Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ ከ680 ሚሊዮን ብር በላይ በማትረፉ ለባለአክሲኖች ጠቀም ያለ የትርፍ ድርሻ ማከፋፈሉን ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2009 ዓ.ም. በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን ውጤት በማስመዝገብ፣ ውሱን የነበረውን የትርፍ ዕድገቱን ያሻሻለበት ዓመት እንዳሳለፈ አስታወቀ፡፡

 ከተቋቋመ በ18 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ንብ ባንክ፣ ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ዕድገት ካሳየባቸው አፈጻጸሞች ውስጥ ዓመታዊ የትርፍ መጠን ዕድገቱ ይጠቀሳል፡፡ እንደ ባንኩ ሪፖርት ከሆነ፣ በ2009 ዓ.ም. ከግብር በፊት 681.5 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ይህ ትርፍ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛው ብቻ ሳይሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲያስመዘግብ ከነበረው ትርፍ አንፃር የዓምናው ትርፍ ከካቻምናው በ222.7 ሚሊዮን ብር ወይም በ48.6 በመቶ ከፍ ማለቱም ትልቅ ውጤት ያደርገዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የነበረው የባንኩ የትርፍ ዕድገት እንደሚያሳየው ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት ተብሎ የተመዘገበው 36 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ውስጥ የትርፍ ዕድገቱ እየቀነሰ መምጣቱንም የባንኩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ2006 ዓ.ም. 415 ሚሊዮን ብር ሲያተርፍ የትርፍ ዕድገቱ ግን 36 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. 441 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ቢችልም፣ የትርፉ ዕድገት ግን በ26 ሚሊዮን ብር ላይ የተወሰነ ነበር፡፡ ካቻምና የተመዘገበው የትርፍ ዕድገት ወደ 18 ሚሊዮን ብር ወርዶ የ459 ሚሊዮን ብር ትርፍ ብቻ እንዲያስመዘግብ አስገድዶታል፡፡ የዓምናው ትርፍ ዕድገቱ ግን ካቻምና ካገኘው በ222.7 ሚሊዮን ብር ብልጫ በማሳየት ወደ 681.5 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡

የባንኮች የዕድገት መመዘኛ ከሚባሉት ውስጥ የተቀማጭ ገንዘብ፣ የተሰጠ አዲስ የብድር መጠንና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በመሆኑም በተጠቀሱት መስኮች ንብ ባንክ በ2009 ዓ.ም. የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንጃ ገልጸዋል፡፡ንብ ባንክ ከ680 ሚሊዮን ብር በላይ በማትረፉ ለባለአክሲኖች ጠቀም ያለ የትርፍ ድርሻ ማከፋፈሉን ይፋ አደረገ

 

በባንኩ ሪፖርት መሠረት በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በአራት ቢሊዮን ብር ጨምሮ 16.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ32.1 በመቶ ጭማሪ ያሳየው የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ካቻምና 12.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥርም በ26.1 በመቶ ጨምሮ ወደ 520,791 አድጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር በ2009 ዓ.ም. በተለያዩ የፋይናንስ ዘርፎች ውስጥ ካሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ከወለድ ነፃ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ476 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ተመልክቷል፡፡

ባንኩ በ2009 ዓ.ም. 6.44 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር የሰጠ ሲሆን፣ ይህም የብድር ክምችቱን ወደ 10.9 ቢሊዮን ብር ከፍ አድርጎታል፡፡ የሰጠው ብድርም በ42.4 በመቶ ወይም በ3.2 ቢሊዮን ብር ዕድገት እንዳስመዘገበ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ንብ ባንክ ለደንበኞቹ ካቀረበው ብድር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለማምረቻ ዘርፉ ወይም ለማኑፋክቸሪንግ የሰጠው ብድር ነው፡፡ ከጠቅላላ ብድር ውስጥ 21 በመቶውን ወይም 2.28 ቢሊዮን ብር ለማምረቻው ዘርፍ መዋሉን አቶ ክብሩ ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ካቻምና ለብድር ከሰጠው ጠቅላላ ገንዘብ ውስጥ 22 በመቶውን ለማምረቻ ዘርፍ እንዳቀረበ ይታወሳል፡፡

የንብ ባንክ ጠቅላላ ገቢ 1.94 ቢሊዮን ብር መድረሱም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ይህ ገቢ ከ2008 ዓ.ም. አንፃር ሲታይ በ517.6 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የ36.2 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦበታል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ወጪም 1.27 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የ294.8 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከካቻምናው በ30 በመቶ ብልጫ ታይቶበታል፡፡

ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት የተገኘው ገቢ በ135.8 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቶ 384.6 ሚሊዮን ብር እንደደረሰና ከዚህ ዘርፍ የተገኘው ገቢ ከባንኩ ጠቅላላ ገቢ ውስጥ የ19 በመቶ ድርሻ እንዲይዝ ከባንኩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በተለያዩ ዘርፎች ለአጠራጣሪ ብድሮችና ለሌሎች ሒሳብ መጠባበቂያ ወጪዎች ተቀንሶ ከታክስ በፊት 681.5 ሚሊዮን ብር ማትረፍ በመቻሉ፣ የተጣራ ትርፉን ከ2008 ዓ.ም. በ159.7 ሚሊዮን ብር ጨምሮ ወደ 516.4 ሚሊዮን ብር በመድረሱ፣ ለባለአክሲዮኖችም የተሻለ ትርፍ ድርሻ ለማከፋፈል አስችሎታል፡፡ ባንኩ ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል ያቀረበው 386.1 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ግን 266.3 ሚሊዮን ብር ለትርፍ ድርሻ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን 157 ብር አስገኝቷል፡፡

ንብ ባንክ በአሁኑ ወቅት 3,681 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. ብቻ 600 አዳዲስ ሠራተኞችን ለመቅጠር በቅቷል፡፡ በዚሁ ዓመት 329 ሠራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ከባንኩ መልቀቃቸው ታውቋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 21 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከ2008 ዓ.ም. አኳያ የ33 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባንኩ የሀብት መጠኑን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ በቅርቡ የገዛው ሕንፃና በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች የጀመራቸው ግንባታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች