በቀደም ዕለት ምሣ ሰዓት ላይ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ ተቀምጠን ወጋችንን እንሰልቃለን፡፡ በስድስት ሰዓት ተኩል የጀመርነውን ወሬ ስምንት ሰዓት ሊሆን ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ቀጥለናል፡፡ ቢሮ የወዘፍኩት ሥራ ቢኖርብኝም አብረውኝ ምሣ ሲበሉ ከነበሩ ጓደኞቼ ጋር ቡና እየጠጣን እያወጋን ሳለ፣ አንድ ትልቅ ሰው አጠገባችን መጡ፡፡ አንደኛው ጓደኛችን መቀመጫውን ለቆላቸው ተቀመጡ፡፡ ካፌው በጣም ከመጣበቡ የተነሳ መቀመጫ አልነበረም፡፡
ጓደኛችን እሳቸውን ካስቀመጠ በኋላ አንደኛውን ጓደኛችንን ተደግፎ በመቆም ወሬያችንን ስንቀጠል አዛውንቱ፣ ‹‹ልጄ ተባረክ፡፡ አንተም የዕድሜ ባለፀጋ ሆነህ ኖር የሚልህ አግኝ፡፡ ከታክሲ ወርጄ እዚህ ለመግባት አንድ ደቂቃ ባይፈጅብኝም፣ ይኼው እንደምታዩት መቀመጫ በመጥፋቱ ለደቂቃዎች ባዝኜ ነበር. . .›› ብለው ከት ብለው ሳቁ፡፡ እኛም በሳቅ አጀብናቸው፡፡ አዛውንቱ ሻይ በሎሚ አዘው፣ ‹‹ወጣቶች እናንተ ግድ የላችሁም፡፡ ሥራ ቦታ ብትፈለጉም በወሬ አመካኝታችሁ ቁጭ ብላችኋል፡፡ ድሮ በእኛ ጊዜ አለቃ በጣም ይፈራ ስለነበር ዝናብ ሆነ ንዳድ፣ በረዶ ወረደም ጎርፍ አጥለቀለቀ በሰዓቱ ከች ነው፡፡ ልክ እንደ ወታደር. . .›› ብለው ሳቃቸውን ለቀቁት፡፡
እኚህ አዛውንት ተጫዋች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ነገር የሚያውቁ መሆናቸውን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብንም፡፡ ይልቁንም ተረጋግተን ወጋቸውን ማዳመጥ ጀመርን፡፡ ‹‹ተወልጄ ያደግኩት እዚሁ አዲስ አበባ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ነው፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት ደግሞ መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡ ታውቁት የለ?›› ብለው አየት አደረጉን፡፡ እኔና አንደኛው ጓደኛችን ማወቃችንን ጭንቅላታችንን በመነቅነቅ ስንገልጽላቸው፣ ‹‹መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ማለት ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን አለፍ ብላችሁ የምታገኙት ዝነኛ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስንት ትንታግ ወጣቶች ያፈራ፡፡ እኔም ከዚያ ነው የወጣሁት፡፡ የኮሌጁን ትምህርት ሁለተኛ ዓመት ላይ አቋርጬ አስተማሪ ሆንኩ፡፡ ለአሥር ዓመታት ያህል ካስተማርኩ በኋላ ትቼው ሌላ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ንግድ፡፡ ከ20 ዓመታት በኋላ ለፍቼ ጠብ የሚል ሲጠፋ የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሆኜ በዚያው ጡረታ ወጣሁ. . .›› ብለው አሁንም ሳቁ፡፡
‹‹በዚህ ሁሉ ዘመኔ ሦስት መንግሥታት አይቻለሁ፡፡ የንጉሡን ዘመን ነቅንቀን ለግብዓተ መቃብር ያበቃነው እኛ ነን፡፡ በበቂ ሁኔታ የደረጀን ስላልነበርን ግማሻችን መኢሶን፣ ሌሎቻችን ኢሕአፓ ሆነን እርስ በርስ ስንተጋተግ ደርግ አባ ጎዳዴ በጊዜያዊነት ስም ሥልጣኑ ላይ ወጥቶ አንድ ላይ ሰለቀጠን፡፡ ለክፉ የሚያደርስ ጠብ ሳይኖረን በመከፋፈላችን ብቻ ለደርግ ጨካኝ ብትር ተጋለጥን፡፡ ያለቁት አልቀው፣ የታሰሩት የእስር ቤት በር ተከርችሞባቸው፣ እግሬ አውጭኝ ያሉት ለስደት ተዳርገው፣ የተቀረነው ደግሞ በደርግ መዳፍ ውስጥ ሆነን 17 ዓመታት ነጎዱ፡፡ ይለይልን ብለው በረሃ የገቡት በለስ ቀንቷቸው ከ17 ዓመታት ትግል በኋላ የምንሊክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጠሩ፡፡ የእኛም ወጣትነት ወደ ጉልምስና፣ ከዚያም ወደ ሽምግልና ተቀይሮ ይኼው ታሪክን እንደ ተረት እናወራለን…፤›› ብለው ለመጀመሪያ ጊዜ ፊታቸው ቅጭም አለ፡፡
ይኼኔ ከሁላችንም አነስ የሚለው ጓደኛችን፣ ‹‹አባት ይቅርታ ያድርጉልኝና እኔ የዚያ ዘመን ሰዎች አይመቹኝም፡፡ እርስ በርስ ይጣሉ የነበሩት እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች ነበር፡፡ ብዙዎቹ የጻፉዋቸውን መጻሕፍት አንብቤያቸዋለሁ፡፡ በጣም ይዋሻሉ፡፡ በዚህ ላይ ለተሰውት ጓዶቻቸው እዚህ ግባ የሚባል ዕውቅና ሳይሰጡ የራሳቸውን እንግልትና የመከራ ሕይወት ይተርኩልናል፡፡ በዚህ ላይ አሁንም ያኔ በተቃራኒ ጎራ የነበሩ ወገኖቻችውን በጠላትነት ዓይን ነው የሚመለከቱት፡፡ እነሱ የዘሩትን ጥላቻና የመጠፋፋት መንፈስ በዚህ ዘመን ትውልድ ላይ እየጫኑበት ነው፡፡ ‹ያ ትውልድ› የሚባለው የዚያን ዘመን ሰው ለይቅርታና ለምሕረት ግድ ስለሌለው፣ አሁንም ቢመቸው ከመገዳደል አይመለስም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ሰላማዊ ተቃውሞን መታገስ እያቃተ ምላሹ ጥይት ብቻ የሆነው. . .›› ብሎ በቁጣ ምሬቱን ገለጸ፡፡
አዛውንቱ አንገታቸውን በይሁንታ እየነቀነቁ በሐሳቡ መስማማታቸውን ሲገልጹ ከቆዩ በኋላ፣ ‹‹ልጄ አስተዋይ ነህ፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተዋይነት ለመተራረም ጥሩ ነው፡፡ በእርግጥ ያኔ በወጣትነት ዘመን አብዮቱም ሆነ የትግል እንቅስቃሴው አዲስና ብርቅ ስለሆነ ሁሉም ሰው ስሜታዊ ቢሆን አይፈረድበትም፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ ዕልቂትና መከራ አገሪቱን የከል ሸማ ካለበሳት በኋላ መለስ ማለት መልካም ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ቢያንስ ባለፉት 25 ዓመታት ያ የተበላሸ ታሪካችን መለወጥ ሲገባው፣ ከመደብ ትንቅንቅ ትግል ወጥተን ወደ ብሔር ፖለቲካ ገባን፡፡ ብርቱ እርማት የሚያሻው ያ የተበላሸ ገጽታችን ሌላ ገጽታ ይዞ በመምጣቱ፣ እንኳን ከስህተት ለመታረም ከስህተት ወደ ስህተት መንጎድ የተለመደ ሆነ፡፡ መነጋገር የለ፡፡ መደማመጥ የለ፡፡ ሐሳብ ለሐሳብ ተለዋውጦ በጋራ ችግር ላይ መምከር የለ፡፡ ሁሉም የራሱን ትክክለኛነትና እውነት እየሰበከ ነው፡፡ እስቲ የተለያዩ አማራጮችን እንይ ሲባል ደግሞ የተለየ ነገር መስማት አይፈለግም፡፡ በእርግጥ በጣም ያማል፡፡ እኔ ይኼ እጅግ በጣም ያናድደኛል፣ ይቆጨኛል. . .›› እያሉ ተብሰከሰኩ፡፡ ሰዓቱ ረፍዶብን ስንለያይ አዛውንቱ በጥልቅ ሐዘን ውስጥ ነበሩ፡፡ እኛም የእሳቸው ተጋብቶብን የአገራችንን መፃኢ ዕድል እያሰብን እንደ ደበተን ወደ ሥራችን ተመለስን፡፡
(ኢዮብ ገናናው፣ ከገርጂ)