Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የለስላሳ መጠጦች አምራች ኩባንያ ኦሮሚያ ውስጥ 720 ኩንታል ስኳር ተወረሰበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ሦስት ከተሞች ኮካ ኮላና ሌሎች ለስላሳ መጠጦችን የሚያመርተው ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ፣ ለባህር ዳር ፋብሪካው ሲያጓጉዘው የነበረው 720 ኩንታል ስኳር በኦሮሚያ ክልል ጎሃፅዮን ከተማ ተወረሰበት፡፡

ሪፖርተር ከኩባንያው ምንጮች ለማወቅ እንደቻለው በጉዞ ላይ የነበረው የጭነት ተሽከርካሪ በሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ በምትገኘው የጎሃፅዮን ከተማ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በፖሊስ እንዲቆም ተገዶ፣ የጫነውን 420 ኩንታል እንዲያራግፍ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት ተጨማሪ ሦስት ኤፍኤስአር አይሱዙ ተሽከርካሪዎች በድጋሚ 300 ኩንታል ስኳር እንደጫኑ እንደተያዙበትም ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የኩባንያው ኃላፊ ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡ የተወረሰው 720 ኩንታል ስኳር በሕጋዊ መንገድ የተገዛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ካገኛቸው ሰነዶች ለማየት እንደተቻለው ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ የተወረሱትን ጨምሮ ለፋብሪካው ግብዓት የሚውል 20,498 ኩንታል ስኳር፣ ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የአዳማ መጋዘን ክፍያ ፈጽሞ ተረክቧል፡፡

የምርቶቹን ሕጋዊነት ኮርፖሬሽኑ ለኦሮሚያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኅዳር 14 እና ቀደም ብሎ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ያረጋገጡ ሲሆን፣ የተያዘበት ስኳር እንዲለቀቅለትም ጠይቋል፡፡

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮውም ከኮርፖሬሽኑ የተጻፉለትን ደብዳቤዎች ስኳሩን ለወረሰው የወረጃርሶ ወረዳ ፖሊስ መምርያ ጽሕፈት ቤት አያይዞ፣ ስኳሩ እንዲለቀቅ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ሪፖርተር የወረዳውንም ሆነ የክልሉ ፖለስ ኮሚሽን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ ኃላፊዎችም ቀድሞ የተወረሰው ስኳር ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ መከፋፈሉ እንደደረሳቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዘግይቶም ቢሆን የሁለቱን ተሽከርካሪዎች ጭነት ለማስመለስ ኩባንያው ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ ስኳር፣ ጨው፣ ዘይትና የተለያዩ ዕቃዎች መያዛቸው ይነገራል፡፡ በተለይ የኮንትሮባንድ ዝውውር ለመግታት በፀጥታ ኃይሎችና በነዋሪዎች እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ በአዎንታዊ መንገድ ቢታይም፣ ሕጋዊንና ሕገወጡን በመለየት ረገድ ያለው አሠራር ጥያቄ ይነሳበታል የሚሉ አሉ፡፡

በጥቅምት ወር በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ ከተማ በመጓጓዝ ላይ የነበረ ስኳር ላለማሳለፍ በተፈጠረ ሁከት፣ ከአሥር በላይ ሰዎች መገደላቸው አይዘነጋም፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች