Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየግለሰቦች ፍላጎት የሚያምሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

የግለሰቦች ፍላጎት የሚያምሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

ቀን:

ፊፋ (ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባሳሰበው መሠረት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከመከናወኑ አስቀድሞ የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ ተደርጓል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስመራጭ ኮሚቴውን ለመምረጥ ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የአስመራጭ ኮሚቴውን ማንነትም ይፋ አድርጓል፡፡

ምንም እንኳ የአስመራጭ ኮሚቴው በፊፋ ሕገ ደንብ መሠረት መከናወኑ በበጎ ጎኑ የሚታይ ቢሆንም፣ አስመራጭ ኮሚቴ ሆኖ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ የነበረው ሽኩቻና መጠላለፍ ግን ብዙውን የስፖርት ማኅበረሰብ ያሳዘነ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

አብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጪዎች፣ በምርጫው ለመካተት በግለሰቦች መካከል የተደረገው ትንቅንቅ፣ እግር ኳሱን ለማሳደግ ቢሆን ስፖርቱ የት በደረሰ ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ የፍጥጫውና የሽኩቻው ሒደት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን፣ ግለሰባዊ ጥቅምና ክብርን ለማስጠበቅ የተደረገ በመሆኑ ለኳሱ የሚያበረክተው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይሞግታሉ፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን አመራሮች ለመምረጥ የሚደረገው የምርጫ ሒደቱ፣ በአብዛኛው ከሁከትና ንትርክ እንዲሁም ከመጠላለፍና ከብልጣ ብልጥነት መውጣት የተሳነውም፣ ወጥ የሆነ የመዋቅርም ሆነ የአሠራር ሥልት አቅዶና ነድፎ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚደረግ ፉክክር ይልቅ በአመዛኙ የግለሰቦች ፍላጎትና ክብር ጎልቶ የሚወጣበት መድረክ እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነም ያምናሉ፡፡

በዚህም የተነሳ አብዛኛው የስፖርቱ ማኅበረሰብ የአገሪቱ እግር ኳስ ያለበትን ደረጃ በማመላከት፣ ዕድገቱን ለማፋጠንና ተግባራቱንም ለመቀየስ የሚደረግ ምንም ዓይነት ምልክት የሌለው፣ በተቃራኒው ግን ትርምሱን የግለሰቦችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡ ይኼ ሁሉ ትርምስና  ሁከቱ በዕውን የእግር ኳሱን ዕድገት ለማፋጠን? ወይስ ለግል ጥቅምና ክብር? ሲሉ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ይጠይቃሉ፡፡

በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው በፌዴሬሽኑ ድምፅ ካላቸው 144 መራጮች መካከል በዕለቱ 125 ተገኝተዋል፡፡ ጉባዔው ከእግር ኳሳዊ ይልቅ፣ የወንዜነት ጽንፍ በተላበሰ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ሲንፀባረቅበት ታይቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከወር በኋላ በአፋር ሰመራ ለሚደረገው ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የአስመራጭ ኮሚቴው የሚያስቀምጠው የምርጫ አቅጣጫና ለምርጫው እነማን ብቁ ናቸው? እነማን ብቁ አይደሉም የሚለውም መለየትና የማጥራት ኃላፊነት ስላለበት ነው፡፡

ብዙዎች ‹‹ውክልና እንጂ ምርጫ›› ሊባል እንደማይገባው በገለጹት ምርጫ፣ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከማኅበራት አንድ ሰው ታክሎበት በአጠቃላይ 12 ሰዎች በኮሚቴው እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት ከአዲስ አበባ አቶ በለጠ ዘውዴ፣ ከድሬዳዋ አቶ መኰንን ደስታ፣ ከሐረሪ አቶ አብድርሃኪም አብዱርአህማን፣ ከኦሮሚያ አቶ ዲዳ ድሪባ፣ ከአፋር አቶ መሐመድ ያዮ፣ ከትግራይ አቶ አባዲ ሐዲስ፣ ከሶማሌ አቶ ፈርዓን መሐመድ፣ ከአማራ አቶ ዘሪሁን መኰንን፣ ከቤንሻንጉል አቶ ደርቤ ከበደ፣ ከጋምቤላ አቶ ባንግ ሩዌይ፣ ከደቡብ ኮሚሽነር ፍሥሐ ጋረደውና ከማኅበራት አቶ ሸዋረጋ ደስታ ሆነዋል፡፡ የአዲስ አበባውና የአፋሩ ተወካይ በደቡቡ ተወካይ ኮሚሽነር ፍሥሐ ጋረደው ሰብሳቢነት በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴነት ሲሰየሙ፣ የተቀሩት በአማራው ተወካይ አቶ ዘሪሁን መኰንን ሰብሳቢነት በአስመራጭ ኮሚቴነት እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ የኦሮሚያና የትግራይ ክልሎች ቀደም ሲል ያቀረቧቸውን ተወካዮች ቀይረዋል፡፡ የወከሉዋቸውን ዕጩዎች ማንነት ግን ይፋ አላደረጉም፡፡ የቀድሞዎቹ ለፕሬዚዳንትነት አቶ አንተነህ ፈለቀ፣ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደግሞ አቶ ታምራት በቀለ ነበሩ፡፡ ክልሉ ዕጩዎቹን የቀየረበት ምክንያት ይፋ አላደረገም፡፡

የቀሩት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ግን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ተጨማሪ ዕጩዎችን ማቅረባቸውና በማቅረብ ላይ ስለመሆናቸው ጭምር ታውቋል፡፡

ይሁንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለይ ዕጩዎችን በማቅረብ ሒደት ላይ መተዳደሪያ ደንቡ በአብዛኛው ለትርጉም አሻሚ በመሆኑ አከራካሪ ጉዳዮች እየተነሱበት ነው፡፡ ለዚህ በማሳያነት በመተዳደሪያ ደንቡ በአንቀጽ 8 እንደተጠቀሰው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አባላት የሚባሉት የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በባለቤትነት የሚያወዳድራቸው የፕሪሚየር ሊግ፣ የከፍተኛ ሊግና የብሔራዊ ሊግ ክለቦች እንዲሁም የሴት ተጨዋቾች፣ የዳኞች፣ የአሠልጣኞችና የወንዶች ተጨዋቾች ማኅበር መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ነገር ግን ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊም ሆነ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ዕጩ ተደርገው የቀረቡበት መንገድ ከዚህ በተቃራኒ በክልሎች ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ድጋፍ የክልል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ስለመሆናቸው ጭምር እየተናገረ ይገኛል፡፡

በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ፣ አንድ ዕጩ አባል ለፕሬዚዳንታዊ ሆነ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ መወዳደር የሚችለው በአባል ክልል ፌዴሬሽን ወይም ማኅበር ተደግፎ በመወዳደሪያ ቅጽ ላይ ፎቶግራፍ ተደግፎና የደጋፊ ማኅበሩ ማኅተም ተደርጎበት ለፌዴሬሽኑ ሲቀርብ ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት በክልሎች ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ድጋፍና ማኅተም የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የቀረቡበት ሒደት ሕገወጥ ከመሆኑ ባሻገር በዓለም አቀፉ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ‹‹የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያለበት›› ስለመሆኑ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

በተጨማሪም በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው ለአስመራጭ ኮሚቴ የተመረጡት በአብዛኛው የክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ከመሆናቸውም በላይ፣ ለፌዴሬሽኑ ምርጫ የቀረቡት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በእነዚሁ አካላት ፊርማና ማኅተም የተላኩ መሆናቸው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ምን ያህል አሻሚ ትርጉም እንዳለው ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከዚሁ በመሳነት የኢትዮጵያ ዳኞችና አሠልጣኞች ማኅበር በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የየራሳቸውን ዕጩ ማቅረብ እንደሚችሉ፣ አንዳንዶቹ ይህንኑ ጉዳይ እየተነጋገሩበት ስለመሆኑም የሪፖርተር ምንጮች ይናገራሉ፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...