Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአገርን ለማዳንና ለምርጫ 2012 ለመዘጋጀት ምን ይደረግ?

አገርን ለማዳንና ለምርጫ 2012 ለመዘጋጀት ምን ይደረግ?

ቀን:

በቶላ ሊካሳ

እንዲህ እንደ ዛሬው ሳይሆን፣ በየአቅጣጫውና በየዘርፉ ትናንት ከዛሬ ይሻላል፣ ነገ ደግሞ ከዛሬ ይብሳል፣ ሁሉም ነገር ‹‹ድሮ ቀረ›› ማለት ከክፉ አመል ይልቅ የብዙ ሰው እምነት ከመሆኑ በፊት፣ የ2002 ዓ.ም የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹ታሪካዊ›› ድርድርን የኢትዮጵያ ተራማጅ ኃይሎች ተችተውት ነበር፡፡ የሚገባውን ያህልም አጣጥለውት ነበር፡፡ ከሁለት አጠቃላይ ምርጫዎችና ከድፍን ስምንት ዓመት በኃላ ዛሬ ለ‹‹ምርጫ 2012›› ዓ.ም. የሚደረገው ድርድር ሲታይ ድርድርን ድሮ ቀረ ማለት ድረስ ጭምር የኋልዮሽ ጉዞ፣ አለዚያም ባለበት መርገጥ ውስጥ መውደቃችን አሌ የሚባል አልሆነም፡፡

ለምርጫ 2002 ዓ.ም. መዳረሻ በተደረገው ድርድር አካሄድና ይዘት ላይ ልክ የዛሬ ስምንት ዓመት በዚህ ወቅት የተባለውንና የተዘረዘረውን አስታውሳለሁ፡፡ ድርድሩ ውስጥ በገቡት (እንዲገቡ በተፈቀደላቸው፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭምር በተፈቀደላቸው) ፓርቲዎች መካከል ድርድር መደረጉ፣ ጨርሶና አካቶ ውድቅ አልተደረገም፡፡ ተከባብረንና ተደማምጠን ለመደራደር ቻልን መባሉ ይበል የሚያሰኝ ጅምር መሆኑን፣ ቢሆንም ግን በምርጫ ሥነ ምግባር ላይ ስምምነት መድረሱ ሕገወጥነትንና ሸፍጥን ያለቀለት የሚያስመስል ሆይ ሆይታውና ጥሩንባው ግን የውሸት የውሸት መሆኑን በወቅቱ የተናገሩ ነበሩ፡፡ በምርጫ 1997 ግርግር ጉዳት፣ ቀውስና ጥፋት የደረሰው ‹‹አሳሪ› የሆነ የሥነ ምግባር ደንብና የጋራ መግባባት ባለመኖሩ ምክንያት አልነበረም፡፡ በሕግ የተደነገገውና በተግባር የሚፈጸመው አራምባና ቆቦ መሆናቸው ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ወዲህ፣ ገዥው ፓርቲ ወዲያ ሆነው አልገናኝ በማለታቸው ነው፡፡ ከሕግ በላይ መሆን ያለከልካይ በመቻሉ ነው፡፡

በ2002 ዓ.ም. ምርጫ መዳረሻ ጊዜ ውስጥ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ዛሬ ላይ ሲታይ በአንፃራዊነት የሚገርምና የሚደነቅ መግባቢያና ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ከሥነ ምግባር ደንብ ሌላ የአገር ሕግ ሆኖ በታወጀ ሰነድ ላይ የሕዝብን ውሳኔ በመፃረር፣ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ለመቆየትም ሆነ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ ሥልጣን ላይ የመውጣት እንቅስቃሴ እንደሚቃወሙ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና የዳኝነት ሥርዓቱ ከፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ማገልገል እንዳለባቸው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልና ተጠባባቂ ጦርም ሆነ የአካባቢ ታጣቂዎች ወራሪን ለመመከት ዳር ድንበርን ለማስበር ሲባል የተደራጁና ሠራዊቱ ከወገናዊነት ነፃ እንዲሆኑ የተደነገገ መሆኑን እንደሚገነዘቡ የሚገልጽ መግባቢያ አስቀመጡ፡፡ ተፈራረሙ፡፡ ተማማሉ፡፡

ይህ ሁሉ መሆን ያለበት ነው፡፡ በሕግም የተደነገገ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አፅድቀናል፣ በሥራ ላይም አውለናል፣ በዚህም መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ አቋቁመናል ስንል መሆን ያለበትን ማቋቋማችንና መዘርዘራችን ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ምሽግ ይዘው፣ ከየትኛውም የፌዴራልም ሆነ የክልል የሥልጣን አካል በላይ በሆነ ኃይል የተደነገጉት የሕገ መንግሥቱን የበላይነት፣ የተለያዩ የመንግሥት የሥልጣን አካላትን ነፃነትና ገለልተኛነት የሚወስኑት ድንጋጌዎች የሚሉትም ይህንን ነው፡፡

ይህ ሁሉ መሆንና መደረግ ያለበት፣ በሕግም የተደነገገ ነው፡፡ መሆንና መደረግ ስላለበት በሕግም ስለተደነገገውና በጋራም ስለሚቃወሙት ነገር መስማማት የማይናቅ ጉዳይ ነው፡፡ በጣምም አስፈላጊ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይና ያኔም ዝም የተባለው፣ የተናቀውና ዛሬም አስታዋሽ ያጣውና እንደ ዘበት ዝም የተባለው መሆን ያለበትንና በሕግም የተደነገገውን የሚያደናቅፉ፣ እንዳይሆን የሚያደርጉ ችግሮችን መለየት፣ ችግርነታቸውንና ጋሬጣነታቸውን ለማስወገድ የሚከናወኑ ተግባራትን በማስቀመጥ በእሱ ላይ መስማማት ሒደቱንም መጀመር ነው፡፡ የ2002 ዓ.ም. የፓርቲዎች ድርድር ድክመትና ስብራት ይኼኛው ነው፡፡ የዘንድሮ ድርድር ደግሞ ብሶበት በጨዋታው ሕግ መሠረት በማይሠራበት አገር የጨዋታውን ሕግ በማሻሻል ቅድሚያ ላይ፣ ሕግ ማሻሻል ያለ ብልኃትና አለ መላ አንቀጽ በአንቀጽ የሕግ ውይይት/ክርክር ውስጥ ተገብቷል፡፡

የአዲስ አበባ የኦሕዴድ አባላት ድርጅታዊ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡ የኦሕዴድ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በባሌ ሮቤና በነቀምቴ ከተሞች በመካሄድ ላይ ነው፡፡ የደኢሕዴን የብር ኢዮቤልዩ በ(. . .  አገር) የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድምቀት ተከበረ፣ ወዘተና መሰል ‹‹ዜናዎች›› የሚለቀቁት በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ድረ ገጽ ላይ ነው፡፡

አሁን ይኼ የ‹‹መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን›› ነው? ብሎ የሚጠይቅና የሚደነግጥ ጠፍቶ የየዕለቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዜና ጭምር መንግሥትና ፓርቲ እንዴት እንዴት እያደረጉ ‹‹ልብስ እንደሚጋፈፉ›› ያሰሙናል፡፡ ዋና ካሉት ዜና ይልቅ መንግሥትና ፓርቲ የመቀላቀላቸውን እውነት ያረዱናል፡፡

በአንድ በኩል የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በዓላት በውጭ አገር ሚሲዮኖችና ኤምባሲዎች፣ ከቀበሌ/ወረዳ ጀምሮ እስከ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ባሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲከበሩ ዓይናችን ያያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጽሕፈት ቤትና የመሰብሰቢያ አዳራሽ/ሆቴል ኪራይ መስጠት ሲበዛ ያስፈራል፣ ያስጠረጥራል፣ ያስጠቃል፡፡

ሕጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ከፖለቲካ ሌላ ኃይል የላቸውም፡፡ ሕግን ቢደፍሩ፣ በጉልበትም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ሥልጣን እንይዛለን ለማለት ቢሞክሩ፣ የሕግና የፀጥታው አካል ይቆነጥጣቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲስ? ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲስ? ሁሉም ፓርቲዎች በሕግ ፊት እኩዮች ናቸው? ኢሕአዴግ ሕግን ልተላለፍ ቢል በሕግ መከልከል ይችላል? የመንግሥት ዓምድ (State) እና የመስተዳድር ልዩነት በወጉ ተፈልቅቋል? ወሳኝ ጥያቄ ይህ ነው፡፡

በዴሞክራሲ ውስጥ ሥልጣን የያዘው የትኛውም ፓርቲ ቢሆን ከአውታረ መንግሥቱ ጋር ልዩ ትስስር በማበጀትና ባለማበጀት ምክንያት ፓርቲዎች ተጎጂና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ የለም፡፡ ፓቲዎች በሕግና በምርጫ ወጪና ወራጅ በመሆን ረገድ አይበላለጡም፡፡ በኢትዮጵያ ገዥውን ፓርቲ በዚህ ዓይነት መመዘኛ ከተቃዋሚዎች ጋር እኩል ማስቀመጥ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ እጅ የገባ መንግሥት “Government” ከመሆን በላይ ዓምደ መንግሥት የሆነ ያህል ነው፡፡ ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጣሉና የሚነሱ ተቃውሞን የማስተዳደርያ ዘዴ መሆን የቻሉት፣ መሰሪ መንገዶችና የፖለቲካ ሙስና ጭምር እንደ ትግል መሣሪያ የመጠቀም ዘይቤ ያለ ጠያቂ የሠፈነው፣ ሥልጣንን የመከላከልና ከተቃውሞ ጋር የመተናነቅ ተግባር ዋናው የፓርቲውና የመንግሥት ሥራ የሆነው በዚህ ምንያት ነው፡፡ በአገራችን በምርጫ አማራጭ ፓርቲ ሆኖ የመንግሥትን ሥልጣን ‹‹በተረኛነት›› መያዝ ሱሚ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡

ምርጫ ያላንዳች ጉድፍ ቢካሄድ እንኳን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ስለመኖሩ ማረጋገጫ መሆን የሚችል አይደለም፡፡ ይህን ለማሳየት ምርጫው የቆመበትን ምድርና አየር ንብረት መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡   

እንጨትና ብረት አንድ ላይ ሊበየዱ እንደማይችሉ ሁሉ ዴሞክራሲ (የሕዝብ አስተዳደር) ቡድናዊ ወገንተኛነት በተጎናፀፈ የታጠቀ ኃይልና የቢሮክራሲ አውታር ላይ መቋቋም አይችልም፡፡

ወታደራዊ ትግል ወደ ሥልጣን የመጣው ኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት የሆነው የደርግን ሠራዊት በትኖና የራሱን ሠራዊትና የፀጥታ መረብ የሥልጣኑ ጉልበት አድርጎ ነበር፡፡ በሽግግር መንግሥትነት በቀጠለበት ጊዜም በመከላከያ ኃይልነት ዕውቅና አግኝቶ ይሠራ የነበረው የራሱ ሠራዊት ነበር፡፡ በ1984 ዓ.ም. የብሔራዊ አካባቢያዊ ምርጫ ተብሎ ክልሎች በተዋቀሩ ጊዜም የቡድኖችን የታጠቁ ኃይሎች ካምፕ አስገቢ፣ ተቆጣጣሪና እምቢ ባይን ቀጪ፣ የምርጫውን ፀጥታ አስከባሪም የነበረው የራሱ ጦር ነበር፡፡ ከኢሕአዴግ ፍላጎት እንዳያፈተልክ ሆኖ በተረቀቀና በፀደቀ ሕገ መንግሥት አማካይነት በተካሄደ የ1987 ዓ.ም. ምርጫ ኢሕአዴግና ርቢዎቹ የ‹‹ኢትዮጵያ ሕዝቦች መንግሥት›› ሆነው እንደተሰየሙ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል መሆን የቻለውም በመሠረቱ የኢሕአዴግ ሠራዊት ነበር፡፡ ሠራዊቱ ከፓርቲው ወጥቶ የሕገ መንግሥቱ ተገዥ እንዲሆን ቢደነገግም፣ የውስጥ አዋቂው አቶ ገብሩ አሥራት ጭምር እንደሚነግሩን ፓርቲው የሚወያይባቸው አጀንዳዎች ትንሽ ለወጥ ተደርገው የሠራዊቱም መወያያ ይሆኑ ነበር፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም የሠራዊቱ ጭምር አመለካከት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን ኅብረ ብሔረሰባዊ ሥጋ የማሟላቱ ሒደትም የኢሕአዴግን አፅምነት አላናጋም፡፡ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይል                                           ግንባታውም የተዋቀረው በኢሕአዴጋዊ አከርካሪ ላይ ነበር (በሰው ኃይልም በአመለካከትም)፡፡

መከላከያውን ፖሊሱን አገር ምድሩን በ‹‹ሠራዊት›› የማደራጀት ኢሕአዴግ አስተሳሰብ የማጥመቅና የአመለካከት ታማኝ አድርጎ የመቅረፁ ሥራ ለአንዴም የማይቦዘንበት የዘወትር ሥራ ሆኗል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ዘመነ መንግሥት የአገሪቱ የታጠቀ ሠራዊት ለገዥው ታማኝ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀ ነበር፡፡ የእነሱን ከዛሬው ጋር ለማወዳደር ቢሞከር ግን አጠገቡም አይደርሱም፡፡ በመንግሥት መገናኛና በየስብሰባ/በየኮንፈረንሱ አጋጣሚ ከሚካሄደው ጥምቀት ባሻገር፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በወታደራዊ ሥልጠና ካሪኩለም ውስጥ ተዋቅሮ እስከ መሰጠት ጠልቀዋል፡፡ በደመወዝ፣ በሙያ ማሻሻያና በመሳሰሉት ያለው አያያዝ ከቀድሞው እጅግ የተሻሻለ መሆኑም ለጠመቃው ሥር መያዝ አግዟል፡፡

ከመደበኛው የታጠቀ ኃይል በታች በተጠባባቂ ጦር ዓላማ እየሠለጠነ ወደ ኅብረተሰብ የሚመለሰውና በተለያየ የመተዳደሪያ ሥራ ላይ እየተሠማራ፣ የታጣቂ/ሚሊሺያ ሚናን የሚጫወተው በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ኃይል አለ፡፡ የዚህ ኃይል ሰዎችን በይፋ የኢሕአዴግ አባላት ከመሆን የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ አቶ ገብሩ አሥራት እንደሚከተለው ይነግሩናል፣ “ኢሕአዴግ እንዴት ታጣቂ ሚሊሻዎችን በአባልነት ያቅፋል የሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ እነዚህማ ብረት ከማንገባቸው በስተቀር ሲቪል ናቸው . . . የሚል መልስ ይሰጥ ነበር” (ገብሩ፣ 2007፤ 369)፡፡

በተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ ቁጥር 532/1999 አንቀጽ 47(4)፣ ‹‹ማንኛውም ወታደር ወይም ፖሊስ በፖለቲካ ድርጅት ስብሰባ ወይም በምርጫ እንቅስቃሴ መለዮውን አድርጎ መሳተፍ አይችልም፤›› ይላል፡፡ ማለትም መለዮ ሳያደርጉ መሳተፍ የተፈቀደ ነው፡፡ በተግባር ያለው እውነት እንደሚነገረን ግን ተፈቃጅነቱ ለኢሕአዴጋዊ ተሳትፎ ነው፡፡ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሙን ጄኔራል ሳሞራ የኑስን በሕወሓት ስብሰባ ላይ ያለመለዮ የምናያቸው፣ ስለተጋድሏቸው ዘመንም በቴሌቪዥን ሊያወጉን የቻሉት የተፈቀደ ስለሆነ ነው፡፡ ኤታ ማጆር ሹሙን በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ማየት ግን እንኳን በዕውን በህልምም የተፈቀደ አይደለም፡፡ በተቃዋሚ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ሸብ እረብ እላለሁ የሚል ተራ ወታደር ቢከሰት እንኳ በእንጀራ ገመዱ የቆረጠ መሆን አለበት፡፡ የተሻሻለው የፓርቲዎች ምዝገባ ሕግ በአንቀጽ 58 (1፣ 2) ዳኛ፣ የመከላከያ አባልና የፖሊስ አባል በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ የፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ይከለክላል፡፡ በሁለቱ አዋጆች ውስጥ እንደሚታየው ከፖለቲካ ተሳታፊነት የተቀነሰ ነገር ቢኖር በአባልነት ተመዝግቦ መታወቂያ ካርድ መያዝ ብቻ ነው፡፡

በሌላ አባባል ከመታወቂያና ከምዝገባ መጉደል በቀር የመከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት አባልነት የኢሕአዴግ አባል የመሆን ያህል የእምነት ተከታይነት ያለበት (የሚጠበቅበት) ነው፡፡ በዚህ ረገድ መደበኛው ሠራዊት ከታጣቂው ሚሊሻ አይተናነስም፡፡ የተፃረሩ ረድፎች ባሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ‹‹ልማታዊ›› የተባለውን መስመር የእኔ እንዲል የተደረገ፣ የልደት ታሪኩን ከኢሕአዴግ የተጋድሎ ታሪክና ከግንቦት 20 ድል ጋር አያይዞ እንዲያይ የተደረገ፣ “መለስ ታላቁ መሪያችን” የሚል ለታላቁ መሪውና ለሰማዕታት በቅፅሩ መታሰቢያ የሚያቆም ነው፡፡ ይህን ያህል ወገናዊ የሆነ ኃይል መለስንና የፖለቲካ መንገዱን የሚቃወመውን የፖለቲካ ወገን እንደ ጠላት የማይቆጥረውና ከሌላው ጋር በእኩል ዓይን ሊያይ የሚችለው በምን ምትኃት ነው? ‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል›› የሚለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት (አንቀጽ 87(5)) ከዚህ ሁኔታ ጋር እንዴት ነው መጣጣም የሚችለው?

