡፡

ከ60 ቀናት በኋላ በደረቅ ወደቦች የቆዩ ንብረት የጫነ ኮንቴይነሮችና ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተወርሰው በሽያጭ መወገድ እንደሚገባቸው በሕግ ቢደነገግም፣ ኮንቴይነሮች በደረቅ ወደቦች በከፍተኛ መጠን መከማቸታቸው መቀጠሉ ለምን እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሥራ አፈጻጸሙን ለመገምገም ባካሄደው ውይይት ላይ፣ የተቋሙ ተቆጣጣሪ የመንግሥት አካላት እንዲገኙ ያደረገ በመሆኑ የተቆጣጣሪ ተቋማቱ አመራሮች የተገለጸው የኮንቴይነሮች ክምችት አሳሳቢና አገራዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በሰጡት ምላሽ፣ በደረቅ ወደቦች ሳይነሱ የተከማቹ ንብረት የጫኑ ኮንቴይነሮች 95 በመቶ የሚሆኑት የሌሎች አገሮች የመርከብ ኩባንያዎች ንብረት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮንቴይነሮቹ የተጫነባቸው ንብረት ተራግፎ ለሌላ ጭነት መዘጋጀት ሲኖርባቸው ወይም ለባለቤቶቹ መመለስ ሲገባቸው፣ በደረቅ ወደቦች ውስጥ እንደ ዕቃ መጋዘንነት እያገለገሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኮንቴይነሮቹ ባለመመለሳቸው የኮንቴይነር መያዣና የዴመሬጅ ክፍያ ያላግባብ እየወጣ መሆኑን፣ እንደ አገርም በየዓመቱ ከ7.5 ሚሊዮን ዶላር እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር እንደሚወጣ አስረድተዋል፡፡

ለምንድነው ንብረት የጫኑ ኮንቴይነሮች ክምችትን ማስቆም ያልተቻለው  የሚለውን ለመመለስ መንስዔውን መረዳት እንደሚያስፈልግም አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡ አስመጪዎች ንብረታቸውን ማንሳት አለመቻላቸው ዋናው የችግሩ መንስዔ መሆኑን ጠቁመው፣ በአስመጪዎቹ በኩል የሚነሳው ችግር ንብረትን ለማንሳት የሚያስፈልገውን የቀረጥ ክፍያ ለመክፈል የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ንብረቱን ካስመጡ በኋላ ገበያ የማጣት ችግር እንዳለባቸውም የሚያወሱ መሆናቸውን ዘርዝረዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩን የመፍታት አሠራር ቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትና አስመጪዎች በጋራ መክረው የሚያመነጩትን የመፍትሔ ሐሳብ ደግሞ፣ መንግሥት ተቀብሎ ሊደግፍ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ በሌሎች አገሮች አስመጪዎች ከፊል ክፍያ ፈጽመው ከፊል ንብረቶችን ማውጣት የሚችሉበት አሠራር አላቸው፡፡ በሌሎች አገሮች ደግሞ ባንኮች ኢምፖርት ፋይናንሲንግ ይከተላሉ፤›› ብለዋል፡፡

ተመሳሳይ ወይም ሌሎች አማራጮችን በመቅረፅ ወደ ትግበራ ካልተገባ ችግሩን ለመቅረፍ አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለአጭር ጊዜ መፍትሔ ግን መንግሥት ከዓለም ባንክ ካገኘው 150 ሚሊዮን ዶላር በደረቅ ወደቦች መጋዘኖች በመገንባት፣ ኮንቴይነሮችን በማራገፍ ክምችት ለማስቀረት ፕሮጀክት ተቀርፆ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ይህንኑ ችግር በተመለከተ ልዩ ኦዲት እንዲከናወን በ2009 ዓ.ም. የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን እንዳዘዙ፣ ዋና ኦዲተርም የኦዲት ሥራውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም ይህንኑ በማንሳት የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የተቋሙ  ተቆጣጣሪ የሆነው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ ክልሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የመጨረሻ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባው አሳስቧል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች