Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምልዓተ ጉባዔ ለጥቂት ተሟልቶ የተካሄደው የፓርላማ ውሎ

ምልዓተ ጉባዔ ለጥቂት ተሟልቶ የተካሄደው የፓርላማ ውሎ

ቀን:

  • የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመርቷል

ፓርላማው ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. የነበረውን መደበኛ ስብሰባ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ምልዓተ ጉባዔ ለጥቂት በማሟላት፣ ለዕለቱ በያዛቸው ሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ፓርላማው መደበኛ ስብሰባውን የሚያካሂደው ምልዓተ ጉበዔው ሲሟላ መሆኑንና ምልዓተ ጉባዔውም ከጠቅላላ አባላቱ ከግማሽ በላይ ሲገኙ እንደሆነ፣ የፓርላማው የሥነ ሥርዓትና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ይደነግጋል፡፡

በዚህም መሠረት ከምክር ቤቱ አጠቃላይ 547 አባላት መካከል 275 እና ከዚህ በላይ የተገኙ እንደሆነ ምልዓተ ጉባዔው ተሟልቶ መደበኛ ስብሰባው ሊካሄድ ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የዕለቱ መደበኛ ስብሰባ መበተን ይኖርበታል፡፡

ባለፈው ሐሙስ የነበረው መደበኛ ስብሰባ ከመበተን የተረፈውም ከአጠቃላይ አባላቱ 275 አባላት ብቻ ተገኝተው ነው፡፡ በሁለት ረድፍ ከተከፈለው የፓርላማው መቀመጫዎች በእጅጉ ሳስቶ የታየው የኦሕዴድ አባላት ረድፍ ነው፡፡ ፓርላማው ለሐሙስ መደበኛ ስብሰባው የያዛቸው ሁለት አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ እነርሱም የንግድ ሚኒስትሩ በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች የሚሰጡትን ምላሽ ማዳመጥ፣ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆ ለፓርላማ የላከውን የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ በዝርዝር ሲመለከት የነበረው የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን የውሳኔ ሐሳብ ማፅደቅ ናቸው፡፡ ለንግድ ሚኒስቴር ጥያቄ ለማቅረብ የተመዘገቡ 12 የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎቻቸውን ማቅረብ የነበረባቸው ቢሆንም፣ የተወሰኑት በዕለቱ ባለማግኘታቸው ጥያቄዎቻቸው አልቀረቡም፡፡ ለሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የብር ምንዛሪ ተመን ለውጥ ከተደረገ በኋላ፣ የተስተዋሉ የዋጋ ጭማሪዎች ተገቢነትን በመከታተል የተወሰዱ የማረም ዕርምጃዎችን በተመለከተ እንዲያብራሩ የቀረበው ተጠቃሽ ነው፡፡

የንግድ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረ ብሔራዊ ኮሚቴ የብር ምንዛሪ ተመን ለውጡ ከተደረገ በኋላ፣ ነጋዴዎች የሚያደርጉት የዋጋ ጭማሪ ሚዛናዊ መሆኑን ለመረጋገጥ እየሠሩ መሆኑንና በአንዳንድ ምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ያደረጉ አምራቾችን በማረም ማስተካከል መቻሉን ገልጸዋል፡፡ የጎዳና ላይ ንግድ መስፋፋትን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም የጎዳና ላይ ንግድን ፈር ከመስያዝ ውጪ፣ ማጥፋት እንደማይቻልና ይህንንም ማድረግ የቻለ አገር ተሞክሮ የለም ብለዋል፡፡ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የወደፊት ሕጋዊ ነጋዴዎች ስለሚሆኑ ማገዝና የጎዳና ንግድን ፈር ማስያዝ እንደሚገባ፣ በዚህ ትኩረት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን በጋራ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛ አጀንዳ ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ፓርላማው ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ቀርቦ የነበረውን የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ፣ በዝርዝር እንዲመለከት የተመራለት፣ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን የውሳኔ ሐሳብ ማፅደቅ ነበር፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ፓርላማው ደግሞ እንዲያፀድቀው የተመራ ሲሆን፣ ፓርላማውም ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የመጀመሪያ ውይይት አድርጎበት በዝርዝር ዕይታ ለተገለጸው ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የከተማ ፕላን አዋጅ ቀጥር 574/2000 ሙሉ በሙሉ የሚተካ፣ በፌዴራሉ መንግሥት የበላይ ኃላፊነት በመላ አገሪቱ ከተሞች የተቀናጀና ተመጋጋቢ የሆነ የከተማ ፕላንን መፍጠርና ተግባራዊ ማድረግ ዓላማው አድርጓል፡፡

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ ሰባት ሥር ሊዘጋጁ የሚገባቸው የፕላን ዓይነቶችና ተዋረዳቸው ተዘርዝሯል፡፡ አገራዊ የከተማ ልማት ፕላን፣ ክልላዊ የከተማ ልማት ፕላን፣ የከተማ አቀፍ ልማት ፕላንና ስኬች ፕላን ሊዘጋጁ የሚገባቸው የከተማ ፕላን ዓይነቶች ሲሆኑ፣ የተዘረዘሩበት ቅደም ተከተልም ተዋረዳቸው እንደሚሆን በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል፡፡

አገራዊ የከተማ ልማት ፕላን ማለት በአገር አቀፍ ደረጃ የከተማ ልማትና የአከታተም ሥርዓትን የሚያሳይ ፕላን ዓይነት መሆኑንና በይዘቱም የአገሪቱን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች መሠረት በማድረግ ዋና ዋና የልማት ቀጣናዎችን፣ የአገሪቱን ሥርዓተ ከተማና የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ያካተተ ስለመሆኑ በረቂቁ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

በተያያዘም ከተሞች ከገጠራማ አካባቢዎችና ከሌሎች ከተሞች ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ትስስር፣ እንዲሁም አኀጉራዊና ዓለም አቀፍ ትስስርን የአገር አቀፍ የከተሞች ልማት ፕላን እንደሚያካትት ረቂቁ ይገልጻል፡፡

ክልላዊ የከተማ ልማት ፕላን ዓይነት በበኩሉ በክልል ደረጃ የከተማ ልማትና የአከታተም ሥርዓትን የሚያሳይ መሆን እንዳለበትና አገራዊና ክልላዊ ፖሊሲዎችን፣ ዋና ዋና የልማት ቀጣናዎችን፣ የክልሉን ሥርዓተ ከተማ፣ እንዲሁም የመሬት አጠቃቀም ሥርዓትን የሚያብራራ መሆን እንደሚገባው ይገልጻል፡፡

በተጨማሪም ከተሞች ከከተሞች ጋር የሚኖራቸውን ትስስር፣ እንዲሁም ክልሎች ከክልሎች ጋር ሊኖራቸው የሚገባን ትስስር ክልላዊ የከተማ ልማት ፕላን ይዘት ማብራራት እንደሚጠበቅበት በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡

የከተማ አቀፍ ልማት ፕላን ደግሞ በከተማ ደረጃ የሚዘጋጅ ሆኖ በውስጡም መዋቅራዊ ፕላን፣ ስትራቴጂካዊ ፕላን፣ መሠረታዊ ፕላንና ስኬች ፕላን የተሰኙ የፕላን ዓይነቶች እንደሚያካትት ረቂቁ ይገልጻል፡፡

ከእነዚህ ዝርዝር የከተማ ፕላን ዓይነቶች መካከል መዋቅራዊ ፕላን የተሰኘው የፕላን ዓይነት የሕዝብ ቁጥራቸው ከ100,000 በላይ ለሆኑ ከተሞች የሚዘጋጅ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በይዘቱም ከተማው በአቅራቢያው ከሚገኙ የገጠር አካባቢዎችና ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚኖረውን ትስስር፣ ከተማ የሚያድግበትን መጠንና አቅጣጫ ማካተት እንደሚኖርበት ረቂቁ ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል ረቂቅ የሕግ ሰነድ ክልል ለሚለው የራሱን ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን፣ ይኸውም  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47(1) የተመለከቱት ክልሎችና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችንም እንደሚያካትት ይገልጻል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም ለፓርላማው በቀረበበት ወቅት ተነስቶ የነበረው አንድ ጥያቄ ብቻ ነበረ፡፡ እሱም፣ ‹‹ፓርላማው ይህንን አዋጅ የማፅደቅ ሥልጣን አለው ወይ? ሕገ መንግሥታዊስ ነው ወይ?›› የሚል ነበር፡፡ የተነሳው ጥያቄና ሌሎች ጉዳዮችም የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲያይ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሐሙስ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብም ይህንኑ የተመለከተ ነበር፡፡ ቋሚ  ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተጣጥሞ የቀረበ መሆኑን መፈተሽ ትኩረት ያደረገበት ጭብጥ እንደነበር ገልጿል፡፡ በዚህ ጭብጥ ጉዳይ ላይም በመጀመሪያ ከፓርላማው ጽሕፈት ቤት የሕግ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ማድረጉን፣ በመቀጠልም ረቂቅ አዋጁን ካዘጋጁት የሕግ ባለሙያዎች ጋር መወያየቱን አስረድቷል፡፡

በዚህ የምርመራ ሒደትም ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የማይጣጣም ለመሆኑ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሙሉ ድምፅ መወሰናቸውን ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የተፈጻሚነት ወሰንን በሚገልጸው አንቀጽ አዋጁ አገራዊና ክልላዊ የከተማ ልማት ፕላን፣ የከተማ አቀፍ ፕላንና ስኬች ፕላን ዓይነቶች ዝግጅትና ትግበራ የተፈጻሚነት ወሰን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(1) በግልጽ ለፌዴራል መንግሥት ያልተሰጠ ሥልጣን፣ ወይም ለፌዴራል መንግሥትና ለክልል መንግሥታት በጋራ ያልተሰጠ ሥልጣን በክልል መንግሥት ሥልጣን ሥር ይወድቃል ከሚለው ድንጋጌ ጋር እንደማይጣጣም ቋሚ ኮሚቴው በውሳኔ ሐሳቡ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን ለማስፈጸም ደንብ የማውጣት ሥልጣን እንደሚኖረው፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ደግሞ መመርያ እንደሚያወጣ፣ እንዲሁም የወጡ ደንቦችና መመርያዎች በሁሉም ክልሎች መፈጸማቸውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደሚከታተልና ጉድለቶች ካሉም ተገቢውን ማስተካከያ እንደሚያደርግ መቀመጡ አግባብ አለመሆኑን በውሳኔ ሐሳቡ ገልጿል፡፡ ምክንያቱም አዋጁ ቢፀድቅ የሚተገበረው በክልሎች ሆኖ እያለ ይህን የፌዴራል መንግሥት ተቋም ተፈጻሚነቱን እንዲከታተልና በጉድለቶች እርምት እንዲያደርግም ሥልጣን መስጠት፣ ከክልሎች ሥልጣንና ተግባር ጋር የማይጣጣም ሆነ እንዳገኘው በውሳኔ ሐሳቡ አትቷል፡፡

ይሁን እንጂ ረቂቅ አዋጁ ፋይዳ እንዳለው፣ ይኼውም የአንድ አገር የከተማ ዕድገት ትክክለኛ በሆነ መንገድ ለመምራትና ከአገራዊ የከተማ ልማት ፕላን አንስቶ፣ በየተዋረዱ እስከ የገጠር ልማት ማዕከላት ድረስ የተቀናጀና የሚመጋገብ የፕላን ሥርዓት ለማበጀት መሆኑ ተገቢ  እንደሚያደርገው ገልጿል፡፡

በመሆኑም ረቂቅ አዋጁን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(6) ላይ በተደነገገው መሠረት፣ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ሲባል በፌዴራል መንግሥት ሕግ እንዲወጣላቸው የሚያስገድዱ ለመሆናቸው የታመነባቸው የፍተሐ ብሔር ሕጎች መካከል የሚካተት መሆን አለመሆኑ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