ወታደራዊ ያልሆነው የመንግሥት አውታርም ቢሆን በመሠረታዊ ፀባዩ ልማታዊና ሕዝባዊ እኔ ብቻ ነኝ በሚለው የፖለቲካ መስመር የተቃኘ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ አሁን አሁን ከ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ይልቅ የሚዘወተረው ‹‹ልማታዊነት/ልማታዊው መስመር” የሚል አጠራር ነው፡፡ አንዳንድ የዋሆች የአቋም ለውጥ የተደረገም መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ ነገሩ ግን ሌላ ነው፡፡ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ፖለቲካዊ መለያ ስለሆነ ሁሉን አቀፍ ለመሰለ አጠቃቀም አያመችም፡፡ ለዚህ የምትስማማዋ ‹‹ልማታዊነት›› ነች፡፡ ለ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ፖለቲካዊ ወገናዊነት የሌለበት መልክ ታጎናፅፈዋለች፡፡) በሥልጠናና በሴሚናር ከሚካሄድ አጠባ ባሻገር የተስፋፋ የፓርቲ አባልነት ምልመላ የሚካሄድበትና ጠቅላላ የመሥሪያ ቤቶች እንቅስቃሴዎች ከላይ እስከ ታች ድረስ በፓርቲ ሰንሰለትና ምላስ የሚዘወርበት እውነታ ነው ያለው፡፡ ከዚያ ሥር ደግሞ በቡድን በቡድን (የአንድ ለአምስት ደረጃ ድረስ የጠበበ፣ የቤተሰብ ፖሊስ እስከማቋቋም ድረስ የዘለቀ) ትብትብ አለ፡፡ በየዕለቱ ‹‹ፀረ ሕዝብነት››ን፣ ‹‹ፀረ ልማትነት››ን እየኮነነ ልማታዊነትንና አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚናኘው የፕሮፓጋንዳ አውታር ደግሞ ዙሪያ ገባ አየሩን ይቆጣጠራል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠላትነት ያልተጠማመዱ የወንበር ተፎካካሪዎች በሆኑበትና  የመንግሥት ሥራ ማካሄጃ ቋሚ አውታራትም በምርጫ አሸንፎ ለመጣ ለየትኛውም ቡድን ታዛዥ እንዲሆኑ ሆነው በተቀረፁበት ሥፍራ፣ የአንዱ ወይም የሌላው የፖለቲካ ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦች እዚህም እዚያም (በወታደሩ፣ በፖሊሱ፣ በዳኝነቱና የሥራ ገበታ ጭምር) መኖር ጉድለት አይደለም፡፡ የፖለቲካ ዝንባሌ የሥራ ኃላፊነትን ቢያደፈርስ እንኳ ጥፋቱና ተጠያቂነቱ የግለሰቦች ጉዳይ ይሆናል፡፡ ተቋማቱ ራሳቸው በአንድ አመለካከትና ፖለቲካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሞሉና ያንኑ እንዲያገለግሉ የሚጠበቁ ሲሆን ግን ነገሩ ሁሉ ይቀየራል፡፡ ችግሩ ከግለሰቦች ባለፈ ደረጃ ሥርዓታዊ ሆኖ፣ የፖለቲካ አቋም የሥራ ኃላፊነትን ለመቃኘት ሥልጣን ያገኛል፡፡ የእኛ ሁኔታ የዚህ ዓይነት ነው፡፡

በአጭሩ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ኢሕአዴግ በየአምስት ዓመቱ በምርጫ እያሸነፈ ወንበሩን የሚያፀና ቡድን ብቻ ሳይሆን፣ የሚቀመጥበት ወንበር ከካስማና ማገሩ ጭምር የራሱ ንብረት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከመንግሥትነት አልፎ አውታረ መንግሥት (State) ሆኗል፡፡ አውታረ መንግሥት ከመሆንም አልፎ ተርፎ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላትም ውስጥ መረብ ዘርግቷል፡፡ የሙያና የሕዝብ የሚባሉ ማኅበራትም ውስጥ ዓይን፣ ጆሮና አንደበቱ ገብቶ መዋቅራቸውን ተብትቧል፡፡ በዓመት አንዴ በሠራተኛ ቀን ሠልፍ መውጣት እስኪጠፋ ድረስ እንቅስቃሴያቸውን አኮማትሯል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በተስፋፋ የፕሮፓጋንዳ መዘውሩ ‹‹ባለጠላት›› ፖለቲካውን ‹‹ትክክለኛ›› ማኅበራዊ ንቃት አድርጎ ሾሟል፡፡ የዚህ ዓይነት አውታረ መንግሥት በትክክለኛ ስሙ ሲገለጽ፣ አገርን የዋጠ የፖሊስ አገዛዝ ነው፡፡ ከደርግ የሚለየው በቅርፅ፣ በአለባበስና በዝንባሌ ነው፡፡ ደርግ ሶሻሊዝም የሚባል ደበሎ የለበሰና ወደ ፍለጠው ቁረጠው ያደላ አንድ ወጥ አምባገነንነት፣ ይኼኛው ደግሞ ከእምብርት የማታልፍ ዴሞክራሲ የሚሏት ጥብቆ ያጠለቀ፣ ፌዴራላዊ ቆዳ ያለውና እስከ ጓዳ መሰለል የሚወድ አምባገነንነት ነው፡፡

በዚህ ኢሕአዴጋዊ የአገዛዝ ባህር ውስጥ ሆነው (ተቃዋሚዎች እንዲህና እንዲያ ናቸው የሚል ፖለቲካ የተሞላ የ‹‹ፖሊሲ ሥልጠና›› እየዋጡ) ዓቃቤ ሕግ፣ ዳኝነትና ምርጫ ቦርድ ውኃ የማይነካቸው ደሴት መሆን የሚችሉት እንዴት ብለው ነው?  ‹‹ሥልጠናው›› ቢቀነስ እንኳ፣ ባህሩ ብቻውን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ሳለ ምርጫ ቦርድና ዳኞች በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 102(1) እና በአንቀጽ 79(2፣3) መሠረት በሙሉ ነፃነት ተግባራቸውን ማካሄድ እንዴት ይቻላቸዋል? የሥልጣን ኃይል በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር የሆነበትንና ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ የተወራለትን እውነታ እንደታቀፉ የብሔሮች እኩልነት መረጋገጡን ለማሳመን መልፋት፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት እስከ ሕዝብ ማኅበራት የደጋፊና የፓርቲ መረብ አንሠራፍቶ፣ ካደረ አይቆረጠምም ብለው የሚያስቡትን ተቃዋሚ በስነጋና በሸፍጠኛ ውንጀላ እያሹ የፓርቲና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በምርጫ ውስጥም ሆነ በፍትሕ ሥራ ውስጥ እንደሌለ  ለማሳመን መውተርተር ውኃና ዘይትን ለማቀላቀል ከመልፋት በምን ይሻላል?

ገብሩ አሥራት አረና ትግራይ ለ2002 ዓ.ም. ምርጫ በተወዳደረባቸው ቦታዎች የኢሕአዴግን ወይም የደኅንነት አባላትን የምርጫ አስፈጻሚ ሆነው ስለማግኘታቸው፣ በሕዝብ ታዛቢነትም የኢሕዴግ አባላት ተመርጠው ስለመሳተፋቸው ነግረውናል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትም በበኩሉ የ2007 ዓ.ም. ምርጫን በተመለከተ 250 ሺሕ ታዛቢዎች በተመረጡ ጊዜ የየትኛውም ፓርቲ አባል የሆኑ ራሳቸውን እያሳወቁ ከጥቆማ ስለመውጣታቸው በዜና ነግሮናል፡፡ መጨበጥ ያለበት ቁልፉ ጉዳይ ግን የፓርቲ አባልን ነቅሶ በማውጣት ችግሩን ማስወገድ አለመቻሉ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በአንድ ፓርቲ አጠባ ውስጥ መውደቁ ገለልተኛ የመሆን ዕድልን አሰልሏል፡፡ የምርጫ ቦርድ የአናት መሪዎች በተቃዋሚ ተሳትፎ ይቅርና በተቃዋሚ ቢመረጡ እንኳ፣ ምርጫውን ገለልተኛ ለማድረግ ከላይ ተንሳፈው ሊጫወቱ የሚችሉት ሚና ኢምንት ሆኗል፡፡

ለኢሕአዴግ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ መሆኑ እንደፈለገ ለመሆን ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ሕግ አክባሪነትን፣ የምርጫ አካሄድንና ውጤትን ለእሱ ባለው ተስማሚነት እንዲለካ ይፈቅድለታል፡፡ ካስፈለገ ድምፅ ከመስጠት ያኮረፈ ዜጋን ከቤት ድረስ “ቀስቅሶ” በ‹‹ደስታ›› ምርጫ እንዲያከናውን ማድረግ ያስችለዋል፡፡ ሥውር ድርጅታዊ ሥራ ውስጥ ሳይገባም አየሩን የተቆጣጠረው ፕሮፓጋዳው በልማት ሥራዎች እየታገዘ የልብም ሆነ የእበላ ባይ ተከታዮችን ያረባለታል፡፡ ‹‹ፀረ ሕዝቦችን/ፀረ ልማትን›› የመታገሉ ተግባር በየአቅጣጫው ብዙ ወዶ ገቦች ይኖሩታል፡፡ በየትኛውም የሥራ መስክ ላይ ያሉ የኅብረተሰቡ አባላት ለኢሕአዴግ ባደላውና ተቃዋሚቹን በተፃረረው ጠላታዊ አመለካከት ለመሰልቀጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በዚህ እውነታ ላይ ዴሞክራሲን ይቅርና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ከባድ ነው፡፡ ምን ቢለፋ፣ ምን ሕዝብ ቢነቃነቅ፣ የገዥ ቡድን ተፈሪነትና የሕዝቡ ፈርቶ አዳሪነት አይቀየርም፡፡

በፖለቲካ ወንጀል የተከሰሰ ተቃዋሚ ከፖሊስ ጣቢያ አያያዝ እስከ ክስ አመሠራረት፣ ከክርክር እስከ ፍርድ ብያኔና እስከ ማረሚያ ቤት ድረስ መድልኦ ቢገጥመው የማያስገርመው፣ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና የደኅንነት ሰዎች ስብሰባ ውስጥ ሰርገው ለመበተንና ለማስፈራራት ሞከሩ ቢባል (ገብሩ፣ 2007፤ 358፡፡) ለማመን የማይከብደን ለዚህ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ መሻሻል የሚሻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከተቃዋሚ በኩል ትልቅ ቅዋሜ ሊመጣበት የቻለውም ሕጉ አያስፈልግም በሚል ምክንያት ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ ለሸፍጠኛ ውንጀላ ይጠቀምበታል በሚል እምነት ነው፡፡ ቀንቶን የጠላትነት ፖለቲካን ማፍረስ ቢሳካልንና ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን ያሚያገለግል አውታረ መንግሥት የማነፅ ሥራ ውስጥ ብንገባ እንኳ፣ ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት ፖለቲካዊ ዝንባሌን በልጦ እስኪፀና ድረስ የመከላከያ፣ የደኅንነትና የፖሊስ አባላት፣ እንዲሁም የዓቃቤ ሕግና የዳኝነት ሰዎች ከፓርቲ አባልነት ባለፈ ከየትኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ የተገለሉ እንዲሆኑ በሕግ መገደብ፣ ፈልገውም ወገናዊ ከሆነ አመለካከት ነፃ ለመሆን እንዲጣጣሩ ማሳመን ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

ፓርቲዎች በየትኛውም ሥፍራ ለመንቀሳቀስና መዋቅር ለመዘርጋት፣ ተጠናክሮም ለመወዳደር እኩል የተግባር መብት ባላገኙበት (ሜዳውን ሁሉ አንድ ፓርቲ በያዘበት) የኢትዮጵያ ሁኔታ ሰባ ምናምን ፓርቲዎች ስላሉ የብዙ ፓርቲ ሥርዓት ተቋቁሟል ማለት ቀልድ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በተደላደለባቸው አገሮች ውስጥ እንኳ ከሁለት ፓርቲ ሽክርክሪት ማለፍ ያቃታቸው የብዙ ፓርቲ ሥርዓት ለመባል አንሰው የሁለት ፓርቲ ሥርዓት ነው የሚባሉት፡፡ እኛ ዘንድ ያሉት የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመቃወም፣ ወዘተ ነፃነቶች ከዴሞክራሲ አገዛዝ ከሚፈልቁ የፖለቲካ ነፃነቶች ጋር በህልውናቸው ረገድ ለየቅል ናቸው፡፡ ከዴሞክራሲ የሚመነጩት፣ ዴሞክራሲው እስካለ የሚኖሩ፣ ቢጣሱ እንኳ ለጣሺው ተጠያቂነት ሥርዓቱ ራሱ ዋስትና ሆኖ የሚቆምላቸው ናቸው፡፡ በእኛ አገር ውስጥ ያሉት ነፃነቶች ግን በአምባገነንነት ኪስ ውስጥ ያሉ ከሲታዎች “ባለቤቱ” እንዳሻ ሊያጠባቸው/ሊዘጋቸው የሚችል፣ አስተማማኝ ህልውና የሌላቸው እንዲያውም ዕርባናቸው ለስም ታህል ከተሰፋ ቁና ወይም የተቃውሞ ዝንባሌን ለማስገሪያ የቢርቢራ ያህል ከመሆን የማይርቅ ነው፡፡ 

የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲገዙበት የታወጀው የተሻሻለው የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ (573/2000) እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር ሕግ (662/2002) ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ላይ ባለመቆማቸው ምክንያት፣ ለአንድ ፓርቲ አሸናፊነትና ገዥነት ዋስትና የሰጠውን አየር ንብረት ከማገልገል አያመልጡም፡፡ በተሻሻለው የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንቀጽ 46(2) እንደተቀመጠው፣ ከመንግሥት ለፓርቲዎች የሚሰጥ ድጋፍ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት መሀል መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር የማድረግ ሥራንም ከተደጋፊዎች ይጠይቃል፡፡ ማለትም መንግሥታዊ የገንዘብ ድጋፍ ሲወሰድ የፕሮፓጋንዳ ዕገዛ የመስጠት ቀረጥን የመክፈል ግዴታም አለ፡፡ ፓርቲዎች መዋጮ የሚሰጣቸውን ወይም ቃል የገባላቸውን አካል ስም ያካተተ የሒሳብ መግለጫ እንዲያሰናዱ የሚያዘው አንቀጽ 54(2) በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ያለው ትርጉምም፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ እረዳለሁ የምትይ ሁላ ዋልሽ! ስምሽ ተጽፎ እንደሚቀርብልኝ አውቀሽ እጅሽን ሰብሰቢ የሚል ነው፡፡

የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉም በጥቅሉ ምርጫን ተከትሎ ቅዋሜ እንዳይመጣ ፀጥታ ከማስከበር ዓይነት ያለፈ ብዙም ጥቅም የሚሰጥ አይደለም፡፡ በአንቀጽ 11 (2፣ሀ) ላይ ከግጭት ቆስቋሽነት ጋር የተቀመጠው “ስም አጥፊ” ንግግርን ማስወገድ ጥፋትንና ገመናን ከማሳየት ጋር እንዳያሻማ ሆኖ ባለመለየቱ፣ አድልኦንና ሸርን ከማጋለጥ ይልቅ ለመሸበብ ይጠቅማል፡፡ የማጋለጥ ሙከራም “የስም ማጥፋት ወንጀል” እየተባለ ሲፎከርበት ታይቷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ጊዜ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ አንቀጽ ተገን አድርጎ ሲጠቀምበት ነበር፡፡ አንቀጽ 10 “ፍትሐዊና ነፃ የምርጫ ውጤትን ስለመቀበል” የሚል ርዕስ ቢይዝም፣ በሥሩ የተደነገገው ግን የምርጫ ውጤትን ስለመቀበል ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ ተግባራዊና ፕሮፓጋንዳዊ አፈና እስከተንሠራፋ ድረስ ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ አይኖርምና ይህም አንቀጽ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን ከመቀበል ጋር ግንኙነት አይኖረውም፡፡

