በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት ለተጀመረው የማከፋፈያ መስመሮች ማሻሻያ የአፍሪካ ልማት ባንክ 101.4 ሚሊዮን ዶላር ሰጠ፡፡
ባንኩ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ከተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ውስጥ 15.2 ሚሊዮን ዶላሩ በስጦታ መልክ የተበረከተ ሲሆን፣ ቀሪው 86.26 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ወለድ በብድር መቅረቡን አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ የጀመረው የኤሌክትሪክ መስመሮችን፣ ማከፋፈያዎችንና ማስተላለፊያዎችን የማሻሻል ሥራ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ይገመታል፡፡
የግንባታ ሥራዎች፣ 545 ኪሎ ሜትር መካከለኛ ቮልቴጅ መሸከም የሚችል የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋት፣ 582 የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮችን ነቅሎ አዲስ የመትከል፣ እንዲሁም 14 ዋና ሰብ ስቴሽኖች (ማከፋፈያ ጣቢያዎችን) ማሻሻልና አዲስ የመቆጣጠርያ ጣቢያ መገንባት የፕሮጀክቱ ዋና ዋና ተግባሮች ናቸው፡፡
ይህንን ፕሮጀክት የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) እና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ የፋይናንስ አቅርቦት እየደገፉት ነው፡፡ እስካሁን 216.87 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ የዚህን ፕሮጀክት ሥራ እያከናወነ ያለው ፓወር ቻይና የተባለ ኩባንያ ነው፡፡