ይህ አባባል በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የሚኖሩ የአያሌ ተከራዮች የብሶት ድምፅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ በተጋነነ መልክ በመጨመር ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ከምግብና ልብስ የበለጠ ፍላጎት በማሳደሩ ተከራይ ዜጎች ኑሮ ለከፍተኛ ምሬት እየዳረገ ይገኛል፡፡ ችግሩ ከዜጎች የመቋቋም አቅም በላይ በመሆኑ ተከራይ ወገኖች በመተሳሰብና በመረዳዳት ወርቃማ እሴት የተመሠረተው በጋራ ጥቅም የማመን አመለካከት በመሸርሸሩ በአገራቸውና በወገናቸው መተማመን አልቻሉም፡፡ ተስፋ መቁረጥና ስደትን መመኘት ይታይባቸዋል፡፡፡
ለመሆኑ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለከተማ ቦታና ሱቆች ኪራይ በተጋነነ ሁኔታ ዋጋ መጨመሩ ቁልፍ መንስዔ ምንድነው? በነፃ ገበያ መርኅ፣ ገበያው በአቅርቦትና ፍላጎት መጣጣም መመራት ስላለበት ነው የሚል ምክንያት ለመኖሪያ ቤት ኪራይ መወደድ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ግን ነፃ ገበያ በነፃ ውድድር፣ በፈጠራና በጥረት ለመብለጥ በሚደረገው ጠንካራ ፉክክር ምርታማነትና አገልግሎት በዓይነት በመጠን በመሻሻል ኅብረተሰቡ ፍትሐዊ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህ የነፃ ገበያ ትሩፋት በበለፀጉና በአደጉ አገሮቹ በተግባር ታይቷል፡፡
በእኛ አገር እየታየ ያለው የስም ነፃ ገበያ ጥቅሙ ሳይሆን ጉዳቱ ነው፡፡ የነፃ ገበያ ነውር ጎልቶ የወጣባቸው በመኖሪያ ቤት ኪራይ፣ በከተማ ቦታ መወደድና በንግድ ቤቶች የተጋነነ ኪራይ ነው፡፡ ለዚህ ተገቢ ያልሆነ ኪራይ ዕድገት ቁልፍ መነሻው ምንድነው?
የአብዛኛው አከራይ ባለቤቶች የሀብት ምንጭ በጥረትና በተገቢ ሥራ ያልተገኘ መሆኑ ነው፡፡ ነጋዴዎች፣ ባለሥልጣናትና የተለያዩ ግለሰቦች በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት በተገኘ ገንዘብ መኖሪያ ቤቶችንና የከተማ ቦታን እየገዙ ተገቢ ያልሆነ፣ የማያቋርጥ ከፍተኛ ገቢ በቀላሉ ያጋብሳሉ፡፡ በመሆኑም እሴት ሳይጨምሩ ወይም ጥቂት ጥረት በማድረግ ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት የሥራ መስክ የመኖሪያ ቤትና የቦታ ኪራይ በመሆኑ፣ ራስ ወዳድና ስግብግብ ዜጎች በመላ አገሪቱ በመንቀሳቀስ የሥርዓቱን ቀዳዳ እየተጠቀሙ የብዝበዛ መረባቸውን አንሠራፍተዋል፡፡ ተከራይ ዜጎችን ለብሶትና ለጭንቀት ኑሮ በመዳረጋቸው ገንዘቡ የሚገኘው በሥራ ሳይሆን በኪራይ ነው የሚል የተሳሳተና አፍራሽ አመለካከት በኅብረተሰቡ በመስፋፋት ላይ ነው፡፡ የግል ባለቤቶች የጋራ መኖሪያ የዕጣ ባለቤቶችና የቀበሌ ቤት በአነስተኛ ዋጋ የተከራዩት ወገኖች በወቅቱ የቤት ኪራይ በመጨመር ዜጎቹን በማስጨነቅ ላይ ናቸው፡፡
የችግሩ አሳሳቢነት ግልጽ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ መነሻ ደመወዝና የአንድ ጠባብ ክፍል የኪራይ መነሻ እንመልከት፡፡ በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የተጣራው የመነሻ ደመወዝ ክፍያ ከብር 2,000 በታች ነው፡፡ የአነስተኛ የቤት ኪራይ ዋጋ ክፍል መነሻ ኪራይ ብር 1,500 በላይ ነው፡፡ ተመራቂ ሠራተኛው ለቤት ኪራይ ብር 1,500 እንዲከፍል ይገደዳል፡፡ በመቶ ሲሰላ የደመወዙ 75 በመቶ መሆኑ ነው፡፡
ወጣቱ ሠራተኛ በዝቅተኛ ደረጃም ቢሆን መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ባለመቻሉ ለከፍተኛ ጭንቀትና ብሶት ይዳረጋል፡፡ መማሬ፣ ሥራ መያዜ ፋይዳው ምንድነው? ካልተማረውና ከሥራ ፈቱ በምን እለያለሁ? እና ሌሎች መሰል መሠረታዊ የኑሮ ጥያቄዎች በየዕለቱ እንዲያነሳ ይገደዳል፡፡ ለጥያቄዎቹ ግን መልስ አያገኝም፡፡ ስለሆነም በጥረት፣ በተስፋና በሒደት ለማደግ ራዕይ ያጣል፡፡ በተስፋ መቁረጥ ለማያውቀው አደገኛ ስደት ራሱን ያመቻቻል፡፡
መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የጋራ መኖሪያ ገንብቶ በዕጣ በማከፋፈልና ዜጎች በማኅበር ተደራጅተው የራሳቸው ቤት እንዲገነቡ ነፃ ቦታ በመስጠት የተለያዩ ጥረቶች አድርጓል፡፡ ነገር ግን የመኖሪያ ቤት ኪራይ መጠን መጨመር ከቶ ሊገታው አልቻለም፡፡ በተቃራኒው የቤት ኪራይ ውድነት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የቤት ኪራይ ውድነት ለመባባሱ ምክንያቱ ምንድነው?
የመጀመርያው በድጎማ ተሠርተው ለዜጎች በዕጣ የተከፋፈሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በባለ ገንዘቦች በገንዘብ መተላለፋቸው ነው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመግዛት ባለቤት የሆኑ ሰዎች የሀብታቸው ምንጭ በአብዛኛው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ በመሆኑም በሕገወጥ ባገኙት ገንዘብ የተገዛ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከፍተኛ የቤት ኪራይ በመጠየቅ ብዝበዛቸው ቀጣይና አስተማማኝ አድርገዋል፡፡ ቀሪዎቹ ያልሸጡ በዕጣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለቤቶችና በሕዝብ ድጎማ ያገኙትን ቤት በከፍተኛ ኪራይ ወገናቸውን ይበዘብዛሉ፡፡ ለምሳሌ ልደታና ባልደራስ የኪራይ መጠን እንመልከት፡፡ ከ1,500 ያነሰ የባንክ ዕዳ እየከፈሉ በሕዝብ ድጎማ በዕጣ ያገኙትን መኖሪያ ቤት እስከ 10,000 ብር ያከራያሉ፡፡ ከሕዝብ በድጎማ አግኝቶ መልሶ ሕዝብን መበዝበዝ በምንም መልኩ ትክክል አይሆንም፡፡
በዋና ዋና ከተሞች በመባባስ ላይ ያለው የቤት ኪራይ ጭማሪ የነፃ ገበያ መርህ የሚቃረን ነው፡፡ የነፃ ገበያ መርህ በውድድር፣ በፈጠራና በጥረት ዜጎች ራሳቸውን ለመጥቀም በሚያደርጉት ጥረት ምርትና አገልግሎት በመጠንና በዓይነት ይጨምራሉ፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት እየተናበቡ አገር ዕድገትና ልማት ያገኛል፡፡ መላ ኅብረተሰቡም እንደ ጥረቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል ነው፡፡ የነፃ ገበያ የመጨረሻ ግቡ በአገራችን እየታየ ያለው የቤትና የቦታ ኪራይ መወደድ ግን የነፃ ገበያ መርህ ይቃረናል፡፡ ዋና ምክንያቱ የባለቤቶች መነሻ ወደ ምንጩ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በመሆኑ ነፃ ውድድርና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አይቀበልም፡፡
የመፍትሔ ሐሳቦች
- ለችግሩ ተገቢ ትኩረት መስጠት፡- የቤት ኪራይ መወደድ ከምግብ ፍላጎት በላቀ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ መንግሥት ለስኳር፣ ዘይትና ዱቄት ከሚሰጠው ድጎማ የበለጠ ይገባዋል፡፡ ምግብና ልብስ በቁጠባና በማብቃቃት ቀንን በተስፋ መግፋት ሲቻል፣ የመጠለያ መጥፋት ችግር ግን ይህንን ዕድል አይሰጥም ተከራዮች ፆም አድረውም ቤት ኪራይ ለመክፈል እየተገደዱ ነው፡፡
- በጋራ መኖሪያ ቤት የኪራይ መጠን መወሰን
በሕዝብ ድጎማ በዕጣ የተገኘ መኖሪያ ቤት መልሶ ሕዝቡን እንዲበዘብዝ መፈለግ በምንም መልኩ ትክክል አይሆንም፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤት ኪራይ ለባንክ ብድር በሚከፍለው ሒሳብ መሠረት መወሰን ይችላል፡፡ የጋራ መኖሪያ ባለቤት ለባንክ ብድር 1,000 ብር ቢከፍል የጋራ መኖሪያው ኪራይ በምንም መልኩ ከ2,500 ብር መብለጥ የለበትም፡፡ የገንዘብ ግሽበቱ ማስተካከል እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡
- የቀበሌ ቤት ተከራይተው በከፍተኛ ገንዘብ መልሰው በሕዝብ ሀብት ሕዝቡን የሚበዘብዙ መለየትና የቤቱና የቦታው ባለቤትና በጥረት ለሚኖሩ ዜጎች በባለቤትነት ማስተላለፍ፡፡ አረጋውያንና በሽተኞች፣ አዕምሮ ደካሞች የበዝባዥ መሣሪያ እንዳይሆኑ መቆጣጠር፡፡ ይህ የኮንቴይነር ሱቆችን ኪራይ ይመለከታል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ጤናማና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በጥረትና በሥራ ለሚያምኑ ዜጎች ተገቢ ድጋፍና ዕርዳታ ቢሰጥ ምርትና አገልግሎት ይጨምራል፡፡ ለዕድገትና ልማት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ብላ በላብህ ያልሠራ አይብላ በልመናና በአቋራጭ መበልፀግ ሙስናና የኪራይ ሰብሳቢን አመለካከት ማሳያ ነው፡፡
- የግል ቤት አከራዮች የኪራይና የጭማሪ መመርያ ደንብ ማዘጋጀትና መተግበር ባላቸው ክፍት ቦታ የኪራይ ቤት እንዲገነቡ በማበረታታት የኪራይ ቤት አቅርቦት እንዲጨምር መገፋፋት ያስፈልጋል፡፡
- መንግሥት የኪራይ ቤት ችግር ከምግብ ባላነሰ አሳሳቢ የዜጎች ፍላጎት መሆኑ ተቀብሎ አስቸኳይና የዘላቂ መፍትሔ ቀይሶ መንቀሳቀስ፡፡ የኪራይ ቤት እየሠራ በተመጣጣኝ ማከራየት፣ የዜጎች የቁጠባ ባህል ለማሳደግም በሒደት የኪራይ ቤቶች የተከራዮች እንዲሆኑ አቅጣጫ መከተል፡፡
- የአከራዮችን ማንነት መለየት፣ በጥረትና በሕጋዊነት ያልተገኘ ቤት መውረስ፡፡ የሙስና አመለካከት ለመከላከል፡፡
በጥቅሉ በአሁኑ ወቅት የቤት ኪራይ ውድነት ከምግብ ሸቀጦች በበለጠ በተከራዮች ኑሮ ብሶትና ምሬት እያሳደረ ነው፡፡ በተለይ በወጣቱ ሠራተኛ ከፍተኛ የኑሮ ፈተና በመሆኑ በኑሮው ተስፋ መቁረጥና በአገሩና በመንግሥቱ እንዲያማርር ብሎም ስደትን እንዲመኝ እየገፋፋው ነው፡፡
ስለሆነም መንግሥት ለችግሩ አሳሳቢነት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠት፣ ‹‹ገንዘብ የሚገኘው በሥራ ሳይሆን በኪራይ ነው፤›› የሚለው የተሳሳተ አፍራሽና ጎጂ አመለካከት ገንዘብ የሚገኘው በሥራ፣ በጥረትና በሒደት ብቻ ነው በሚለው ገንቢና ትክክለኛ አመለካከት እንዲተካ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡
(ከዳዴ ወልደ መስቀል፣ ከአዲስ አበባ)