በፌዴራል ምክር ቤቱ እንዲወሰን ረቂቅ አዋጁ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስፈላጊውን የሕግ ሒደት ጨርሶ ወደ ፓርላማው ተመልሶ እንዲመጣ፣ ለዚህም ሲባል ፓርላማው ረቂቅ አዋጁን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመራው ቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

በውሳኔ ሐሳቡ ላይ አንድ የፓርላማው አባል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ይኸውም ቋሚ ኮሚቴው ከሕጉ አርቃቂዎች ጋር በተወያየበት ወቅት ረቂቁ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ነው የሚለውን የኮሚቴው ጭብጥ አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያ፣ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ ደረጃ አፅድቆ ለፓርላማ ሲመራው ስለተገለጸው መጣረስ ግንዛቤ አልነበረውም ወይ የሚል ነበር፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ከመነሻ ማብራሪያ ለመስጠት ጠይቀው የተፈቀደላቸው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አማኑኤል አብረሃም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን አዋጅ ፓርላማው ማፅደቅ የሚችለው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ይሁንታ አግኝቶ መሆን እንዳለበት ግንዛቤ እንደነበረው፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀጥታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መምራት ስለማይችል ለፓርላማው መምራቱን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ግን አቶ አማኑአል በሰጡት ማብራሪያ አይስማሙም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ረቂቅ አዋጁ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያልፍ ማድረግ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ቋሚ ኮሜቴው ለቀረበው ጥያቄ በሰጠው ምላሽ የሕግ ሰነዱን ያረቀቁት ባለሙያዎች ፓርላማው በራሱ መንገድ ሊያፀድቀው ይችላል የሚል ምላሽ እንደሰጡ፣ ምክንያታቸውም በሥራ ላይ የሚገኘው የከተማ ፕላን አዋጅ ቁጥር 574/2000 የፀደቀው በፓርላማው መሆኑን እንዳስረዱ ገልጿል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ይህንን መነሻ በማድረግ ሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ በፀደቀበት ወቅት የተያዘውን ቃለ ጉባዔ መመርመሩን፣ በወቅቱም ተመሳሳይ ክርክር እንደነበር፣ ነገር ግን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳይመራና ይሁንታውን ሳያገኝ መፅደቁን አብራርተዋል፡፡

ፓርላማው ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ በማፅደቅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መርቶታል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቶ ፓርላማው የሚያፀድቀው ከሆነ፣ የኦሮሚያ ክልል ከሁለት ዓመት በፊት በገጠመው የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት ውድቅ ያደረገው የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ላይ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በድጋሚ  እንዲያንሰራራ፣ አልያም እንደ አዲስ ልዩ ዞኑ ሊያዘጋጀው የሚችለው ፕላን ከፀደቀው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ግን የተቀናጀና ተመጋጋቢ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

በሐሙሱ የፓርላማው ስብሰባ በርካታ የኦሕዴድ አባላት ሳይገኙ መቅረታቸው ከዚህ ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሆን የሚል ጥርጣሬ ይጭራል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዕለቱን ስብሰባ የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ግን፣ በዕለቱ የተገኙት የፓርላማ አባላት ቁጥር ማነስ ከምንም ነገር ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡

በርካታ የፓርላማው አባላት ለመስክ ሥራ በመውጣታቸው ሊገኙ አለመቻላቸውን፣ የአንድ ቋሚ ኮሚቴ 21 አባላት በመስክ ሥራ ላይ እንደሚገኙ፣ ሌሎች ከ50 በላይ የሚሆኑ አባላት ደግሞ በአፋር ክልል በተዘጋጀ አንድ ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ በመሄዳቸው የተፈጠረ መሳሳት መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎችን ኢሕአዴግና አጋሮቹ መቶ በመቶ የተቆጣጠሩት ሲሆን ከእነዚህም ወንበሮች መካከል ኦሕዴድ 178፣ ብአዴን 138፣ እንዲሁም ዴኢሕዴን 123 ወንበሮችን በመያዝ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...