በአጠቃላይ ወርቅ ሕግ ቢወጣ ወይም ወርቅ አንቀጽ ቢቀመጥ ሊያሠራው ከሚያስችል ሁኔታ ጋር እስካልተገናኘ ድረስ ጥቅም የለውም፡፡ ከመዘንጋት አልፎ በአሳቻ መንገድ የመተርጎም ጥቃት ሊደርስበትም ይችላል፡፡ ለምሳሌ የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉ አንቀጽ  16(1) “ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቀጣይ ግንኙነት ፈጥሮ መንቀሳቀስ አለበት” ይላል እንጂ፣ የጋራ ምክር ቤት አባል ለመሆን የሚሻ ፓርቲ በሥነ ምግባር ሕጉ ለመስማማቱ ይፈርም አይልም፡፡ ኢሕአዴግ ግን ካልፈራማችሁ አይቻልም በሚል (አዳራሽ አላከራይም ከማለት ባልተለየ) ተንኮል የተወሰኑ ተቃዋሚዎቹን ነጥሎ ለማግለል ተጠቅሞበታል፣ የጋራ መድረኩም የኢሕአዴግ የቢሻኝ ዕቁብ ቤት ከመሆን የማይሻል ሊሆን በቅቷል፡፡

የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉ ስለሕጋዊነት (ሌጅትመሲ) (የሕጉን የእንግሊዝኛ እኩያ በቀኝ በኩል ይመለከቷል) አስደናቂ አንቀጽ አለው፡፡ አንቀጽ 5(1) ላይ ሕጋዊነትን የሚወስኑትን ሲያስቀምጥ መራጮች “ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎችና ስለዕጩዎች ባህርይ የተሟላ መረጃ ሲሰጣቸውና የራሳቸውን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ሲያደርጉ” እና “በነፃነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለፍርኃት፣ ያለተፅዕኖ፣ ያለጫና ወይም ከጉቦ ነፃ በሆነ መልኩ ድምፅ መስጠት ሲችሉ ነው” ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ከአውታራት እስከ ፕሮፓጋንዳዊ አየር በአንድ ፓርቲ ወገናዊነት የተሞላ እንደ መሆኑና ከዓመት ወደ ዓመት የሚዳብር ወገናዊነት በየአምስት ዓመት ብቅ በምትል የምርጫ ዘመቻ ጊዜ መታጠብ እንዳለመቻሉ ከፍርኃት፣ ከጫናና ከአድልኦ እንደማይመለጥ ምርጫ ውስጥ ገና ሳይገባ የታወቀ (አውቶማቲክ) እውነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ‹ሌጅትመሲ› ከተቋም አፅዳቂነት ይበልጥ በአግባብነትና በሕዝብ አፅዳቂነት (ለመታመን በመብቃት) ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ስናገናዝብ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ የተካሄዱትና ምርጫ ቦርድ ያፀደቃቸው የምርጫ ውጤቶች በሙሉ የሌጅትመሲ ደሃ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ስለነፃና ስለፍትሐዊ ምርጫ ስናወራም በኢትዮጵያ ሁኔታ ማተኮር ያለብን የድምፅ አሰጣጥ ክንዋኔ ውስጥ ገብተን ምርጫ ካርድ ዕላፊ ሄደ፣ ያልተመዘገበ መረጠ፣ ታዛቢ ላይ ጫና ተደረገ፣ ወዘተ የሚሉ ነገሮችን መልቀም ላይ ሳይሆን፣ በጥቅሉ ምርጫ ደረሰም አልደረሰ ፓርቲዎች ሁሉ ያለ አፈና ተንቀሳቅሰው ለመሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ ኖረዋል? ወይስ አንዱ አልጋ በአልጋ ሲሄድ ሌሎቹ እሾህ በሾህ ላይ እንዲጓዙ ተገደዋል? ገዥው ፓርቲ በጊዜው ባለበት ደረጃ የአድሎኛ አገዛዙን አስተናነፅ ለመቀየር ይሻል? የሚሻ ለመሆኑስ የሚያሳምን ተግባራዊ አዝማሚያ አሳይቷል? ወይስ በሥልጣን መቆየት አለመቆየቱን የልማትና የለውጡ መቀጠልና አለመቀጠል አድርጎ ይመለከተዋል? የሚሉ ትልቁን እውነታ የሚያሳዩ ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ ነው፡፡ ለዚህም የሚጎሰምለት ‹‹ድርድር›› ለሕዝብ የሚተርፍ ቁም ነገር የሚኖረው በመንግሥት አውታሩ ውስጥ ያለውን ለአንድ ፓርቲ አዘንባይነትና ገብሮ በላነት ማቃናት የሚያስችል ዝግጁነት ካለ ብቻ ነው፡፡ መሆን ያለበትና በሕግም የተደነገገው ይኸው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...