Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመሬት አልባ ወጣቶች ጉዳይ ወቅቱን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጅ እንዳይሆን ምሁራን ሠግተዋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሊቢያውያን በስደተኞች የተፈጸሙት ፀያፍ ተግባር በርካቶችን አስቆጥቷል

በአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ላይ ምሁራንና የባህል መሪዎች ከየአገራቸው በመሰባሰብ በአዲስ አበባ ሲመክሩ ሰንብተዋል፡፡ ስብሰባቸውን ሲቋጩም የአፍሪካ መሪዎች ስለወጣቶች እንዲያስቡ፣ በመሬት ፖሊሲዎቻቸው ውስጥ የወጣቶችን ባለድርሻነት እንዲያሰፍኑ የጠየቁት ተሰብሳቢዎቹ፣ የአፍሪካ ወጣቶች በአኅጉሪቱ የመሬት ይዞታ ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ ከተነፈጋቸው ወደፊት ጊዜ ጠብቀው ሊፈነዱ የሚችሉ ፈንጂዎች ናቸው ሲሉም ሥጋታቸውን ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡

የናሚቢያን የመሬትና ዳግም ሠፈራ ሚኒስቴር በመወከል በአዲስ አበባ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደው የአፍሪካ መሬት ፖሊሲ ስብሰባ ወቅት የታደሙት ፕሪስካ ማንዲምካ የተባሉ ተሳታፊ እንደተናገሩት፣ የአፍሪካ ወጣቶች አብዛኛውን የሕዝብ ቁጥር የሚወክሉ እንደመሆናቸው መጠን፣ ከመሬት ሀብት ተሳታፊ የሚሆኑበት ሥርዓት ካልተበጀ ጊዜ ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦንብ ሥጋት መሆናቸውን እኚህ ግለሰብ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

አብዛኞቹ የዚህ ስብሰባ ተሳታፊዎች ምሁራን ሲያሳስቡ የነበረውም የአኅጉሪቱ የመሬት ሥሪት በባህላዊ አስተዳደር ሥር መሆኑ መቀየር እንዳለበት ነበር፡፡ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚገመተው የአፍሪካ መሬት በአገር ሽማግሌዎች ወይም በጎሳ አለቆች የሚመራ በመሆኑ ወጣቶችን ያገለለ፣ ለወጣቶች ተሳትፎ ቦታ የሌለው በመሆኑ ከ65 በመቶ እንደሚልቅ የሚታሰበውን ወጣት ክፍል የበይ ተመልካች እንዲሆን አስገድዶታል፡፡

በርካታ ወጣቶች በግብርና በሚተዳደረው አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል ውስጥ ይህ ነው የሚባል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማጣትም ለከፋ ስደት ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ አብዛኞቹም መጨረሻው የከፋ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በባህር እየሰጠሙ ሲያልቁ ታይተዋል፡፡ በርካቶቹ በጨካኞች እጅ እየወደቁ፣ አካላቸው እየወጣና በድናቸው የትም ሲጣል ዓለም ታዝቧል፡፡

ጥቂት የማይባሉትም ለስደት የወጣው እግራቸው መጨረሻቸውን ለአሸባሪዎች ሲሳይ ሲያደረገው፣ በአደባባይ ሲታረዱ የዓለም ሕዝብ ታዝቧል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በዘግናኝ አኳኋን ከታረዱት ስደተኞች ውስጥ 30ዎቹ ኢትዮጵያውያን የመላው ዓለም መነጋገሪያ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

ከሰሞኑም በሊቢያ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ወጣቶች ለባርነት ሲሸጡ፣ እንደ እንስሳ ዋጋ እየተከራከሩና እየተጫረቱባቸው ሲገበያዩዋቸው ዓለም ታዝቧል፡፡ መከረኞቹ ስደተኞች ኑሮን ለማሸነፍ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ ከአገር መንደራቸው፣ ከሠፈር ቀዬአያቸውን ጥለው ቢሄዱም የገጠማቸው ግን ለማመን የሚከብድ፣ በዚህ በዲጂታል ዘመን ሰው እንደ ዕቃ ያውም በ400 ዶላርና ከዚህም ባነሰ ገንዘብ ሲሸጥ የታየበት መሆኑ እጅጉን ፍርኃትና ቁጣን አጭሯል፡፡ በየመገናኛ አውታሩ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች በከፍተኛ ደረጃ የዓለም ሕዝብ የተመለከተውን የአፍሪካ ወጣቶች የባርነት ሽያጭ ያጋለጠው ሲኤንኤን ነበር፡፡

ይሁንና ዘገባውን ተከትሎም በርካቶች በሊቢያ መንግሥትና በድርጊቱ በተሳተፉት ወንጀሎኞች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተስተጋባ ይገኛል፡፡ የማንችስተር ዩናይትድ አጥቂ ፈረንሣዊው ፖል ፖግባ በቅርቡ ክለቡ ከኒውካስትል ጋር ባደረገው ጨዋታ ወቅት ጎል አስቆጥሯል፡፡ ሆኖም ደስታውን የገለጸው ግን እጆቹን በኤክስ ምልክት በማመሳቀል በሊቢያ እየተፈጸመ የሚገኘውን የወጣቶች የባርነት ግፍ እንደሚያቆም በማሳየት ነበር፡፡

እንዲህ ያሉ ተቃውሞዎች እየተስተናገዱበት የሚገኘው የሊቢያው የባርነት ንግድ ካስቆጣቸውና ካሳዘናቸው መካከል በመንግሥታት ደረጃ የሩዋንዳ መንግሥት ይጠቀሳል፡፡ የሩዋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው፣ በሊቢያ ወጣቶች ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሚሞክሩበት ወቅት ተጠልፈው ለባርነት ሲዳረጉ የሚሳየው የቪዲዮ ምሥል እጅጉን አሳዛኝ ነው፡፡ የሩዋንዳ ሕዝብና መንግሥት አሁንም በአጋቾቻቸው እጅ ከሚገኙ አፍሪካውያን ወጣቶች ጋር እንደሚቆም ገልጾ፣ ወጣቶቹን ለመደገፍ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

እንዲህ ባለ መንገድ የአፍሪካ ወጣቶች ኑሮን ለማሻሻል፣ ራሳቸውን ለውጠው የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለመለወጥ በሚያደርጉት አስከፊ ስደት የሚደርስባቸው ሰቆቃ እየተባባሰ፣ የሚደርስባቸው ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ግፍ እየተበራከተ ቢመጣም የየአገሮቻቸው መንግሥታት ሁኔታውን ለመለወጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ወጣቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የማድረግ ዕርምጃ እምብዛም ሆኖ ይገኛል፡፡

በአፍሪካ ከሚገኘው የወጣቶች ቁጥር ውስጥ 200 ሚሊዮኖቹ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት የሚሆናቸው ሲሆኑ፣ አብዛኞቹም ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ከአዋቂዎች ይልቅ በሁለት እጅ ያነሰ በመሆኑ ለስደት፣ ለሕገወጥ ተግባራት፣ ለአመፅና ለሽብር ተግባራት በቀላሉ እንደሚመለመሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች